>

ከምህረት ፍርድ መቅደም አለበት!!! (ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

ከምህረት ፍርድ መቅደም አለበት!!!
ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
 
*  ማሩኝ የሚሉ ሳይኖሩ፣ ይቅርታ እድርጌላችኋለሁ፣ ምሬአችኋለሁ ማለት ትርጉም የለውም፤
 
* ከመደመር ይቅደም መመርመር!!
የምንኖረው አብሪት፣ ትእቢት፣ ጭካኔ፣ ሴራና ግድያ በሞሉበት ዐለም ውስጥ ነው። ይህ የጭለማ ዐለም  የፍቅርን፣ የይቅርታንና የምህረትን ብርሃን ጠልቶ ሊያጠፋው እንደሚጥር እሙን ነው። ሆኖም ቦምቡ የተወረወረው ከላይ ለእርስዎ ቢሆንም፣ ከውስጥ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለማጥቃትና አሁን የተቀዳጁትን ፍቅር፣ አንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመንጠቅ የታቀደ እኩይ ሴራ ነው።
እርስዎ ያበሰሯቸው ይቅርታና ምህረት፣ በመሰረቱ፣ መልካም ቢሆኑም፣ ይቅርታና  ምህረት የሚደረጉት ስለ በደሉ ተፀፅተው፣ ይቅርታንና ምህረትን ለሚጠይቁ ሰዎች ብቻ ነው። አጥፍቻለሁ ይቅር በሉኝ፣ ማሩኝ የሚሉ ሳይኖሩ፣ ይቅርታ እድርጌላችኋለሁ፣ ምሬአችኋለሁ ማለት ትርጉም የለውም።  በዳዮቹ ስንትና ስንት ግፍ ፈፅመው፣ ሳይፀፀቱ፣ በቀላሉ ምሬአችኋለሁ ሲባሉ፣ ስላልተቀጡ፣ ታብየው፣ አዲስ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ። ለማድረስም ሲጥሩ እየታየ ነው። ይህ እውነት ለመሆኑ ማረጋገጫው ምህረት፣ ፍቅርና መደመር በሚሰበክበት ሰዐት፣ የተወረወረው ቦምብና አሁንም በሃገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚከሰቱት ትርምስና የህዝብ ፍጅት ናቸው።
እውነተኛ ምህረት ማድረግ የሚገባው፣ በዳይ በይፋ ወጥቶ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደተደረገው፣ ወንጀለኛም ፊት ለፊት ቆሞ “አጥፍቻለሁ፣ ተፀፅቻለሁና ይቅርታ አድርጉልኝ፣ ስለ ፍቅር በስመአብ ይቅር፣ እባካችሁ ማሩኝ” ሲል ብቻ ነው። ከዛ በፊት ግን ወንጀል የፈፀሙትን ገዳይዎችንና ሌቦችን ጨምሮ፣ ለፍርድ ማቅረብ ግድ ይላል። እነዚህ ግለሰቦች፣ ከያሉበት ተሰብስበው ተይዘው ወንጀላቸው በህግ ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ፣ ዘብጥያ መውረድ አለባቸው። ከዛ በኋላ ተፀፅተናል፣ አጥፍተናል ሲሉ ጉዳያቸው ተምርምሮ፣ ምህረት ሊደረግላቸው ይገባል። ስለዚህ ከምህረት ፍርድ መቅደም አለበት። መቼም እንደ እግዚአብሄር መሀሪ የለም። ሆኖም አግዚአብሄር እውነተኛ ፈራጅ ነው። በተለያዩ ጊዜያት በግፈኛች ላይ የፈረደ ቢሆንም ትልቁን ፍርድ ለዐለም ፍፃሜ ጊዜ አዘግይቶታል።
በዚህ ጊዜ ተደብቀውም ሆነ በጉልበታችውና በገንዘባችው ተማምነው ወንጀል የሠሩትን አጋልጦ ይፈርድባቸዋል። እግዚአብሄር መሀሪ እንደመሆኑ መጠን፣ ፈራጅም ስለሆነ፣ የእሱን ፈለግ ተከትሎ ፈራጅም መሆን ይገባል። ምህረትና ፍርድ እይነጣጠሉምና። ባለፉት 27 ዓመታት እና አሁንም ደም የሚያፋስሱትን እብሪተኞች መቅጣት ይገባል። እንዲህ ዐይነቶቹ እብሪተኞች፣ ፍቅርና ምህረትን እንደ ፍርሃትና ልምምጥ ስለሚቆጥሩት፣ እነዚህ መልካም ቃላት ያስቋቸዋል እንጂ ልባቸው ውስጥ አይሰርፁም።
ስለ መደመርም አንድ ቃል ማለት እፈልጋለሁ። በቀውጢ ቀን ከህዝብ ገፊዎች ጋር ተደምረው፣ ሀብትና ስልጣን ሲያካብቱ የኖሩትን መንገደኞች፣ ለማተባቸው ከቆሙት እኩል፣ በሉ ተደመሩን ብሎ መጋበዝ፣ ፍትህን ማጓደልና ፍርድን መበደል ነው። ስለዚህ፣ ከመደመር ይቅደም መመርመር።
ፖሊሶችና  ወታደሮችም ከአዲሱ ለውጥ ጋር አብረው እንዲራመዱ መታደስ አለባቸው። ዛሬ ያሉት  በተለይ ፌዴራል የሚባሉት ፖሊሶች፤ ሰውን ከመደብደብና ከመግደል በቀር ምንም ሙያ የላቸውም። እንደዚህ ለህግና ስርዐት ተገዢ እንዲሆኑ በአስቸኳይ መታደስ አለባቸው።
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች፣ ምስኪኑን ህዝብ ሳይጨርሱና ሳያጫርሱ፣ መሳሪያቸውን ድንገት ሳያስቡት፣ ከየቤታቸው መልቀምና ሀገር እስኪረጋጋ ድረስ እነሱን ጠራርጎ፤ ወህኒ ቤት ማቆየት በጣም ያስፈልጋል። ይህን ነገር ችላ ሳይባል በቶሎ እርምጃ ይቅደም!
Filed in: Amharic