>

አረጋኸኝ ወራሽ፣ ቀሺ ገብሩ፣ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን!!! (አሰፋ ሀይሉ)

አረጋኸኝ ወራሽ፣ ቀሺ ገብሩ፣ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን!!!
አሰፋ ሀይሉ
እምዬ ኢትዮጵያ — ከእንግዲህ — ወገን ከወገኑ የማይጨራረስባት የፍቅር ምድር ትሁን!!!
 
‹‹ስለፍቅር ሲባል.. ስለጥላቻ እያወራን.. ያሳለፍነው መንገድ ያሳዝናል››
 
ከጥቂት ዓመታት በፊት — በተንቀሳቃሽ ምስል ተደግፈው በኢቲቪ ከቀረቡ (እና ካልረሳኋቸው) — ዘጋቢ ፕሮግራሞች አንዱ — የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት በውጊያ ላይ ማርኳት… በእስር ላይ ቆይታ.. ኋላ ከመረሸኗ በፊት — በአንድ ጋዜጠኛ (መርማሪ) ቃለ-መጠይቅ ሲደረግላት ያየሁት — በቅፅል ስሟ ቀሺ ገብሩ — በእውነተኛ ስሟ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር — ስለምትሰኝ — ስለ አንዲት የህወኀት ተዋጊ ወጣት (‹‹ታጋይ››) የተመለከትሁት መሳጭ እና ልብ የሚነካ ታሪክ — አንዱ ነው፡፡
ስለዚያች በቲቪ መስኮት ስላየኋት ወጣት — ስለ ቀሺ ገብሩ — ባሰብኩ ቁጥር — ከምንም በላይ — ያ የገጠር ኮረዳ ከመሰለ የዋህና መንፈሰ-ቀሊል ከሚመስል ፊቷ በተቃራኒው —  በሁለመናዋ የተላበሰችው እጅግ አስገራሚ ፅናቷ —  ሁሌም ባሰብኳት ቁጥር ይገርመኛል፡፡ ሃቀኝነቷ ይገርመኛል፡፡ አንድ ሰው ወይም አንድ ሀበሻ — ላመነበት ዓላማ — እስከምን ድረስ በጽናት ሊጓዝ አቅም እንዳለው —  በተግባር ያሳየች — ህያው ምስክር ነች ባይ ነኝ በበኩሌ፡፡ አሁን እንዲህ — ደሃ በየመንገዱ ልጆቹን አስጥቶ በልመና እያደረ፣ ሰው ኑሮው ከእጅ-ወደአፍ ሆኖ አላላውስ ባለው በአሁን በእኛ ዘመን ላይ — እንዲህ ሌብነትን፣ ዝርፊያን፣ ዕብሪተኝነትን ብቸኛ ዓላማ አድርገው — እንዲህ ያለዕፍረት — በየአደባባዩ ሠላማዊ ወጣት ላይ ለመተኮስ፣ ድብደባ ለመፈጸምና ለማዋረድ ምንም የማይገዳቸውን — እኒህን የእሷን የዘመን የመከራ ጓዶች ማየት — በእውነቱ —  ምንኛ አሳፋሪ ነው?? ቀሺ ገብሩ — ዲሞክራሲ ለሀገሬ አሰፍናለሁ፣ እኩልነት አመጣለሁ፣ ፋሺስት መንግስትን አስወግዳለሁ ስትል እንዲያ መከራዋን በበላችበት፣ ህይወቷን በሰጠችበት አስከፊ መንገድ መጥተው — እንዲያው ከነበረው በላይ ሌብነትን ጨምረው — ቁጭ ያንኑ ሆነው የተገኙትን ጓዶቿን ብታይ — ያቺ ቀሺ ገብሩ ምን ታስብ ይሆን???
አይ አንቺ ሀገር — ያልታደልሽ!! 
ቀሺ የተማረከችው በጦር ሜዳ ላይ ነው፡፡ ምናልባት ምስጢር ብታጋልጥ፣ ወይ አንዳንዶቹ ምርኮኞች ምህረት ለማግኘት እንደሚሉት — እርሷም — ተገድጄ ነው ለወያኔ የዘመትኩት፣ ከእረኝነት ታፍኜ ነው የተወሰድኩት፣ የሚዋጉበትን ዓላማ አላውቀውም፣ ምንበትም፣ ልጅ ነበርኩ ተታልዬ ነው፣ ወዘተ ወዘተ ብትል ኖሮ — ምናልባት — ከደርግ አፍ — ወይም አፈሙዝ — የመትረፍ ዕድል የነበራት ይመስለኛል፡፡ እንደወትሮው ‹‹ባገር-የመጣች›› በሚል — ፈጽሞ ላይራራላት፣ ላይምራትም እንደሚችል እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡ አይ ሀገር! ሀገር ግን ምንድነው? ሀገር ድንበር ነው ያሉት እንደወጡ — ዳግም ወደወጡበት የሞቀ ቤታቸው ላይመለሱ — ቀሩ ተበልተው በእነ ቀሺ ገብሩ ጥይት፡፡ ዲሞክራሲ ያሉት፣ ነፃነት ያሉትም እንዲህ — ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው — እንደወጡ ቀሩ — በደርግ ጥይት ተበልተው፡፡ እውነት ሀገር ማለት ግን ምንድነው?? ምንድነው ሀገር — ያንዱ ልጅ በሌላኛው ልጅ የሚበላላበት ምድር ይሆን?? ወይስ የቀሺ እናት እና የደርግ ሠራዊት እናት — ሁለቱም እናቶች — በየተራ እንዲያለቅሱ የተጣፉበት የልቅሶ ምድር ይሆን ሀገር ማለት??? አይ አለመታደል?!!
ብቻ ግን አሁን ወደዚያች ወደማልረሳት ወደ ቀሺ ገብሩ ታሪክ ልመለስ፡፡ ያን የቀሺ ገብሩን ታሪክ ያየ ሁሉ ግን — የጋዜጠኛውን ስነልቦና ማጤን አያዳግተውም፡፡ የጋዜጠኛው አጠያየቅ ሁሉ — በቃ — ያቺን የሚጠይቃትን ወጣት ሴት ለማትረፍ ነው፡፡ ወይም እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ በተለያየ አቅጣጫ እያዟዟረ መላልሶ ያንኑ ጥያቄ ይጠይቃታል፡፡ አንዲት ለእርሱ ለፕሮፓጋንዳ የሚሆነው፣ ለእርሷ ደግሞ ለምህረት የሚሆናት — አንዲት ቅንጣት ማስተባበያ እንድትሰጠው፡፡ ሳልፈልግ ነው — ተገድጄ ነው — ገንጣዮች ናቸው ያሳሳቱኝ — ፍፁም ለማላምንበት ዓላማ ስዋጋ ነው የእናንተ የምህረት እጅ ላይ የጣለኝ — እንድትል፡፡ አሁንም አሁንም ደጋግሞ ይጠይቃታል፡፡ እሷ ግን ወይ ፍንክች! የጋዜጠኛውን አኳኋን ስታይ ልብህ ይነካል፡፡ ምንም ቢሆን እኮ — ምንም ለ‹‹ጠላት›› ስትዋጋ ብትያዝ — ምንም ቢሆን — አንተኑ የመሰለች — ወገንህ ነች — እና ታዝናለህ — ሴት ነች — ወጣት ነች — ታናሽ እህቱም ልትሆን የምትችል — እና ሊያተርፋት ይሟሟታል ለማሳመን፡፡ እርሱ — እርሷ አሳዝናዋለች፡፡ እኔ ደግሞ አሣዝኖኛል ጠያቂው፡፡ እና እርሷ፡፡ ሁለቱም፡፡ እና ሁላችንም፡፡ የሁላችንም ነገር — ስንቱ ተወርቶ ያልቃል? —
‹‹ስለፍቅር ሲባል.. ስለጥላቻ እያወራን.. ያሳለፍነው መንገድ ያሳዝናል››
 
እና ይቀጥላል ጋዜጠኛው፡፡ ምንም አልተገደድሽም? ይላታል፡፡ በፍፁም! ትለዋለች፡፡ ቆይ በሠላም በግብርና እየኖራችሁ አይደል ወያኔ መጥታ ከነጓደኞችሽ ለጦርነት የዳረገችሽ?? እና ከሠላም አውጥታ ለጦርነት ስትዳርግሽ ምን ይሰማሻል? ልክ ነው ብለሽ ታምኚያለሽ አንቺን የመሰሉ የዋሆችን ወደ ጥፋት መንገድ መጨመሩ? (ዓይነት የሚመስሉ ጥያቄዎችን እየደጋገመ ያቀርብላታል)፡፡ እሷ ሆዬ ግን — ፍንክች!! ደሞ ምንም መደባበቅ ብሎ ነገር አልፈጠረባትም፡፡ እቅጯን ነው ቁጭ የምታደርገው፡፡ በፍፁም! ማንም አላታለለኝም! አምኜበት ነው! እንዲያውም ልጅ ነሽ አትዋጊም ብለውኝ ነበር፡፡ በራሴ ፍላጎት ነው፡፡ ፋሺስቱን ደርግ ለማስወገድ እና ዲሞክራሲን ለማስፈን እየሞከርኩ ብሞትም አይቆጨኝ! ዓላማዬ ህዝቤን ነፃ ማውጣት ነው፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጨቋኝ አምባገነን ወታደራዊ ሥርዓት ነፃ ማውጣት ነው! ብዙ ጓዶቼ ተሰውተዋል! እኔም አብሬ ለመሰዋት ዝግጁ ሆኜ ነው ወደ ትጥቅ ትግል የወጣሁት፡፡ አሁንም ጓደኞቼ ሞተው እኔ ከምተርፍ… አብሬያቸው ብሰዋ ደስ ይለኝ ነበር! ላለመማረክ ብዙ ጥሬያለሁ እዚያው እንዲጨርሱኝ! አሁንም የመጣብኝን እቀበላለሁ! ለህዝቤ በመዋጋቴ ክብርና ጀግንነት ይሰማኛል እንጂ አላፍርበትም! ወዘተ ወዘተ ወዘተ… ብዙ ማለቂያ የሌላቸው፡፡ ወኔ የተሞላባቸው፡፡ ስሜት ቀስቃሽ ምላሾች..፡፡ ፍፁም ፍርሃት ያልጎበኘው ቆራጥ የወጣት መንፈስ፡፡ ጀግንነት የሞላው የሴት ልብ፡፡
ያመነችበትን ያለፍርሃት ትናገራለች፡፡ ገረመኝ፡፡ አዘንኩም፡፡ እንደ ጋዜጠኛው፡፡ ከሞት አፋፍ ሊያተርፋት ሞክሮ ሞክሮ እንዳልቻለው፡፡ እንዳዘነው ጋዜጠኛ — እኔም አዘንኩ፡፡ ታሳዝናለች በእውነት፡፡ ቀሺ ገብሩ እንግዲህ ይህች ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ ምላ ቆርጣ የወጣች — ላመነችበት ዓላማ እስከመጨረሻዋ ጠብታ የታገለች — ሃቀኛ! ፊትለፊት! እና የዋህ! የሆነች — እጅግ አስገራሚ ፍጡር!! |በነገራችን ላይ ከዚያ ወዲህ የወጣውንና የህወኀትን ወጣት የትጥቅ ታጋይ የቀሺ ገብሩን ህይወት ታሪክ የሚያሳየውን ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› ስፖንሰር አድርጎ ያሠራው የሚያማምሩ ስፌቶችን በመስፋት በዓለም በሚታወቁት የሐረሪ ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡|
የቀሺ ገብሩን ታሪክ ከመፈጸሜ በፊት ግን ስለ አረጋኸኝ ወራሽ አንድ ነገር ልበል፡፡ ቀሺ ገብሩንና አረጋኸኝ ወራሽን ለመሆኑ ምን አገናኛቸው?? — የሁሉም ጥያቄ መሆን እንደሚሆን እገምታለሁ፡፡ አረጋኸኝ ወራሽንና ቀሺ ገብሩን ያገናኘቻቸው አንዲት ቀጭን ኪስ ነች፡፡ የአንድ ከመሐል ሀገር በውትድርና ተመልምሎ — የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብራለሁ በማለት — ከእነ ቀሺ ገብሩ ጋር ሊዋጋ ከወጣ — እና እንደወጣ በእነ ቀሺ ገብሩ ጥይት በጦር ሜዳ ህይወቱ ካለፈች — ከአንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ አስከሬን ኪስ ውስጥ — የተገኘ ካሤት ነው — የቀሺ ገብሩና የአረጋኸኝ ወራሽ ግጥምጥሞሽ፡፡ በሟቹ ኪስ ውስጥ የተገኘው የአረጋኸኝ ወራሽ በወቅቱ ፋሽን የነበረ ተወዳጅ ዘፈን የተቀረፀበት — ኦሪጂናል ካሤት ነበር — በዚያ ለሀገር ብሎ ወጥቶ በቀረው ወጣት ኪስ ውስጥ፡፡ /NB. አሁን ላይ ይህን የልጁን ፍፃሜ ሳስብ… ይህኛውስ ልጅ እናት ይኖሩት ይሆን? የፈረደባት እናቱ እንዴት ስታለቅስ ትኖር ይሆን? የሚል የሆነ ወገናዊ የሐዘን ስሜት… ሰውነቴን ጠልቆ ይመዘምዘኛል፡፡ ቃላት የለኝም፡፡ ስሜት ብቻ የሚገልጸው የወገን እርስ-በርስ እልቂት ሐዘን እና የፈሰሰው እንደማይታፈስ ያወቀ ሀገራዊ ቁጭት የሚመላለስበት ልብ፡፡ ያ ነው ያለኝ፡፡ ያ ነው የሚሰማኝ፡፡ ሳስብ፡፡/
አሁን ወደ ካሤቱና ወጣቶቹ እንመለስ፡፡ ከላይ ያለውን የተናገረው — አሁን በህይወት ያለው — እና በኢቲቪ ስለ ቀሺ ገብሩ ሲናገር — እንባ ከአይኖቹ የሚቀድሙት — የቀድሞ የህወኀት ትጥቅ ታጋይ — የነበረ — በዘመኑ — የቀሺ ገብሩ — የትግል ሜዳ አጋርና — የፍቅር ጓደኛ — ወይም እጮኛዋ የነበረ — የህወኀት የበረሃ ወጣት፡፡ አሁን ላይ — በቴሌቪዥን — የዚያኔውን የቀሺ ገብሩን የመጨረሻ ቃለመጠይቅ ሲያሳዩት — በቲቪው መስኮት እየተቀረፀ — ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ እርሱም ደግሞ አሳዘነኝ፡፡ ልቤን በላው፡፡ ፍቅረኛውን አስገድሎ፣ ወገኑን ገድሎ፣ ነፃነትን ለማውጣት፣ አስቸጋሪውን መንገድ አልፎ የመጣ፣ ወይ ከፍቅሩ ያልሆነ፣ ወይ ከምኑ ያልሆነ ሃቀኛ፣ ቀቢፀ-ተስፈኛ ወጣት መሆኑ — እጅጉን አድርጎ  ልቤን ነካው፡፡ አሳዘነኝ የምሬን፡፡
 
 ‹‹እኔና እሷን ያፋቀረችን አንዲት ካሤት ናት›› አለ፡፡ እንዴት? 
 
እና ይህ የቀሺ ገብሩ የትግል ጓድ እንዴት ከእሷ ጋር ሊግባቡና ወደፍቅር ሊያመሩ እንደቻሉ.. የመጀመሪያዋን አጋጣሚ ሲናገር… ‹‹እኔና እሷን ያፋቀረችን አንዲት ካሤት ናት›› አለ፡፡ እንዴት? ላለው ጋዜጠኛ ሲያስረዳ… በወቅቱ በእርግጥ በትግል ላይ ሆነህ ፍቅር መጀመር ክልክል ነበር፡፡ ነገር ግን እኔና እሷብዙ ጊዜ አንድ ጦርሜዳ አብረን እየተሰለፍን ስለቆየን እየተያየን እንደተዋደድን ገብቶኛል፡፡ አንድ ቀን ቅልጥ ካለ ጦርነት በአሸናፊነት ወጣን፡፡ ብዙ ‹‹የጠላት›› አስከሬን ነበረ፡፡ ከኛም ብዙ ታጋይ ተሰውቶብናል፡፡ እና ቀሺ ገብሩ በህይወት ብትተርፍም፣ አሸናፊ ሆና ብትወጣም፣ በቁጭት እያለቀሰች ነበር፡፡ እና ሳያት አሳዘነችኝ፡፡ እና ያን ካሤት እንቺ ስጦታዬ ነው ብዬ ሰጠኋት፡፡ ካሤቱ በወቅቱ በትግል ላይ እያለን በየሄድንበት የምንሰማው.. እና በጣም ተወዳጅ የነበረው.. የአረጋኸኝ ወራሽ ኦሪጂናል ካሤት ነበር፡፡ ካሤቱ ያን ዕለት የአንድን ‹‹ጠላት›› አስከሬን ኪስ ስፈትሽ ያገኘሁት ነበር፡፡ እና በቃ እሱ ነው ያገናኘን እኔንና እሷን፡፡ ሌላ ጊዜ አዳመጠችና ለምን ሰጠኸኝ? አለችኝ፡፡ ስለምወድሽ ነው አልኳት፡፡ እና የኔና የእሷ ፍቅር ከዚያች ካሤት በኋላ በዚያው የትግል በረሃ የተጀመረች መከራ ያልተለያት ፍቅር ነበረች፡፡ ነበር ያለው፡፡ ይገርማል፡፡ ይገርማል ብቻ ሳይሆን ልብም ይነካል፡፡ ልብም ይነካል ብቻ ሳይሆን ግራም ያጋባል፡፡ በቃ… ቅድም ብዬው የለ? ድምፃዊውስ ብሎት የለ?? አዎ፡፡ በቃ፡፡ .. ያሳለፍነው መንገድ ያሣዝናል፡፡
እምዬ ኢትዮጵያ እንዲህ በመሠለ መልኩ ነበር… ወገንና ወገን.. በሁለት በሶስት በአራት ጎራ ተሰልፎ… ሲጋደል የኖረው፡፡ አንዱ ከሚኖርበት ከተማ.. ወደ ጦርሜዳ… የአረጋኸኝ ወራሽን ካሤት በኪሱ ይዞ… እናት ሀገሩን ብሎ ሊሠዋ ይወጣል፡፡ ሌላው ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ብሎ.. ከሚኖርባት ጎጆ… ሕዝብን ዓላማን ብሎ ሊሠዋ ይወጣል፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ ልጆች — በዚያው የጦር ሜዳ — ይገዳደላሉ፡፡ እንደ ፍቅር ጥሎሽ ከአንዱ ኪስ ወጥታ ወደሌላው ኪስ የገባችው የአረጋኸኝ ወራሽ ካሤት ደግሞ — ለቀሺ ገብሩ — በፍቅር ስጦታነት ትበረከታለች፡፡ ቀሺ ገብሩ ደግሞ — ከእነያዘቻት ካሤት — በድጋሚ — ካሤቷን መጀመሪያ በኪሱ ይዟት የነበረው የሟቹ ወጣት የደርግ ሠራዊት እጅ — በጦርሜዳ ትማረካለች፡፡ ወገን ወገኑን ገድሏል፡፡ የሞተው ሞቷል፡፡ ያጣውን የጎደለበትን ቆጥረን አንጨርሰውም፡፡ የተረፈውም አሁንም በቲቪ መስኮት በእንባ ጎርፍ ሲጥለቀለቅ ያየነው ነው፡፡ ወገኖች መተላለቃቸውን አያቆሙም፡፡ አረጋኸኝ ወራሽም መዝፈኑን ይቀጥላል፡፡ ይህን የወገን ትራጀዲ የምናቆምበት መላ ሣናበጅ — አንዲትም ስንዝር ወደፊት አንራመድም፡፡ ባይ ነኝ በበኩሌ፡፡
እምዬ ኢትዮጵያ — ከእንግዲህ — ወገን ከወገኑ የማይጨራረስባት የፍቅር ምድር ትሁን!!!
ከጥነት እስከ ዘንድሮ ለሞቱት — እንደቅጠል ለረገፉት — ወጥተው ለቀሩት — እናቶቻቸውን ላስለቀሱ — የእምዬ ኢትዮጵያ ልጆች — ለሁሉም — ነፍሳቸውን ይማር፡፡ የእናቶቻቸውን ልብ ያፅናና፡፡ የወገኖቻቸውን ልብ ያራራ፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ — ከእንግዲህ — ወገን ከወገኑ የማይጨራረስባት — የተባረከች — የአንድ እናት ልጆች መሠማሪያ — የክበር መስክ፣ የፍቅር ምድር ትሁን፡፡ አምላክ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ — ከትውልድ እስከ ትውልድ — በፍቅሩ፣ በፀጋው፣ በምህረቱ — ይባርካቸው፡፡ ኢትዮጵያ — ለዘለዓለም — ትኑር፡፡
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic