>

ደርግና ፡ ኢሕአዴን ...ምን አንድ አረጋቸው?- ሠላሣ  ሦስት (ሺህ) ቃላት ብቻ! (አሰፋ ሀይሉ)

የደርግ ቃላት — ‹‹ከሕውስታ›› እስከ ‹‹ሸማቾች››!! 
 
    — ደርግና ፡ ኢሕአዴን … ምን  አንድ  አረጋቸው ? — ሠላሣ  ሦስት (ሺህ) ቃላት ብቻ !
አሰፋ ሀይሉ
۝በደርግ ኢሠፓአኮ አማካይነት ከ1973 እስከ 1978 ተዘጋጅቶ ከታተመው የደርግ ‹‹ማርክሳዊ ሌኒናዊ መዝገበ ቃላት›› እየፈለቁ ወጥተው …. ለበርካታ ዓመታትና አሁንም ጭምር ከየብዙሃን መገናኛ ማሰራጫዎች  እና ከገዢው ፓርቲ ልሳን በየጆሯችን ሲለቀቁ የኖሩት ቃላትና ሐረጎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ቃላቱ ማለቂያ የላቸውም!
۝۞۝ ከ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› እስከ ‹‹ቀያጭነት››፣ ከ‹‹መገንጠል›› እስከ ‹‹ውሣኔ ሕዝብ››፣ ከ‹‹መፈክር›› እስከ ‹‹ሽብር››፣ ከ‹‹ሠላማዊ ሠልፍ›› እስከ ‹‹ሕዝባዊ አመፅ››፣ እና ሌሎች በዘመነ ደርግ-ኢሠፓአኮ ተፈጥረው… በዘመነ ወያነ-ኢህአዴግ ጥቅም ላይ የዋሉ የትየለሌ አብዮታዊ ቃላት አሉን!
መቼም በብዙዎች እንደሚታወቀው . . . ያው በተለምዶ ‹‹ደርግ›› እየተባለ የሚጠራው በዕለተ ዓርብ፤ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ/ም በሬዲዮ በተነበበ አዋጅ ለተቋቋመው ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› … መጠሪያነት ‹‹ደርግ›› የሚል አጭር ስያሜ ተሰጥቶት የተቋቋመ፣ 120 (በትክክል 109) አባላት ያሉት፣ ከየጦሩ የተውጣጣው የበታች ወታደሮች ኮሚቴ ነው፡፡ ይህን ኮሚቴ ወይም ደርግን ያቋቋሙትም በወቅቱ ከመላ ሃገሪቱ ተውጣጥተው በአዲስ አበባ አራተኛ ክፍለጦር በተሰበሰቡበት -ከ3ኛ ክፍለጦር የመጣው ሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማርያም፡- ‹‹እኛ እዚህ የተሰበሰብነው… ንጉሡን ለማሠር ነው? ወይስ ሀገር ለመምራት? ንጉሡን ስለማሠር ነው የምናወራው? ወይስ በሕዝብ ስለተጣለብን ታሪካዊ አደራና ስለንምፈጽመው ታሪካዊ ገድል?!›› የሚል ‹‹የተቀናበረና ስሜት ቀስቃሽ›› ንግግሩን ካሠማ በኋላ፡   ‹‹ሊቀመንበሩ አሁኑኑ ይመረጥ!›› በማለት ሻለቃ መንግሥቱ ያቀረበውን ሐሳብ ተቀብለው በሰጡት የምሥጢር  ድምፅ፡-  መንግስቱ ኃ/ማርያምን ሊቀመንበራቸው፣ አጥናፉ አባተን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበራቸው አድርገው የመረጡት የቀኃሥ ወታደራዊ መኮንኖች ቡድን ነው — ‹‹ደርግ››፡፡
ልክ እንደሌሎቹ እንደ እነ ‹‹ቀበሌ››፣ ‹‹ሕብረት-ሱቅ››፣ ‹‹ሕዝባዊ ማደራጃ››፣ ‹‹ወዛደር››፣ ‹‹አርሶአደር››፣ ‹‹ከፍተኛ››፣ ‹‹አድሃሪ››፣ ‹‹አብዮታዊ››፣ ‹‹ሕዝባዊ››፣ ‹‹የፓርቲ ልሳን››፣ ‹‹ሰፊው ሕዝብ››፣ ‹‹ጠባብነት››፣ ‹‹አድኃሪያን››፣ ወዘተ ወዘተ ወዘተ እንደሚሉት ከአብዮቱ ዘመን እንደወረስናቸው የወቅቱ ሶሻሊስታዊ ቃላት… ‹‹ደርግ›› የሚለው ቃል ‹‹ኮሚቴ›› ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአቻነት የተቀመጠ የደርግ-አብዮት የወለደው ቃል ነው፡፡ በአጭሩ ‹‹ደርግ›› የሚለው ቃል ትርጉም… ‹‹የሰዎች ስብስብ ወይም ጉባዔ›› እንደማለት ነው፡፡ ይሄም ‹‹ሕዝባዊ ኮሚቴ›› እየተባሉ ይታወቁ ከነበሩት የሩሲያ አብዮተኞች ዘንድ… የተዋስነው  — ከአማርኛ ነባር መዝገበ-ቃላት ተጎልጉሎ — ለአብዮቱ ጥቅም የዋለ የአማርኛ ቃል፡፡
‹‹ደርግ›› ለቃላት ፍቺ እየሰጠ ማሳተም ከመጀመሩ በፊትም ቀደም ብለው የታተሙ… በሃገራችንም የታወቁ – ሁነኛ መዝገበ ቃላት ነበሩ፡፡ በምሳሌነት፡- የእነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ፣ የእነ ከሣቴብርሃን ተሰማ፣ የእነደስታ ተክለወልድ፣ የእነዎልፍ ልሳል፣ የእነ አባ ዮሐንስ ገ/እግዚአብሔር፣ የአባ ጊዮርጊስ፣ አለቃ አጥሜ፣ የእነ አለቃ ታዬ እና ሌሎችንም — በጃንሆይ ልዩ ድጋፍ በሊቃውንት ተዘጋጅተውና ታትመው — ጥቅም ላይ የዋሉ የቃላት ፍቺን የያዙ ጥራዞች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የተቀጣጠለው የአብዮቱ ወላፈን ግን… እነዚያ መዝገበ-ቃላት ውስጥ የተከማቹ ሀገርኛ ቃላት እጅግ ልዝብ ሆኑበት፡፡ የሚፈልገውን አመጸኛ፣ ኃይለኛ፣ አንበርካኪ የሆኑ… እና ፈጣን እርምጃዎችንና እንቅስቃሴዎችን የሚፈጥሩ… ‹‹ወቅታዊ›› የማታገያ ቃላትን.. ወይም የዘመኑን ‹‹ነባራዊ ሁኔታ›› በትክክል የመግለጽ አቅም ያላቸውን ቃላት ፈልጎ አጣ፡፡ ደርግ፡፡ ወይም ባጭሩ የራሳችን ሀገር-በቀል ቃላት — ‹‹ተራማጅ›› ሆነው — አላገኛቸውም፡፡ ወይም የራሳችን ነባር ቃላት.. ሊፈጥሩ የሚችሉት..  ህዝባዊ ግለት.. አንጀቱን ‹‹አላረⷋውም››፡፡
ስለዚህ ኢሠፓአኮ (ማለትም፡- ‹‹የኢትዮጵያ ሠርቶአደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ››)… እጅግ በከፍተኛ ጥረት… የራሱን አዳዲስ የአብዮተኞችንና የተራማጆችን ቃላት የያዘ አብዮታዊ መዝገበ ቃላት አሣተመ፡- ‹‹የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት›› (ወይም ‹‹የተራማጅ መዝገበ ቃላት››) የሚባል፡፡
ያ ‹‹የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት››፤ በ1978 ዓ.ም.፤ በአዲስ አበባ የታተመው  በ‹‹ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት››  ሲሆን፤ የመዝገበ ቃላቱ ሥራ የተጀመረው በ1973 ዓ.ም.፤ ለማጠናቀቅ የፈጀው ጊዜ ደግሞ 5 ዓመት ነበረ፡፡ ለዚያ መዝገበ ቃላት የመጀመሪያዎቹን ብዛታቸው 600 የሆኑ ቃላት ያዋጣው የኢሠፓአኮ ርዕዮተዓለም መምሪያ ሲሆን፤ የመዝገበ ቃላቱ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ደግሞ፡- ከኢሠፓአኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት፣ ከየካቲት 66 የፖለቲካ ት/ቤት፤ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ አባላት ነበሩበት፡፡
ብቻ ግን ያን መዝገበ ቃላት ያየ . . . አዳዲስ ቃላትን በመፍጠር … ‹‹ኮንፈረንስ›› ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› ‹‹ዝቅጠት›› ‹‹ቦናፓርቲዝም›› ‹‹ጥገኝነት›› ‹‹ጠባብነት›› ‹‹ሙሰኝነት›› ወዘተ ወዘተ እያለ በየዕለቱ አዳዲስ ቃላት ከሚፈበርከው ከኢህአዴግ በባሰ መልኩ… ለካንስ ደርግ አቻ የማይገኝለት የቃላት አመንጪ፣ የቃላት ማበልፀጊያ ተቋም እንደነበረ ይገነዘባል፡፡ የሚገርመው እኮ አሁን በዚህኛው ገዢ ፓርቲና መንግሥቱ ጠዋትና ማታ የምንሰማቸው ቃላት ራሳቸው የመነጩት ከእነዚያ ደርግ ካመረታቸው የሌኒኒስት ኮሚኒስት መዝገበ ቃላት መሆናቸውን ስንረዳ ጭምር እኮ ነው፡፡ ህወሀትም ሆነ ኢህአዴግ ‹‹በደርግ መቃብር ላይ ዲሞክራሲ ያብባል›› ብለው የተነሱና ድልም የቀናቸው ኃይሎች መሆናቸውን ላየ… እንዴ… ግን እንዴት ነው ታዲያ… እነዚያን ሁሉ የደርግ ቃላት ጥቅም ላይ የዋሉት?? እሳት እና ጭድ ምን አንድ አረጋቸው? ማለቱ አይቀርም፡፡ ወይም ደግሞ በተቃራኒው … እሺ . . . ደርግና ኢህአዴግን በምን እንለይ?? ብሎ መጠበቡ፡፡
አሁን ወደቃላቱ እናምራና ከደርግ ኢሠፓአኮ መዝገበ ቃላት ውስጥ ከተገኙት ብዙ ብዙ ኢህአዴጋዊ ቃላት መካከል…  እስቲ ለትውስታ ያህል የተወሰኑትን ከነተገኙበት ገጽ እናውርዳቸው፡፡ እና  . . . ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዕውቅ የአማርኛ ግዕዝ መዝገበ ቃላት እና ከዚያኛው ከኢሠፓአኮ መዝገበ ቃላት የትኛውን በአሁን በእኛ ማህበራዊ፣ ብዙሃን መገናኛና ፖለቲካዊ መድረኮች ሲስተጋባ እንደምናገኘው. . . እስቲ ራሳችን እንፍረድ፡፡ ለመፍረድ ብዙ ጥልቅ ምርምር ማድረግ አያስፈልግም፡፡ ሕውስታችንን ብቻ መጠቀም በቂ ነው፡፡ ይቅርታ – ሕውስታ – ከትውስታ ይለያል፡፡ ‹‹ሕውስታ›› ምን እንደሆን ለማወቅ ከፈለግህ – ወደ ‹‹ማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት›› በቀጥታ አምራ፡፡ አሁን ወደ መዝገብ-ቤት፡፡ ወደቃላት መዝገብ ቤት፡፡ መልካም ቃላት፡፡
እነሆ ተጀመረ በ‹ሕውስታ› !  ‹‹ትውስታ›› አላልኩም – ‹‹ሕውስታ››! ! !
1) ‹‹ሕውስታ››
‹‹ሕውስታ›› ይልና ምንም ማለት እንደሆነ በእንግሊዝኛ ‹‹Sensation›› ብሎ በማስቀመጥ እንዲህ ሲል ይተረጉመዋል፡- ‹‹ሕውስታ የስሜት አካላት የሚያከናውኑትን ተግባር፡- ማሽተትን፣ ማየትን፣ መስማትን፣ መዳሰስን የሚገልጽ ሕዋስ ከሚል የግዕዝ ቃል የመጣ ነው፡፡… ነባራዊው ዓለም በሰው ሕዋሳት ላይ የሚያደርሰው የመጀመሪያውና ቀጥተኛው ተጋብሮት ነው፡፡›› ሲል ይናገራል፡፡ (ገጽ 18)
2) ‹‹ኂስና ግለኂስ››
‹‹ኂስና ግለኂስ›› (Criticism and Self-criticism)፡- ‹‹ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን መመሪያቸው ያደረጉ አብዮታዊ ፓርቲዎችና ሌሎች የሠራተኛ ድርጅቶች አብዮታዊ ተግባራቸውን በሚያካሄዱበት ጊዜ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚፈጽሙትን ስህተት በግልጽ እያነሡ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚተቻቹበት፣ የሚወቃቀሱበት፣ የሚተራረሙበትና ትምህርት የሚወስዱበት ዘዴ ኂስና ግለኂስ ይባላል፡፡ (ገጽ 27)
3) ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ››
‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› (Revolutionary Democracy) :- ‹‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› በሠራተኛው መደብ የትግል ታሪክ የመጀመሪያው ወቅት፤ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ከከተማው ንዑስ ከበርቴ፣ ከገበሬውና ከተራማጁ ምሁራን መካከል የፖለቲካ ንቃት ያላቸውን ፀረ-ፊውዳልና ፀረ-ካፒታሊስት የሆነውን ትግል የሚደግፉትን፤ ለዚህም የሚታገሉ ክፍሎችንና እንዲሁም የነዚሁኑ ፍላጎትና ጥቅም የሚያራምዱ ፓርቲዎችን፣ ድርጅቶችንና ቡድኖችን የሚያጠቃልል ቃል ነበር፡፡ በአሁኑ ታሪካዊ ወቅት ደግሞ በዕድገት ወደ ኋላ በቀሩና ካፒታሊዝም እምብዛም ባልተስፋፋባቸውና ባልተጠናከረባቸው ሀገሮች ለብሔራዊና ለማህበራዊ አርነት የሚታገሉ ኃይሎችን በዚህም ውስጥ ለጋ የሆነውንና በማደግ ላይ የሚገኘውን የሠራተኛ መደብ እንቅስቃሴም የሚያጠቃልል ቃል ነው፡፡›› (ገጽ 287)
4) ‹‹ጓድ›
‹‹ጓድ›› (Comrade) የሚለውን መጠሪያ ቃል ትርጉም ደግሞ እንዲህ በማለት አስቀምጦት እናገኘዋለን፡- ‹‹ለሶሻሊዝምና ለኮሚኒዝም ድል አድራጊነት በሚደረገው የመደብ ትግል በግንባር ቀደምትነት ሰፊውን ሕዝብ በመምራት በመሥዋዕትነት የታገሉና የሚታገሉ ተራማጅ ኃይሎች፣ ታጋይ አብዮታውያንና የሰፊው ሕዝብ ወዳጆች እርስበርስ የሚጠራሩበት የትግል አንድነትን የሚገልጽ የወል ስም ነው፡፡… ቃሉ ማንም ሰው ተነሥቶ በራሱ የሚካነው ወይም የሚሞካሽበት ተራ ስም ሳይሆን ለሕዝባዊ ዓላማ በቁርጠኝነት መታገልንና መሥዋዕት ለመሆን ዝግጁ መሆንን የሚያመለክት ጥልቅ ትርጉምና መልዕክት ያለው ክቡርና ታላቅ መጠሪያ ነው፡፡›› (ገጽ 461)
5) ‹‹አድርባይነት›› 
‹‹አድርባይነት›› (Opportunism) የሚለውን ቃል ደግሞ እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፡- ‹‹በሠራተኛው መደብ እንቅስቃሴ ውስጥ በንድፈ ሐሳብና በተግባር የሠርቶ አደሩን መሠረታዊ ፍላጎት በጥቂት ጊዜያዊ ጥቅሞች ለቡርዧዚው አሳልፎ የመሸጥና በመራራ ትግል ለሚከፈል መሥዋዕትነት ዝግጁ ያለመሆን አድኃሪ አዝማሚያ ‹አድርባይነት› ይባላል፡፡›› (ገጽ 307)
6) ‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበር››
‹‹የኅብረት ሥራ ማኅበር›› (Cooperatives) :- ‹‹አነስተኛ የኢኮኖሚ ይዞታ ወይም ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ገንዘባቸውን ወይም የማምረቻ መሣሪያቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር ምርታቸውን ለማሳደግና የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ወይም የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት በፈቃደኝነት የሚያቋቁሙት ድርጅት ኅብረት ሥራ ማኅበር ይባላል፡፡›› (ገጽ 31)
7) ‹‹ሉዓላዊነት››
‹‹ሉዓላዊነት›› (Sovereignty) :- ‹‹‹ሉዓላዊ› የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የበላይነት ማለት ነው፡፡ አንድ መንግሥት የውስጥና የውጭ ፖሊሲውን ለመንደፍና በተግባር ላይ ለማዋል ያለው የመጨረሻው ከፍተኛና ነፃ የሆነ ሥልጣን ወይም ኃይል ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሕግን በሚመለከት ረገድ ‹ሉዓላዊነት› የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በአሥራ ስድስተኛው ምዕት ዓመት በጥቅም ላይ ያዋለው ዣን ቦዳ የተባለ ፈረንሳዊ ምሁር ነበር፡፡… የአንድ መንግሥት የሀገር ውስጥ የሉዓላዊነት ሙሉነት ከውጭ ኃይል ነፃ ከመሆኑ ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ አንድ መንግሥት በውጭ ኃይል ተፅዕኖ ሥር እስከ ወደቀ ድረስ በሀገር ውስጥ የሚኖረው ሉዓላዊነት ውሱን ይሆናል ማለት ነው፡፡›› (ገጽ 34)
8) ‹‹ሁኔታ›› 
‹‹ሁኔታ›› (Condition) :- ‹‹ሁኔታ ከተገብሮት ቀድሞ የሚገኝ፤ ነገር ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተገብሮት ወሳኝ ክስተት ያልሆነ፤ የአንድ ነገር ውስጣዊ ቅራኔ የሚከናወንበት አካባቢ ነው፡፡ ሁኔታ ውስጣዊ ቅራኔ የሚከናወንበት ውጫዊ ቅራኔም ሊሆን ይችላል፡፡ ሁኔታ በርካታ ነገሮች ለአንድ ነገር መገኘት አስፈላጊ ሆነው ሣለ፤ ነገር ግን አንዱ ወሳኝ ሆኖ እራሳቸው በራሳቸው የወሳኝነት ሚና ባይኖራቸውም ለነገሩ ወይም ለድርጊቱ መከናወን፤ ወይም ለተግብሮቱ መገኘትና መሟላት ባለባቸው ነገሮች መስክ ሲገኝ ያን ለመግለጽ የሚውል ቃል ነው፡፡ ሙቀት፣ አፈርና እርጥበት ስንዴን ወደ ቡቃያነት እንዲለወጥ ቢያስፈልጉትም የስንዴው ወደ ቡቃያነት የመለወጥ ጉዳይ የውስጣዊ ባህርይ ተገብሮት እንጂ በተጠቀሱት ነገሮች መንሥዔነት አይደለም፡፡ ስለዚህ የተጠቀሱት ነገሮች ሲገኙ ሁነታቸውን ወይም መኖራቸውን ለመግለጽ ሁኔታ ተብለው ይጠራሉ፡፡›› (ገጽ 54)
9) ‹‹መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች›› 
‹‹መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች›› (Middle Strata) ፡- ‹‹በካፒታሊስት ሥርዓት በወዝአደሩና በቡርዧዚው መካከል የሚገኙ መደቦችና የኅብረተሰብ ክፍሎ ናቸው፡፡ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ዝቅተኛ ነጋዴዎች፣ ትናንሽ የማምረቻ ድርጅቶች ባለቤቶችና መካከለኛ ገበሬዎች፣ እንዲሁም የግል ሀብት የሌላቸውና ለካፒታሊስቶች ተቀጥረው ዕውቀታቸውን በመሸጥ የሚተዳደሩ ምሁራንና የቢሮ ሠራተኞችና የሙያ ሠራተኞች፣ በግለሰቦች ቤት ተቀጥረው የሚሠሩና ሌሎችም ከተለያዩ መደቦች የተንጠባጠቡ ክፍሎች ሁሉ በመካከለኛ የሕብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ይጠቃለላሉ፡፡ በአጠቃላይ መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማኅበረሰቡ ውስጥ በያዙት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቦታ የተነሣ በፖለቲካ አቋማቸው አንድ ጊዜ ከሠራተኛው መደብ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቡርዧዚው ጋር የመቆምን ባሕርይ ስለሚያንፀባርቁ ወላዋይነትና የአለመረጋጋት ባሕርይ ይታይባቸዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የካፒታሊስቱ ሥርዓት ብዝበዛ እየከፋና የኑሮ ሁኔታቸውም እያዘቀጠ ሲሄድ ወደ ወዝአደርነት እየተለወጡ የሚሄዱ ናቸው፡፡ ለሶሻሊዝም በሚደረገው ትግል ሠራተኛው መደብ መካከለኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደቅርብ አጋሮቹ ይመለከታቸዋል፡፡›› (ገጽ 63)
10) ‹‹መገንጠል›› 
‹‹መገንጠል›› (Secession) :- ‹‹ከአንድ መንግሥታዊ አስተዳደር ወይም ሀገር በስምምነት ወይም በኃይል መለየት መገንጠል ይባላል፡፡ የመገንጠል ጥያቄ ሁለት ወይም ብዙ ብሔሮች ባሉበት መንግሥት ውስጥ በጨቋኝ መንግሥት ሥር ያለ የተጨቆነ ብሔር ከሚደርስበት አስከፊ ብዝበዛና ጭቆና ለመላቀቅ የራሱን መንግሥት በማቋቋም መብቱን ለማስከበር የሚያነሣው ጥያቄ ነው፡፡ ይህም ጥያቄ ጭቁን ብሔሮች በአድኃሪው መንግሥት ሥር ፈጽሞ ለመኖር በማያስችላቸው አስከፊ ሁኔታ ውስጥ ሲገኙ እንደ አንድ መፍትሔ አድርገው የሚያነሡት ነው፡፡ … ማርክሳውያን የብሔርን የመገንጠል ጥያቄ የሚመለከቱት ከአጠቃላይ የካፒታል ተፅዕኖ፣ ከኢምፔሪያሊዝም መዳከምና ከወዛደራዊው አብዮ መጠናከር አንፃር ነው፡፡ የእነርሱ ዓላማ ምን ጊዜም ጭቆናን በማንኛውም መልኩ ማስቀረትና የሁሉም ብሔሮች ሕዝቦች የተሟላ ነፃነት፣ መብትና እኩልነት እንዲከበር ማድረግ ነው፡፡ የብሔር ጥያቄ በዚህ ዲሞክራሲያዊ ይዘቱ ይህንን ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረገው ትግል አስተዋጽኦ እስካደረገ ድረስ የማርክሳውያንን ድጋፍ ያገኛል፡፡… የመገንጠል መብትን ማወቅና መብቱ በሥራ እንዲተረጎም መታገል የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ማርክሳውያን የመገንጠልን ጉዳይ በመርህ ደረጃ የሚቀበሉት ቢሆንም በተግባር እንዲተረጎም የሚታገሉበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ በሥራ ላይ እንዳይውል የሚታገሉበት ጊዜም ይራል፡፡ የመገንጠል መብት ተግባር ላይ መዋል አስፈላጊነት ከወቅቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የታሪክ ሁኔታዎች አንፃር መገምገም አለበት፡፡ የብሔር ጥያቄ ለብቻው ራሱን እንደቻለ ሳይሆን የአጠቃላዩ የመደብ ትግል አካል እንደሆነ ተደርጎ መታየት አለበት፡፡›› (ገጽ 69)
11) ‹‹መፈክር››
‹‹መፈክር›› (Slogan) ፡- ‹‹የአንድን ትግል ወይም እንቅስቃሴ የቅርብም ሆነ የሩቅ ዓላማና አቅጣጫ ለማመልከት በአጭር ሐረግ ወይም ዐረፍተ ነገር የሚቀርብ መሪ ሐሳብ ነው፡፡ በቃል ሊሰማ፣ ወይንም በመገናኛ መሣሪያዎች ሊገለጽ ይችላል፡፡ መፈክር … ስትራቴጂያዊና ታክቲካዊ ግብ አለው፡፡ የስትራቴጂያዊ መፈክር የረጅም ጊዜን የትግል አቅጣጫ የሚተልምና ለዚህ ዓላማ ሕዝቡን የሚቀሰቅስ የፕሮፓጋንዳ መፈክር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹ኢምፔሪያሊዝም፣ ፊውዳሊዝምና ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም በጭቁን ሕዝቦች ክንድ ይደመሰሳሉ!›› የሚለው መፈክር የስትራቴጂክ መፈክር ነው፡፡ በሌላ በኩል የወቅቱን የትግል ስልት የሚያመለክቱ፣ እንደጊዜው፣ ቦታውና ሁኔታው አመችነት የሚቀርቡ፤ በረጅም የትግል አቅጣጫ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምዱ ወቅታዊና ተግባራዊነት ያላቸው የታክቲክ መፈክሮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፡- ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!›› የሚሉት ወቅታዊነት ላላቸው አብዮታዊ ተግባሮች ሰፊውን ህዝብ የሚያነሳሱ የታክቲክ መፈክሮች ናቸው፡፡›› (ገጽ 73)
12) ‹‹ሙአለ ንዋይ››
‹‹ሙአለ ንዋይ›› (Investment) ፡- ‹‹ትርፍ ለማግኘት ሲባል ካፒታልን ከሞላ ጎደል ረዘም ላለ ጊዜ በኢንዱስትሪ፣ በእርሻ፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽንና በመሳሰሉት የኢኮኖሚ መስኮች የማዋል ክንዋኔ ሙአለ ንዋይ ይባላል፡፡ ሙአለ ንዋይ በሁለት ይከፈላል፡፡ እነሱም የገንዘብ ሙአለ ንዋይና እውን ሙአለ ንዋይ ናቸው፡፡… የገንዘብ ሙአለ ንዋይ የሚባለው ለአረቦኖች፣ ለአክሲዮኖችና ለሌሎች የዋስትና ሰነዶች ግዥ የሚውል ካፒታል ሲሆን፤ እውን ሙአለ ንዋይ የሚባለው ደግሞ ለሕፃዎች፣ ለልዩ ልዩ ማሽኖችና ለማሰሰሉት ቋሚ ንብረቶች ግዥ የሚውለው ካፒታል ነው፡፡ በካፒታሊስት ሀገሮች የንግድና የሙአለ ንዋይ ባንኮች፣ የቁጠባ ባንኮች፣ እንደ መድን ድርጅቶች፣ እንደጡረታ ገንዘብ ማከማቻ ተቋሞች ሞኖፖሊስቶች አያሌ ሙአለ ንዋይን እጃቸው በማስገባት ትርፍ ወደሚያስገኝላቸው እንቅስቃሴ ፈሰስ ለማድረግ የሚጠቀሙባቸው ተጨማሪ አካሎች ናቸው፡፡›› (ገጽ 73)
13) ‹‹የሙያ ማኅበራት››
‹‹የሙያ ማኅበራት›› (Professional Associations) ፡- ‹‹ተመሳሳይ ሙያ ያላቸው ሰዎች የሚሰባሰቡባቸውና ለአባላቱ ጥቅም መከበርና ለሚወክሉትም ሙያ መዳበር የቆሙ የብዙኃን ድርጅቶች የሙያ ማኅበራት ይባላሉ፡፡ የሙያ ማኅበራት ከሌሎች ሕዝባዊ ድርጅቶች የሚለዩት የአባሎቻቸው መመዘኛዎች… በአንድ የተለየ ሙያ የሰለጠኑና የተሰማሩ መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የመምህራን ማኅበር፣ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ የደራስያን ማኅበር፣ የጤና ባለሙያዎች ማኅበር፣ እና የመሳሰሉትን ማኅበራት መጥቀስ ይቻላል፡፡›› (ገጽ 73-74)
14) ‹‹ሚና››
‹‹ሚና›› (Role) ፡- ‹‹ሚና ግለሰብ፣ ቡድን፣ ወይም ድርጅት በኅብረተሰብ ውስጥ በልዩ ልዩ መስክና ደረጃ የሚያከናውነው ወይም የሚጠበቅበት ተግባራዊ ድርሻ ነው፡፡›› (ገጽ 74-75)
15) ‹‹የሴቶች ቀን››
‹‹የሴቶች ቀን›› (Women’s Day / International Working Women’s Day) ፡- ‹‹የዓለም ሠርቶ አደር ሴቶች ለሰላም፣ ለዲሞክራሲና ለሶሻሊዝም በሚያደርጉት ትግል አንድነታቸውን ለማጠናከር በየዓመቱ መጋቢት 28 ወይም 29 (ማርች 8) የሚያከብሩት ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን እንዲከበር ውሳኔ የተላለፈው የታወቀችው ጀርመናዊት የዓለም አቀፍ ኮሚኒስት ንቅናቄ መሪ ክላራ ትዜትኪን በ1910 በኮፕንሃገን ለተደረገው ለሁለተኛው ዓለም አቀፍ ሶሻሊስት የሴቶች ጉባኤ ባሳሰበችው መሰረት ነው፡፡ ዓላማውም የፆታ ጭቆና ከመደብ ጭቆና የማይነጠል በመሆኑ በዓለም ያሉ ሠርቶ አደር ሴቶ ከሚደርስባቸው ጭቆና ለመላቀቅ ወዝአደሩ ከቡርዧዚው ተፅዕኖ፣ ጭቆናና ብዝበዛ ነፃ ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ተካፋ እንዲሆኑ ነው፡፡… ማርች 8 ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በ1911 በጀርመን፣ በኦስትሪያ፣ በዴንማርክና በስዊዘርላንድ ሲሆን በሩሲያም ለመጀመሪያ ጊዜ በ1913 ተከብሯል፡፡ በሀገራችንም ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው  በኢ. አ. 1968 ነበር፡፡›› (ገጽ 138-139)
16) ‹‹ሳንሱር›› 
‹‹ሳንሱር›› (Censorship) ፡- ‹‹አንድ ሐሳብ ወይም የሰዎች የፈጠራ ውጤት ለሕዝብ ከመሠራጨቱ በፊት ተገቢነቱንና ጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ በሕግ በታወቀ አካል የሚደረግ ቁጥጥር ነው፡፡ በሳንሱር አማካይነት የሚካሄደው ቁጥጥር ዓይነተኛ ዓላማ ኅብረተሰቡን ይጎዳሉ የሚባሉ አስተሳሰቦችን መከላከል ነው፡፡ ሳንሱር አንድ መንግሥት የሀገርን አንድነት፣ ነፃነትና ክብር ማስከበር፣ የሕዝቡን አጠቃላይ ክብረ ሕሊና ወዘተ… መጠበቅ፣ እነዚህንና ሌሎችንም ለኅብረተሰቡ ጠንቅ ይሆናሉ የሚላቸውን ነገሮች በማንኛውም መንገድ እንዳይሰራጩ የሚያደርግበት ስልት ነው፡፡›› (ገጽ 136-137)
17) ‹‹በሠላም አብሮ የመኖር መርህ›› 
‹‹በሠላም አብሮ የመኖር መርህ›› (Peaceful Co-existence) ፡- ‹‹የተለያየ ርዕዮተዓለም የሚከተሉ ሀገሮች በመግባባትና በመተባበር በሰላም ለመኖር የሚፈጥሩት ግንኙነት በሰላም አብሮ የመኖር መርህ ይባላል፡፡ …ሰላም ለሶሻሊስት ኅብረተሰብ ግንባታና ለተፋጠነ ዕድገት የተጠናከረ ሶሻሊስታዊ ሥርዓትን ለመፍጠር ያስችላል፡፡ የተጠናከረ የሶሻሊስት ሥርዓት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሶሻሊስት አብዮን ሂደት የማጠናከር ዕድሉ ወይም ችሎታው የበለጠ ይሆናል፡፡›› (ገጽ 126)
18) ‹‹ደብተራዊነት›› 
‹‹ደብተራዊነት›› ለሚለው ቃል የእንግሊዝኛ አቻውን ‹‹Clericalism›› ብሎ በቅንፍ ካስቀመጠ በኋላ እንዲህ የሚል ፍች አስቀምጧል፡- ‹‹በልዩ ልዩ የማኅበራዊ ኑሮ ዘርፎች ላይ የሃይማኖትን ተፅዕኖ ለማጠናከር የሚሞክር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አዝማሚያ ‹ደብተራዊነት› ይባላል፡፡ ዋናው ዓላማ ሠራተኛው መደብ የኮሚኒስትን ርዕዮተዓለም እንደ ትግል መሣሪያው አድርጎ እንዳይዝ መከላከልና የቡርዧውን የበላይነት ማጠናከር ነው፡፡ … ስለሆነም … የቤተክህነት ሰዎች የካፒታሊስትን የብዝበዛ ሥርዓት ተገቢነት ለማሳመን በመሞከር ጎታች የሆነውን ‹ማኅበራዊ ሰላም› ብለው የሚጠሩትን አጉል የመደቦች እርቅ እምነት ይሰብካሉ፡፡ ስለዚህም ለእውነተኛ የሕዝቦች ሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለማኅበራዊ ዕድገትና ለሳይንሳዊ ርዕዮተዓለም መታገል ማለት የደብተራዊነትን አድኃሪ ጠባይ ማጋለጥ ማለት ነው፡፡›› (ገጽ 418)
19) ‹‹ቀያጭነት››
‹‹ቀያጭነት›› የሚለውን ቃል ‹‹Eclecticism›› ብሎ ከገለጸ በኋላ እንዲህ የሚል ፍች ይሰጣል፡- ‹‹‹ቀያጭነት› ሊዛመዱ የማይችሉ ልዩ ልዩ ፍልስፍናዎችን፣ ርዕዮተዓለሞችን፣ አስተሳሰቦችንና መመሪያዎችን መራርጦ ለማስታረቅ የሚሞክር የፍልስፍና አመለካከት ነው፡፡›› በማስከተልም ደግሞ፡- ‹‹ቀያጭነት›› ‹‹የሁኔታዎችን ሰንሰለታዊ ግንኙነት ለማጤን ስለሚያዳግተው በአንድ ታሪካዊ ወቅት ለሚከሰቱ ችግሮች ተገቢ መፍትሔዎችን ለማግኘት ይሳነዋል›› በማለት፡፡ (ገጽ 183)
20) ‹‹ሕሡም›› 
‹‹ሕሡም›› (Ugly)፡- ‹‹ሕሡም የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የከፋ፣ ክፉ፣ መጥፎ፣ ጥፉ ማለት ነው፡፡››… ‹‹የውበት ተቃራኒ የሆነና የሰውን የጥላቻ፣ የእምቢታ፣ ወዘተ… ስሜቶችን የሚገልጽ የሥነ ውበት ፈርጅ ነው፡፡ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ሕሡም የሚያመለክተው የሰው ነፃ እንቅስቃሴ መቀጨቱን ወይም በሚያጣምሙና በሚያዛቡ ማኅበራዊ ኃይሎች ሥር መውደቁን ነው፡፡ በዚህ ፍችው መሠረት ሕሡም የመደብ ትግል ስሜታዊ ክስተት ነው፡፡ በአንፃሩም በሥነ ውበት ውስጥ የሕሡም መታየትና መገለጽ በሰዎች ዘንድ የውበትን ፍላጎት ይፈጥራል፤ ነፃ ለመውጣት የሚያደርጉትንም ትግል ያጠናክራል፡፡›› (ገጽ 18)
21) ‹‹ሕዝባዊ አመፅ››
‹‹ሕዝባዊ አመፅ›› (Insurrection)፡- ‹‹ሰፊውን ሕዝብ ከበዝባዥ መደቦች ለማላቀቅና ሙሉ መብቱን ለማጎናፀፍ በአንድ ወቅት በቁጣ የሚነሣ ሕዝባዊ  የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ሕዝባዊ አመፅ በጠንካራ አብዮታዊ ድርጅት ከተመራ ፍትህና እኩልነት የሰፈነበት ኅብረተሰብ ለመመሥረት ወደሚያስችል ግብ የሚያመራ ይሆናል፡፡›› (ገጽ 20)
22) ‹‹ሕዝባዊ ሠራዊት›› 
‹‹ሕዝባዊ ሠራዊት›› ለሚለውም አቻ የእንግሊዝኛ ቃሉን ‹‹People’s militia›› ብሎ ካስቀመጠልን በኋላ፡- ‹‹ሕዝባዊ ሠራዊት ከጭቁን መደቦችና የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ ፤ ወታደራዊና ርዕዮተዓለማዊ ትምህርት የተሰጠው ፤ የሀገር ፀጥታ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሲደፈርስ ወታደራዊ ተግባር የሚያከናውን ፤ በሰላም ጊዜ በመደበኛ ሥራው ላይ የሚገኝ መደበኛ ሠራዊት ያልሆነ የታጠቀ ሕዝባዊ ኃይል ነው፡፡ … ሕዝባዊ ሠራዊት በሳይንሳዊ ርዕዮተዓለም የታጠቀ፤ ለማንና ለምን እንደሚዋጋ በሚገባ የተገነዘበ በመሆኑ በድርጅታዊ አቋሙና በውጊያ ብቃቱ ተጠናክሮ የሀገርን አንድነት ፤ ነፃነትና የሰፊውን ሕዝብ አብዮት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያለው ታላቅ ኃይል ነው፡፡›› ይላል፡፡ እናም ‹‹አብዮት ጠባቂ›› ተብሎ በአብዮቱ ዘመን የተሾመው ሠራዊት ይኸው ‹‹ዓይነተኛ ተግባሩ የሰፊውን ሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት መጠበቅና መንከባከብ ነው›› የተባለለት ጠባቂ መልዓክ ነው ማለት ነው እንግዲህ፡፡ (ገጽ 18)
23) ‹‹የኢንዱስትሪ ተጠባባቂ ሠራዊት››
‹‹የኢንዱስትሪ ተጠባባቂ ሠራዊት›› (Industrial Reserve Army)፡- ‹‹የሚለው ቃል የሚያመለክተው በአንድ ሃገር ውስጥ የሚገኙ ‹‹በምርት ተግባር ውስጥ ሊሳተፍ ያልቻለ ሥራ የሰው ኃይልን›› ወይም ሥራ አጥ ዜጎችን መሆኑን ይጠቅስና፤ እንዲህ ይላል፡- ‹‹‹የኢንዱስትሪ ተጠባባቂ ሠራዊት› የካፒታሊስት ክምችት የማይቀር ውጤት የመሆኑን ያህል ለካፒታሊስት ስልተ-ምርት ህልውና አስፈላጊ ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም ‹‹የኢንዱስትሪ ተጠባባቂ ሠራዊት›› መኖር ቡርዧዚው በምርት ተግባር ላይ የተሰማራው ወዝአደር ለምንዳ መሻሻልና ለመሳሰሉት ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች የሚያደርገውን ትግል ለማዳከም እንገለገልበት ስለሚያስችለው ነው፡፡ ይህም የምንዳን (የሠራተኛ ደመወዝን) ደረጃ ዝቅ በማድረግ ቡርዧዚው የሚያገኘው ትርፍ እያደገ እንዲሄድና የተስፋፋ ክምችትም እንዲኖረው አመቺ ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡›› በማለት ያስቀምጣል፡፡ (ገጽ 323)
24) ‹‹ሕዝባዊ ውሳኔ (ውሳኔ ሕዝብ)››
‹‹ሕዝባዊ ውሳኔ (ውሳኔ ሕዝብ)›› ይልና በቅንፍ ደግሞ ‹‹Referendum›› ይላል፡፡ እንዲህም የሚል ትርጉማዊ ማብራሪያን ያስቀምጣል፡- ‹‹በአንድ ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ሕገ መንግሥታዊ ፤ ሕጋዊና ሌሎችም ላቅ ያሉ ብሔራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ፖሊሲ ወይም አቋም በሕዝብ ድምፅ የመጨረሻ ውሳኔ የሚያገኝበት አሠራር ነው፡፡›› የሚል፡፡ (ገጽ 21)
25) ‹‹ሕዝባዊ ዲሞክራሲ››
‹‹ሕዝባዊ ዲሞክራሲ›› ወደሚል ቃል ይሸጋገራል፡፡ የእንግሊዝኛ አቻውንም እንዲህ ብሎ ያስቀምጣል፡- ‹‹People’s Democracy››፡- ትርጓሜ ወ ትንታኔውን ደግሞ እንዲህ በማለት አስፍሮታል፡- ‹‹ሕዝባዊ ዲሞክራሲ ማለት ኢምፔሪያሊዝም በተዳከመበትና የኃይል ሚዛኑ ወደ ሶሻሊዝም ባጋደለበት ወቅት የሶሻሊስት አብዮት የተለየ ዕድገት የተንፀባረቀበትና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በብዙ የምሥራቅ አውሮፓና በአንዳንድ የእስያ ሀገሮች የተከሰተ አዲስ የወዝአደሩ የበላይ ገዥነት ቅርፅ ነው፡፡ ሕዝባዊ ዲሞክራሲ የተከሰተው በነዚህ ሀገሮች በተካሄዱት ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮቶች በመሆኑ የየሀገሮቹን የተለዩ ታሪካዊና ብሔራዊ ሁኔታዎች ያንፀባርቃል፡፡ . . . በእነዚህ ሀገሮች … በጨቋኝ ኃይሎችና በተጨቆኑ መደቦች መካከል የነበሩት ቅራኔዎች የተፈቱ ሲሆን ትግሉም የተመራው በወዝአደሩ መደብና በግንባር ቀደም ድርጅቱ በኮሚኒስት ፓርቲው ነው፡፡›› በማለት ነው የሚተነትነው፡፡  (ገጽ 21)
26) ‹‹አብዮት››
‹‹አብዮት›› (Revolution) ፡- ‹‹አበየ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም አሻፈረኝ አለ፤ እምቢ አለ ማለት ነው፡፡›› ይልና የሚከተለውን ፍች ይሰጣል፡- ‹‹በአንድ ነገር፤ ክስተት ወይም ሂደት ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች ተካረው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሚፈጠር መሠረታዊ ለውጥ፤ አዲስ ከፍተኛና የተሻለ ነገር፤ ክስተትና ሂደት ወይም አስተሳሰብና ዕውቀት የሚከሰትበት የዓይነት ለውጥ ‹አብዮት› ይባላል፡፡ … ስለሆነም በአንድ ኅብረተሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ወዘተ… ዘርፎች ውስጥ የሚታየው መሠረታዊ ለውጥ የኅብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶችና የመደቦችን ዓይነት የሚለውጥ በመሆኑ ማኅበራዊ አብዮት ይባላል፡፡›› (ገጽ 289)
27) ‹‹አብዮታዊ ጦር››
‹‹አብዮታዊ ጦር›› (Revolutionary Army) ፡- የሚለውን ደግሞ እንዲህ ይፈታዋል፡- ‹‹‹አብዮታዊ ጦር› በማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተምህሮ የታነፀ፤ ለወዝአደሩ ዓላማና ተልዕኮ ፍፁም ተገዥ የሆነ ከሠርቶ አደሩ የተውጣጣ ሠራዊት ነው፡፡… ይህ ሠራዊት ከብዝበዛና ከጭቆና ነፃ የሆነውን ሶሻሊስት ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችለውን ዲሞክራሲና ሰላም የሰፈነበትን ሁኔታ ለመፍጠር ማናቸውንም መሥዋዕት ለመክፈል የቆመ ነው፡፡›› (ገጽ 289)
28) ‹‹ቀይ ጦር›› 
‹‹ቀይ ጦር›› ለሚለው ቃል (Red Army) ፡- የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ያስቀምጥና እንዲህ ሲል ያብራራዋል፡- ‹‹ቀይ ጦር›› በመደብ ትግል ውስጥ ተፈትኖ ያለፈ፤ በወዛደሩ ርዕዮተዓለም የታጠቀ፤ ከሠራተኛው፣ ከገበሬውና ከተቀሩትም ሠርቶ አደሮች ክፍሎች የተውጣጣ፤ በንቃቱና በውጊያ ችሎታውም ሆነ በሞራሉ ወደር የሌለው፤ ለጽኑ ሕዝባዊ ዓላማ የቆመ ጥራትና ብቃት ያለው የሶሻሊስት ጦር ኃይል ነው፡፡… ቀዩ ጦር ለመጀመሪያ ጊዜ የራሱን መንግሥት በትግሉ የመሠረተውን የሩሲያን የሠራተኛና የገበሬ መደቦች ጥቅም የሚጠብቅ ሕዝባዊ ኃይል ሆኖ በኮሚኒስት ፓርቲው አመራር በሶቭዬት መንግሥት ተቋቋመ፡፡ ቀዩ ጦር አዲሱን የሠራተኛውንና የገበሬውን መንግሥት ለመገልበጥ ያሴሩና ይፈታተኑ የነበሩትን የውስጥ ፀረ-አብዮት ኃይሎችን የደመሰሰና እንዲሁም የዚህን መንግሥት መቋቋምና መጠናከር አጥብቀው ይፃረሩ የነበሩትን የኢምፔሪያሊስት ጣልቃ ገብ ወራሪ ኃይሎች በመመከት የአብዮታዊት እናት ሀገሩን አንድነትና ነፃነት የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን የተወጣ አብዮታዊ ኃይል ነበር፡፡..››፡፡ (ገጽ 183)
29) ‹‹የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ››
‹‹የፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ›› (Party Central Committee) ፡- የሚለውን ቃል ፍች ደግሞ እንዲህ ያስቀምጠዋል፡- ‹‹የፓርቲ ጉባኤ የሚመርጠው አካል ከጉባኤው ቀጥሎ የሚገኝ፤ በጉባኤዎች መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ የፓርቲውን ሥራ የሚያካሂድ ከፍተኛው የአመራር አካል ነው፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴ ኃላፊነቱና ተጠሪነቱ ለፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡… ማዕከላዊ ኮሚቴው የፓርቲውን አንድነት የማጠናከር ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡… ስለዚህ በማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚመረጡት ግለሰቦች በርዕዮተዓለም ብስለታቸው የላቁና በትግል ልምድ የደረጁ ብቻ ሳይሆኑ በሚመደቡበት የሥራ ዘርፍም በቂ የሙያ ችሎታ ያላቸው ቆራጥ ታጋዮች መሆን ይገባቸዋል፡፡›› (ገጽ 502)
30) ‹‹ሽብር››
‹‹ሽብር›› (Terror) ፡- ‹‹ሽብር በመደብ ትግል ውስጥ በተፃራሪ መደቦች መካከል የሚደረገው ሰላማዊ የትግል ስልት ሊሠራ ከማይችልበት ደረጃ ሲደርስ አንዱ ሌላውን ለማንበርከክና የበላይነቱን ለማረጋገጥ የሚያካሂደው የትጥቅ ትግል ነው፡፡›› (ገጽ 175)
31) ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ›› 
‹‹ሰላማዊ ሰልፍ›› (Demonstration) ፡- ‹‹‹ሰላማዊ ሰልፍ› ሰዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ በአደባባይና በይፋ የሚደረግ ትዕይንተ ሕዝብ ነው፡፡ ሰዎች ደስታቸውንም ሆነ ቅሬታቸውን ለማሳወቅ በጉልህ የተጻፉ መፈክሮችን በመያዝና በቃልም በማሰማት በርካታ ሰዎች በሚገኙባቸው አደባባዮችና ዋና ዋና መንገዶች እየተዘዋወሩ ድጋፍ የሚሰጡበት ወይም ተቃውሞ የሚያሰሙበት ስልት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በቅድመ አብዮትና በአብዮቱ የመጀመሪያ ወቅት የኢትዮጵያ ተማሪዎችና ሌለችም የኅብረተሰብ ክፍለች አድኃሪውን መንግሥትና ሥርዓት በመቃወም ያደረጓቸው ሰላማዊ ሰልፎች የተቃውሞ ሲሆኑ፤ መሬትን ለሰፊው የገጠር ሕዝብ ያደረገውንና የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጆችን በመደገፍ በየቦታው የተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ሰፊው ሕዝብ ከልብ የተሰማውን ደስታ የገለጸባቸውና ሙሉ ድጋፉን ለአብዮቱ የሰጠባቸው ነበሩ፡፡›› (ገጽ 125)
32) ‹‹ዋጋ ንረት›› 
‹‹ዋጋ ንረት›› (Inflation) ፡- የሚለውን ቃል ደግሞ እንዲህ በማለት ነው የሚተነትነው፡- ‹‹የተመረቱና በገበያ ላይ የወጡ ሸቀጦችን ለማዘዋወር አስፈላጊ ከሆነው በላይ የወረቀት ገንዘብም ሆነ የዱቤ ገንዘብ መጠን በመጨመሩ ምክንያት የሚከተለው አጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ሲፈጠር የወረቀት ገንዘብ የመግዛት ኃይል ይቀንሳል፡፡›› (ገጽ 407)
33) ‹‹የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር››
‹‹የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር›› (Consumers Co-operatives) :- ‹‹ ‹የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበር›‹ ወይም ‹ሸማቾች› ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን ምርቶች ከብዝበዛ ነፃ በሆነ መንገድ ለማግኘት እንዲችሉና እንዲሁም ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንደየሁኔታው እያመረቱ ለአባሎችና እንዲሁም በአጠቃላይ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ በፈቃደኝነት የሚመሠርቱት ድርጅት ነው፡፡ ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት አጀማመር መንሥኤ ወዝአደሩ ቡርዧዚው ከሚያደርስበት ፤ አትራፊ ነጋዴዎችም ከሚፈጽሙት ብዝበዛ ለመዳን ያደረገው ጥረት ሲሆን ለነሮ የሚያስፈልጉትን ሸቀጣ ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እንዲችል ገንዘብ በማዋጣት የሚመሠርታቸው የጋራ ዕድገት መደጋገፊያ ማህበራት ናቸው፡፡›› (ገጽ 171)
ዝርዝሩ — እነሆ ተፈጸመ — በ‹ሸማቾች› ! ! ! ! !
ነገር ግን እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ለማሣየት እንደሞከርኩት — ከደርግ ከነሁለመናቸው ተወስደው — በኢህአዲጋውያን አንደበት ተከትተው — በሰፊው ጥቅም ላይ የዋሉ የደርግ ቃላት — እጅግ ብዙ፣ ብዙ፣ ናቸው፡፡ መዓት፡፡ ወይም የትየለሌ፡፡
‹‹ነገድ፣ ነፃ ውድድር፣ ንዑስ ከበርቴ፣ አሻንጉሊት፣ አሻጥር፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ ሁኔታ፣ ብሔራዊ የአርነት ንቅናቄ፣ ብሔራዊ ሶሻሊዝም፣ ብሔረተኛነት፣ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ አብዮት፣ ብሔር፣ የብሔር ትምክህተኝነት፣ የብሔር ጥያቄ፣ አርበኝነት፣ ኮርፖሬሽን፣ ሽብር፣ ካድሬ፣ ኪነጥበብ፣ ኮሚሽን፣ ኅቡዕ፣ ፌዴሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን፣ ውዥንብር፣ ዘረኝነት፣ ዝቅጠት፣ ደምሳሽነት፣ ዲሲፕሊን፣ ግንባር፣ ጦረኝነት፣ ፅናት አልበኝነት፣ ኢንተርፕራይዝ፣ እሴት፣ ሕዝበኝነት፣ እጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ (ኒኦ-ኮሎኒያሊዝም)፣ ኢሠብዓዊ ጭፍጨፋ (ጀኖሳይድ)፣ አውዳሚነት፣ አክስዮን፣ የአክስዮን ገበያ፣ አንፃራዊ የኑሮ ሁኔታ ቁርቁዝና፣ አንጃ፣ ጽንፋዊነት፣ ፈቃዳዊነት፣ አሃዳዊነት፣ እውነት፣ ተናሥኦት (አፕራይዚንግ)፣ ዋርድዮች (ጋርድስ)፣ አስመሳይ አብዮተኛ፣ አረብ ሶሻሊዝም፣ ቋንቋ፣ ባህላዊ ብሔራዊ ራስገዝነት፣ ብሔረሰብ፣ ማህበራዊ ዲሞክራሲ፣ ሽምቅ ውጊያ፣ ሐሳዊ መሲህ፣ ሕዝባዊ ካፒታሊዝም፣ የኅሩያን ምስፍና (አሪስቶክራሲ)፣ ሸቀጥ፣ የሴቶች ጥያቄ፣ ቅስቀሳ፣ ወዘተ ወዘተ ወዘተ……›› !!
አሁን ጠዋትና ማታ ከኢህአዴጋውያን አንደበት የምንሰማቸው መዓት ቃላት… እንደጉድ ይገኛሉ.. በዚያ የደርግ መዝገበ ቃላት ውስጥ — ያውም በዓይነት በዓይነቱ ተሰድረው ነዋ!!! እና እኮ በቃ… ያኔም አሁንም ግልጋሎት ላይ የዋሉትን ነገሮችና ቃላት ብዛት ላስተዋለ… ‹‹ምን አንድ አረጋቸው?›› ብቻ ሳይሆን… ‹‹ኧረ የማንኛቸውን ከማንኛቸው እንዴት አርገን እንለያቸው?›› የሚል ጥያቄ ሁሉ ይመላለስበታል፡፡ አያድርስ ነው፡፡ ግራ የገባን – የሁለት ዘመን ግራ-ዘመም ፍጡሮች – እኛ ኢትዮጵያውያን!!!!!
ብቻ – ወደግራም ዘመመች… ወደቀኝ – እምዬ ኢትዮጵያችን – ቃላቷ ይቀያየር፣ ይወራረስ እንጂ – እርሷ እንደሁ ያው ነች፡፡ ልጆቿ ቃላት እየፈጠሩ የሚናከሱባት፣ ጡቶቿን ለሁላችን የዘረጋች፣ አንዲት ምስኪን እናት ነች – እምዬ ኢትዮጵያ፡፡  አንድዬ አምላክ – እናት ሀገራችንን – ከነልጆቿ፣ ከነነፃነቷ፣ ከነአንድነቷ፣ እና ከነሕልሟ ጭምር – ለዘለዓለም ይባርክ፣ ይጠብቅ፣ ያኑርልን ማለት ነው እንግዲህ!!!
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ መልካሙን ሁሉ ያምጣልን፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic