>

ኦ ባህርዳር (አንተነህ መርዕድ - ካናዳ)

ኦ ባህርዳር

አንተነህ መርዕድ ካናዳ
ግራና ቀኝ በዘንባባ መሃሉን በአበባ ባጌጠ አስፋልትሽ በብር ካምሳ እከደከ ጫማ በእግሬ አንዳንዴም በብስኪሌት ቀንና ምሸት የተመላለስሁብሽ፣ አሁንም ሩቅ ሆኜ በህልሜ እምባዝንብሽ የልጅነቴ መስተዋት፤

የመንግስቱ ኃይለማርያም፣ የመላኩ ተፈራ፣ የእሸቱ ዓለሙ ….. ገዳይ መንፈስ ሰቅዞሽ ለእድገትሽ ለመሻሻልሽ ያለሙ ብሩህ ልጆችሽ ተገድለው መንገድ ዳር የተጣሉብሽ በዝምታ ከል ለባሽ እናት፤
ትናንት በወያኔ አልሞተኳሾች ከአምሳ በላይ እምቡጥ ልጆችሽ በአንድ ቀን አስፋልቱን በደም ያጠቡልሽ ምስኪን፤
ከየክልሉ በአማራነታቸው ብቻ ተሳድደው ከጥይት፣ ከጦርና ከቀስት የተረፉ ገበሬዎች የሚንከላወሱብሽ፤
ዛሬ የትናንት ፅልመትና መከራሽን ዳርቻ ብለሽ እንድትጥይው የነገ ተስፋውን በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ሸፍኖ አዲሱ ትውልድ የተመመብሽ ባህርዳር፤
በእስታድየምሽ ህዝብሽ ሞልቶ በቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” በፋሲል ደሞዝ “አረሱት አሉ” ዜማ፤ የኢትዮጵያ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ ተምሳሌት የሆነው ሶስት ሺህ ሜትር የሚረዝመው አንድ ባንዲራ እንዲሁም በእጅ በተያዙ ብዙ ሺህና ራስ ላይ በተጠመጠሙ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት አሽብርቆ ለዘመናት ትውልድ የተሰዋለትን ተስፋ ሲያዜም ሳይ በስደት ካለሁበት ሁኜ በትኩስ እንባ ጉንጬን አጠብሁት። እንባዬ የደስታም፣ የተስፋም የመከራው ሁሉ ትዝታም ነው።
ከለውጡ ጎራ ጎልተው የወጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮነን እንዲሁም የክልሉ ፕሬዝደንት ገዱ አንዳርጋቸው የትናንቱን ስሕተት በፀፀት አስታውሰው በአዲስ ተስፋ ለለውጥ ወደ ፊት እንሂድ ብለው ጥሪ አቅርበዋል።
ጥሪው ከልብ የመነጨ ወይንስ የለመድነው የኢህአዴጎች “እየተሳሳትንም እኛው እንምራችሁ” የገዢዎች ዜማ?
አዲስ ወይን በአሮጌ አቁማዳ እንዲሉ አዲሱን አስተሳሰብ በአሮጌዎቹ መሪዎች ለማስኬድ የአጅቡን ጥሪ ወይንስ አዲሱን ወይን በአዲሱ አቁማዳ እንዲሉ ከልብ የመነጨ ጥሪ?
ለህዝብ በመቆሟ ብቻ ለአስራ አንድ ዓመታት በግፍ ታስራ ብዙ ጭካኔ የተፈፀመባት እማዋይሽ ዓለሙ ሊሰብሩት ያለሙት መንፈሷ ይበልጥ የደደረ መሆኑን የድጋፍ ሰልፉ መደምደምያ ማዕዘን የሆነ ጥያቄ “ጥሪያችሁ ሁሉን ያካተተ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ወይንስ በአሮጌው በተቀደደው ቦይ እንድንፈስላችሁ?” ስትል እስታድየሙን የድጋፍ ማዕበል አናወጠው። በጥቂት መቶ ሜትሮች በፀጥታ የተኛውና በእምቦጭ የታነቀው ጣናንም ሳያነቃንቀው አልቀረም።
ይህ ትውልድ በብዙ መስዋዕት የተገኘን ድል ለማስጠበቅና ወደፊትም ለመራመድ ተደራጅቶ ዋስትና የሚሆኑ ተቋማትን መገንባት አለበት። ለ44 ዓመታት በደርግና በወያኔ ካድሬዎች መገዛቱ እንዲያከትም ህዝቡ ራሱን በራሱ ሊያስተዳድር ተፈጥሮአዊ መብቱ ነው። ያለዚያ ለለውጥ የፈሰሰው ደም ከንቱ፣ በግለት የተነሳውም ተስፋ አድብተው በሚጠባበቁ አውሬዎች ይነጠቃል። ትግሉ ላይጨረስ አልተጀመረም። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ኃይል በጋራና ሁሉን ባካተተ ተሳትፎ ማገዝ ካልተቻለ ጭፍን ድጋፍ የትም አያደርስም። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ከአድፋጭነቱ ተላቅቆ በቁጣ የቀጣቸው ጠላቶቹ ዳግም አንሰራርው ቀንበራቸውን እንዳይጭኑበት ትግሉን ዳር ማድረስ ያስፈልገዋል።

 

Filed in: Amharic