>

ይክበር በማለዳ፣ ይክበር በቀትር፣ ይክበር በማታ - የኢትዮጵያ ጌታ ...! (አሰፋ ሀይሉ)

ይክበር በማለዳ፣ ይክበር በቀትር፣
ይክበር በማታ የኢትዮጵያ ጌታ . . . !
አሰፋ ሀይሉ
የኢትዮጵያው ንጉሥ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ — በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሣኔ መሠረት — ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር — በፌዴሬሽን እንድትዋሀድ — የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት — በጠቅላላ ጉባዔ ውሣኔ ቁጥር 390-ኤ (UN Resolution 390-A(V)) ያሣለፈውን ውሣኔ ተከትሎ
 — በኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት መንግሥት የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተደነገገውን ኢትዮጵያንና ኤርትራን በፌዴሬሽን የሚያዋህደውን ፌዴሽን አዋጅ ያፀደቁባት ያች የዛሬ 65 ዓመቷ የእንቁጣጣሽ ዕለት ማለትም መስከረም 1 ቀን 1945 ዓመተ ምህረት  ወይም በጎርጎሮሣውያን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 11 ቀን 1952 ዓ.ም. — ይህችን ትመስል ነበር፡፡
ግርማዊ ጃንሆይን እና እቴጌ መነንን — እንዲግ ባለ የጨዋ ደንብ — ጎንበስ ብለው እጅ ሲነሱ የምናያቸው — የወቅቱ የኤርትራ ፌዴሬሽን ዋና አስተዳዳሪ (Chief Executive of Eritrea) — አቶ ተድላ ባይሩ — ነበሩ፡፡ ይህ ከተከናወነ ከ2 ቀናት በኋላ ደግሞ — በብዙ መስኮች ሲታይ — ለወቅቱ የኤርትራ ነዋሪዎች — ከኢትዮጵያ ነዋሪዎች የተሻለ ነፃነትን የሚያጎናጽፍና ‹‹በተራማጅነቱ›› አድናቆትን ያተረፈ — የኤርትራ ህገ-መንግሥትም — በንጉሠ ነገሥቱ ተ—ቀባይነት አግኝቶ ፀደቀ፡፡
ይህን ተከትሎ — በ3 ዓመታት ውስጥ ደግሞ — ንጉሠነገሥቱም — የኤርትራ ነዋሪዎች ቀድሞ የነበራቸውን ህገመንግሥታዊ መብት እንዳይቀነስባቸው በማሰብ — እግረመንገዱን ለመላው ኢትዮጵያውያን በረከቱ የተረፈውን — የተሻሻለውን የኢትዮጵያ ህገመንግሥት — በዓለማቀፍ አዋቂዎች አስጠንተው — በምክር ቤቱና በራሳቸው አስጸድቀው — በመላ ሀገሪቱ — በሥራ ላይ እንዲውል አደረጉ፡፡
በእርግጥ በወቅቱ — በመብት ደረጃ ከታየ — በብዙዎች አስተያየት — በኤርትራ ነዋሪዎች ምክንያት — ለኢትዮጵያ ነዋሪዎች ውህደቱ የቸራቸው ትልቁ ትሩፋት ቢኖር — ኤርትራውያን — ከምድሪቱ እንደሚነቀሉ በተረዱት የእንግሊዝና ኢጣልያ አስተዳደሮች አማካይነት — ቀድመው በተሰጧቸው ይበልጥ ነፃነትን የሚሰጡ ግለሰባዊና ሰብዓዊ መብቶችን — የኢትዮጵያውያ ግዛት ነዋሪዎችም — በኤርትራ ግዛት ነዋሪዎች ሰበብ የተነሣ — እና የንጉሡም መልካም ፈቃድ ተጨምሮበት — ይህን ሰፊ መብት እንዲጋሩት መፈቀዱ ነበረ፡፡
ነገር ግን — ይህ የኢትዮ-ኤርትራ ፌዴሬሽን — ለአሥር ዓመት በመካከላቸው ፀንቶ ከቆየ በኋላ — የወቅቱ የኤርትራ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት — ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ሣይሆን — ሙሉ በሙሉ መዋሃድ አለባት በማለት — በሕገመንግሥታዊ ሥልጣኑ ተጠቅሞ — ራሱን በራሱ በሙሉ ድምፅ የኤርትራን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የራስ አስተዳደር መንግሥት በመበተን — ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሃዱን አስታወቀ፡፡
ያን ተከትሎም — ግርማዊ ጃንሆይ — በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሣኔ ተግባራዊ የተደረገውን የኤርትራን ፌዴሬሽን ውህደት በማፍረስ — መላው የኢትዮጵያ ወሰኖች የሚገኙ ዜጎች ሁሉ — በአንድ በሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ሕዝቡን በሚያስተዳድር — አሃዳዊ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሥር ተጠልለው — እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ እንደሚተዳደሩ የሚደነግገውን አዋጅ አፀደቁ፡፡
እና ከዚያ በኋላ ለተከተሉት 50 ዓመታት ሁሉ — እስካሁንም — ጦሱ ሣይበርድ የቆየው —የሁለቱ ሀበሻ ወንድማማች ሕዝቦች — በተቃራኒ ጎራዎች አሠላፊነት ተመዳድበው የመጀሩት የብዙ ዓመታት — የእርስ-በርስ አውዳሚ ፍትጊያ ተጀመረ፡፡ ተጀመረ ስል — አሁን — ከሰሞኑ — በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር — በዶ/ር አብይ አህመድ — ዳግም ጥረት አማካይነት — የበርካታ ዓመታቱ የሁለትዮሽ ሀገራዊ ፍትጊያ — ወደ ሁለትዮሽ ሀገራዊ ፈንጠዝያ ድንገት እስከተለወጠበት — እስከ ሰሞኑ — እስከ ትናንት ወዲያ ድረስ — ማለቴ እንደሆነ — ይያዝልኝ፡፡
 ‹‹Tedla Bairu bust by Afework Tekle
ከዚህ ዘመን በኋላ ደግሞ — ለሁለቱ ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን የሀበሻ ህዝቦች — እና ለሁለቱ በሥልጣናቸው ለመቆየት ሲሉ ‹‹አሁኑኑ ተዋሃዱ!›› እንኳ ቢባሉ… ‹‹ማን ለማን ሥልጣኑን ሊለቅቅ ነው?!›› ብለው – ሁላችንም በያለንበት እንርጋ ከማለት — ወደኋላ የማይሉ መስለው የቆዩትን የሁለቱን ሀገራት ‹ተፎካካሪ› መንግሥታትና ባለሥልጣናት ሁሉ — አንዱ ለአንዱ የማይሰግድበትን — አንዱም የአንዱን ምሥል እንደ ጣዖት የማይቀርጽበትን — በእኩልነት፣ በመፈቃቀድ፣ በጋራ ፍላጎት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተውን ወዳጅነት እንዲያመጣላቸው — የብዙዎች ምኞት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡
በተለይ በተለይ — ላለፉት 50 ዓመታት — እኛ በራሳችን — በሁለቱ የሀበሻ ሕዝቦች መካከል እና አማካይነት የተፈጸሙትም ሆኑ — ባህር ተሻግረው በመጡ ቅኝ ገዥዎችና — ፍርሃት ባደረባቸው እኩይ ኢምፔሪያሊስቶች አማካይነት በመካከላችን የተተከሉና በላያችን የተዘሩ የተንኮል ሥሮችና ልዩነቶች — የቱንም ያህል ዳግም ሁለቱን ህዝቦች ላያቆራኙ ሥር ሠድደው የነገሡ ይመስሉ ነበር፡፡
ሆኖም — ቢመስሉም — ሁለቱ ኩሩ የሀበሻ ሕዝቦች — ኢትዮጵያውያንና ኤትርራውያን ግን — በፈጠሩት ወደር የሌለው የእርስ በእርስ ማግኔታዊ መሣሣብ — እና የአንድነት መንፈስ፣ እና ድንበር ያልገደበው ግፊት የተነሣ — እነሆ — ማናቸውንም ዓይነት ሰው-ሠራሽ አጥር — በፍቅር ኃይል አስከንድቶ — የሁለቱን ሕዝቦች ወደ ጋራ ብልጽግና የሚያሸጋግር — እና ደግሞ ይኸው በሰው ልብ ውስጥ እስከነገሠ ድረስ — ከቶውኑም — ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል — ሊገድበው የማይችል — በአፍሪካ ምድር — በተለይም በአፍሪካ ቀንድ — ተስተናግዶ የማያውቅ — ታላቅ የፍቅር ማዕበል — የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ሁሉ — እያጥለቀለቀ እንደሆነ — ገና ሀገር-ምድሩን ሁሉ እንደሚያጥለቀልቅ — የብዙዎች እምነት ነው፡፡
እኛም እናምናለን፡፡ እና በቻልነው ድምፅ ጮክ ብለን — ማለዳ፣ ማለዳ፣ እናስተጋባለን፡፡ 
ድሮም፡፡ አሁንም፡፡ የቱንም ያህል የተለያየን ብንመስል፡፡ እኛ ግን፡፡ ተጨካከንን እንጂ፡፡ አልተለያየንም፡፡ መለያየትም አንችልም፡፡ ምክንያቱም፡፡ እኛ፡፡ የጋራ ታሪክ፡፡ የጋራ ማንነት፡፡ የጋራ ጀግንነት፡፡ የጋራ እልህ፡፡ የጋራ ጠላት፡፡ የጋራ ህልም፡፡ የጋራ ጥበብ፡፡ የጋራ ሲኒ፡፡ የጋራ ሹሩባ፡፡ የጋራ ስነልቦና፡፡ የጋራ መልክ፡፡ ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ እነዚህን የሚመልስ፡፡ አዲስ፡፡ ኃያል፡፡ የፍቅር ዘመን ያምጣልን፡፡ የፍቅርን ፀሐይ ለሁላችንም ያውጣልን፡፡ በሁሉም አቅጣጫ የምንጠራው አምላካችን፡፡ በቃችሁ ይበለን፡፡
እዚህ ላይ፡- የአምባሣደር ዘውዴ ረታን ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› እና የተባበሩት መንግሥታትን ‹‹የኢትዮ-ኤርትራ የፌዴሬሽን ውህደት ውሳኔ›› በአቅራቢያቸው ከሚገኝ መጻሕፍት መሸጫና ከትሩፋታችን ጉግል ላይ በቀላሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል – ጊዜ ሰጥተው እንዲያነቡት ስንል — መላውን አንባቢያን — በራሳቸው ወጪ ጋበዝን፡፡ መልካም ንባብ፡፡ ሁሩ ወመሃሩ፡፡ አበቃሁ፡፡
አምላክ — ሀበሾችን ሁሉ — ከትውልድ እስከ ትውልድ — አብዝቶ፣ አብዝቶ፣ አብዝቶ — ይባርክ፡፡ ይክበር በማለዳ፣ ይክበር በቀትር፣ ይክበር በማታ — የኢትዮጵያ ጌታ — ፈጣሪ አምላክ! እምዬ — ለዘለዓለም — ትኑር!
ፎቶግራፎቹ (እጅግ ከከበረ ልባዊ ምሥጋና ጋር)፡-
1) ‹‹Ato Tedla Bairu, chief executive of Eritrea, bowing to HIM Haile Selassie on 11 September 1952 (1945 E.C) at the Imperial Palace in Addis Ababa after HIM ratified the Federal Act federating Eritrea – save››
2) ‹‹Tedla Bairu bust by Afework Tekle
Filed in: Amharic