>

ፖሊስ ወይስ ፖሊሲ! ( አብይ ህዝብና ገንዘብ ! ) - ደረጄ ደስታ

ፖሊስ ወይስ ፖሊሲ! ( አብይ ህዝብና ገንዘብ ! )
ደረጄ ደስታ
እውነት ነው በዛሬው ገበያ የአብይ ሀብት ህዝብ ነው። ህዝብ ደግሞ ገንዘብ የለውም። ህዝብን ወደ ገንዘብ ካልቀየሩት እሳቸው ወደ ገንዘብ ወይም በገንዘብ መቀየራቸው አይቀርም። ያኔ ህዝብ ደህና ሰንብች!
አንዳንድ ሰዎች አብይ ፈጠኑ እያሉ ነው። ወይ መፍጠን! እንዲያውም ዛሬ ደግሞ ስናስበው እጅግ በጣም ተንቀርፍፈዋል ብንልስ። ብዙ ነገር ማድረግ እሚችሉበት ጊዜ አሁን ነው። ለመመለክ ጥቂት የቀራቸው እኚህ ሰው ታላላቅ የፖሊሲ ውሳኔዎች ማሳለፍ እሚችሉት ዛሬ ነው። ብዙ አምባገነን መሪዎች ሳይቀር እማይታደሉትን የመታመን የመደመጥና “ብቻ እንደፈለግክ አድርገህ ምራን!” የሚል ፈቃድ የተሰጣቸው “አብይነትዎ” መሆናቸው አያነጋግርም። እስካሁን እሚወስኗቸው ውሳኔዎች በሙሉ በድርጅታቸው መልካም ፈቃድና ውሳኔ ብቻ የተከናወኑ ናቸው ብሎ መከራከርም ያስቸግራል። አብይ ከኢህአዴግ በላይ መሆናቸው እስካሁን ያልገባው ሰው ቢኖር ብዙ ነገር እማይገባው ኢህአዴግ ራሱ መሆን አለበት። ህዝቡ ግን ገብቶታል። አብይ ከኢህአዴግ በላይ ናቸው። የወደዳቸውም ከኢህአዴግ በላይ ስለሆኑም ጭምር ነው። ታዲያ መለስ ከኢህአዴግ በላይ አልነበሩ እንዴ? ሊባል ይችላል። የመለስ የበላይነት የመጣው ቆይቶ ነው። አመጣጡም በአምባገነንነት ነው። አብይ ግን ሥራ ሲጀምሩ ከህዝብ ፍቅር ጋር ነው። አስገራሚው ነገር ግን ይህ ፍቅር ያልዘለቀ እንደሁ አብይ ኪህአዴግም በላይ ሆነው መለስን መሆናቸው አይቀርም።
ቁም ነገሩ እሱ ሳይሆን በህዝብ የተወደዱ መሪዎች ሁል ጊዜም ወደ ሥልጣን ሲመጡ መጀመሪያ አካባቢ እሚያደርጉት ነገር ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ኦቦማ ሲመጡ እንደመጡ ተሯርጠው እንደ የጤና (ሄልዝ ኬር) የመሳሰሉ ትላልቅ ፖሊሲዎችን አወጡ። እየቆዩ ሲመጡ ግን እንኳን ህዝቡ ሁለቱ ፓርቲዎች ራሳቸው አላሰራ ስላሏቸው ብዙ ትላልቅ ነገሮችን መሥራት አልቻሉም። በደጋፊዎቻቸው እጅግ የተወዱዱትና ደጋፊዎቻቸውን የፓርቲያቸው ማስፈራሪያ ያደረጉት ትራምፕ ጊዜ ሳያጠፉ እሚያምኑበትን ነገር ሁሉ በቶሎ እየገለባበጡ ነው። እየቆዩ ሲመጡ ዴሞክራቶች ም/ቤቱን ያሸንፉና የደጋፊዎቻችም ድጋፍ ቀንሶ እንደልባቸው መወሰን እሚችሉበት ሁኔታ ይጠፋል። አሜሪካ ውስጥ እስከዛሬ ጥሩ የሆኑ ህጎች የወጡት መሪዎች ተወዳጅ በነበሩባቸው ወቅቶች እንደሆኑ ይነገራል።
ሁለተኛ በህዝብ የተወደዱ መሪዎች አጀማመራቸው ጥሩ ቢሆንም ነገሮች እያደሩ ሲመጡ የደጋፊዎቻቸውን በሙሉ ጥያቄና ችግር መመለስ ያቅታቸዋል። በችግሮች አፈታትና አመላለስ ላይም ቅሬታዎች እየጎለበቱ ሲመጡ ተቃራኒ አስተሳቦችና ፍላጎቶች እያየሉ ይመጣሉ። መሪዎች በባህሪያቸው መለወጥ ስለፈለጉ ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎች ይለውጧቸዋል። እየተገደዱም ሲመጡ በተለይ በእንደኛ ዓይነቱ አገር፣ ማሰር መግደልና ወደ አምባገንነት እየተሸጋገሩ ይመጣሉ። ስለዚህ በዚያ ጊዜ ማር እንኳ ላቅርብ ቢሉ እሚቀበላቸው አይኖርም። መሠረታዊና ታሪካዊ የፖሊሲ ለውጦችን ማውጣት እሚችሉት ሰው ማሰርና መግደል በጀመሩበት ጊዜ ሳይሆን፣ በተወደዱበትና ተቀባይነታቸው ሰማይ በነካበት ጊዜ ነው። ደርግ የመሬት ላራሹን አዋጅ ከቀይ ሽብር በኋላ ቢያወጣው ኖሮ ዛሬ የአባይ ግድብን ፕሮጀክት መስማት እንደማይፈልጉት ሰዎች ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የዋለ ርካሽ ነገር ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ስለዚህ አብይም ሳይነፍስባቸው፣ ህዝቡ ወይም ፓርቲያቸው እያደር ሳይቆረጥማቸው ወይም እሳቸው ሁላችንንም ልክ አስገብተው ጸጥ እረጭ ሳያደርጉን በፊት፣ ወይንም በጨዋ ደንብ “መስሎኝ ነበር እንዲህስ ከሆነ አልችልም…” ብለው ራሳቸውን ሹልክ ከማድረጋቸው በፊት መፈጸም ያለባቸውን ነገር ውለው ሳያድሩ ቢያደራርጉት ደህና ይመስለኛል።
እሚቀጥለው ጥያቄ ምን ያድርጉ? አሁንስ እያደረጉ አይደለም እንዴ ሊባል ይችላል። እርግጥ ነው መቸም እሚታወሱበትን ትላልቅ ነገሮችን አድርገዋል።  ከዚያም በተረፈ አሁን እያደረጉ ያሉት ነገር እርቅ ማውረድ፣ ሽምልግና ወንበር ማደላደል፣ ስብከትና ንግግር ሊሆን ይችላል። ሌሎች እስረኛ መፍታት የመሳሰሉት በሌላ መልኩ እሚታሰሩ ስለሚኖሩ ተመልሰን እዚያው መሆናችን አይቀርም። አብይ እንኳ ባያደርጉት አዳሜ እየተነሳ በርባንን እሰሩልን! ያን ሌባ ያን ሆዳም አስወግዱልን! ማለቱን ተያይዞታል። መሪ ዝም ቢል እንኳ ሰው ካልታሰረ ደስ እማይለው ብዙ ሰው አለ። በዚያ ላይ እንኳን እሰሩኝ ግደሉኝ ባይ ሞገደኛና ወንጀለኛም ሞልቶናል።
ይልቅ አገሪቱን እንደፊኛ እየነፋ ሊያፈነዳት የተቃረበው ድህነት ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ነው። በቀለለ አማርኛ አገሪቷ ገንዘብ የላትም። ምርት ቀርቶ ስንዴና ዘይት እየገዛች ህዝቧን እየመገበች መሆኑ ይታወቃል። ርዳታውም እየመነመነ የተራረፈውም እየተዘረፈ የአገር ካዝና ባዶ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው እየነገሩን ነው። ስለዚህ እነ አየር መንገድን ልንሽጥ ነው፣ በቃ ከዛሬ ጀምሮ ነዳጅ ማውጣት ጀምረናል ኤርትራ ድንበር ተቀምጦ በጀት እሚያሽመደምደው የሠራዊቱ ቁጥርም መቀነስ አለበት እየተባለ እሚነገረው ለዚህ ነው። የመድሃኒት እጥረት ተከስቶ አገር በቋፍ ላይ መሆኑን እሚያዉቁት ያውቁታል። ለሠራተኞች ነገ ደመወዝ መክፈል ሊቸገር ይችላል። ይህ ሁሉ በአብይ ፍቅር ተቀፍድዶ “ግድ የለም እንችለዋለን!” ተብሎ የተያዘ ይመስላል። ግን እስከመቼ?
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ – የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የኢኮኖሚ ማሻሻያው ስትራቴጂ የሚያስፈልግበት ዋና ምክንያት ሲናገሩ “ ሀገራችን ላለፉት አመታት ስትበደር ቆይታ አሁን መክፈያ ጊዜው ሲደርስ ለመክፈል ከፍተኛ ችግር በማጋጠሙ፤ ፕሮጀክቶችን መጀመር እንጂ መጨረስ ባለመቻሉና፤ የማስፈጸም አቅም ውስንነት መኖሩ እንዲሁም የኑሮ ውድነትም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ፤ የስራ አጥነት እየሰፋ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ስራ በማጣታቸው ነው” በማለት አስረድተዋል።
ኢኮኖሚው ማሻሻያ በሚለው የጠ/ሚሩ አገላለጽና በኢኮኖሚው ፖሊሲ ለውጥ በሚለው መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ያለውን ፖሊሲ ማሻሻል ነው ወይስ ያለው ፖሊሲ እየተለወጠ ነው? ችግሩስ ከፖሊሲው ነው ወይንስ ከፖሊሲው አፈጻጸም ነው? አብይና መንግሥታቸው ማድረግ እሚፈልጉት የትኛውን ነው? ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችስ የአፈጻጸም ወይስ የፖሊስ ወይስ የሁለቱም?
አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አስፈላጊና ቀዳሚውም ይመስለኛል። ኤክስፖርት አድርጋ እሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ገና ብቻ ሳትሆን የጀመረችው ሁሉ አይመስልም ። ምርቱም ገበያውም ለገበያው የማቅረብ አቅሙም ገና ይመስላል። እንኳን ከውጭ በዶላር በአገር ውስጥ ምርት እሚገኘውን ብር (ገቢ) ለመሰብሰብም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቷን ገና በወጉ ማድረግ አልቻለችም። ስለዚህ ገንዘብ የለም።
በቱሪዝምና አገልግሎት ሰጭ ዘርፎችም ዶላሩን ለመጥራት አልተቻለም። ምክንያቱም አንደኛ መንግሥት አብዛኞቹን የመሠረተ ልማት ዘርፎች በባለቤትነት ስለያዛቸው እንኳን ቱሪስቱ ነዋሪው ህዝብ እየተቸገረ ነው። ይህ ደግሞ  ገበያውን ለግሉ ዘርፍና ለውድድር ክፍት ካላማድረግ ፖሊሲ ጋር እሚገናኝ ነው። በዚህ ሁኔታ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት አልተቻለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግስት የተያዙ አንዳንድ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፍተኛ ድርሻ በመንግስት ተይዞ ቀሪው በአክስዮን እንደሚተላለፍ ውሳኔ ላይ መደረሱን መግለጻቸው ይህን ለመመለስ ይመስላል፡፡ ግን ኩባንያዎችን በስም እየጠሩ እንደየተቋም ድርጅቶቹ እሚደረግ ውሳኔ ወይስ በፖሊሲ ደረጃ ተይዞ ወጥ በሆነ አፈጻጸም እሚከናወን ነው? ተቃዋሚዎችና መንግሥት እዚህ ጋር እሚከራከሩት በፖሊሲው ሳይሆን በአፈጻጸሙ ላይ ይመስላል። ፖሊሲው ላይ ተስማምተው ይሆን? ደግሞስ በየትኛው ፖሊሲ? ለመሆኑ የአብይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምንድነው?
የኢኮኖሚ ፖሊሲው ሪፎርም ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች እየነገሩን ነው። አብይ በዚህ ላይ ውውይትና ትላልቅ ፓናሎችን በማድረግ ባለሙያዎችንና ህዝቡን ማነጋገር ማከራከር ይኖርባቸዋል። ሥልጠና መስጠት ብቻ ሳይሆን ከህዝብና ከባለሙያዎች የሚገኙ የተለያዩ ሀሳቦችን ማድመጥ ይኖርባቸዋል። እሳቸው ህዝብን ማሰልጠን እንደሚፈልጉት ሁሉ ህዝቡም እንዲያሰለጥናቸው መድረኩን በመክፈት ተማሪ ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ ለኢኮኖሚው ጉዳይ ተያያዥነት ያላቸው በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ። የፌደራሊዝም ሁኔታ፣ የመሬት ባለቤትነት ፖሊሲው፣ የነጻ ገበያውና የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ የፍትህ ተቋማት ለኢንቨስትመንትም ሆነ ለባለሀብቶች እንዲሁም ለጠቅላላው የአገሪቱ መረጋጋት እሚሰጡት ዋስትና፣ ሌላው ቀርቶ የብርን ትክክለኛ ዋጋ ከመወሰን አስፈላጊነት አኳያ (ዲቫሉዌሽን)፣ የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመትን ለመሳብ፣ በተለይም ዳያስፖራውን በኢኮኖሚው ተሳታፊ በማድረግ ረገድ ያለው የፋይናስና ኢንቨስትመንት ሁኔታው ምን ምን መሆን እንዳለበት፣ ዘርዝሮ እሚያስረዳ ፖሊሲ ይወጣ ዘንድ፣ ህዝባዊ ውይይት መኖር ያለበት ይመስለኛል።
“ጥሪውን ተቀብለናል” ያሉት የፖለቲካ ተፎካካሪዎችም ስለምርጫ ቦርድ ከማውራት በተጨማሪ እሱ ተቋቁሞ እሲከደርስ አጣዳፊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እሚችሉበትን ጥያቄ ማንሳት ይገባቸዋል። ተፎካካሪ ብቻ ሳይሆን ተመካካሪም ሆነው መታየታቸው አስፈላጊ ነው። “ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና ዶ/ር አብይ አህመድ ተገናኝተው ተነጋገሩ” እሚለው ዜና ከሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ በተለይ አጣዳፊ በሆነው የኢኮኖሚው ጉዳይ ላይ አብረው ለመስራት ተስማማተዋል እሚል ዓይነት ነገር ቢታከልበት ውይይቶች ፍሬ ያፈራሉ ብዬ አስባለሁ።
በተረፈ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስንደግፍ ድጋፋችን እንዲህ ያሉ ሁኔታዎችን ይፈጥሩልናል በማለትም ጭምር ነው። የፖሊስ አዛዦችን ብቻ ሳይሆን የባንክና የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችንም እየለወጡ መሆናቸውን ብናደንቅም ከሰዎቹም ጋር አብረው የፖሊሲ ለውጦችን ቢያሳዩን ደህና ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ ጊዜያቸው አሁን ነው! ህዝብን መምራት ሲያጨበጭብልህ እንጂ ሲያጨበጭብብህ አይደለም። “ተደምረናል” ብቻውን ያስቸግራል። ገንዘቡም ይደመር!
Filed in: Amharic