>

እነዚህ ሰዎች ተደምረዋል? (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

እነዚህ ሰዎች ተደምረዋል?
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
ሁሉ ነገር አንፃራዊ ነው። የእያንዳንዱ ሰው አመለካከትም ሆነ አቋም ደግሞ የግል ነው። መቼም በቡድን ማሰብ አይቻልም። ስለሆነም በአመለካከታቸውና በሚወስዱት አቋም ከቡድናቸው የሚለዩ ሰዎች መኖራቸው እሙን ነው።
እናማ ዶ/ር አርከበ እቁባይና ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በተለይ ከወግ አጥባቂው የህወሓት ቡድን ወጣ ያለ አቋም ያላቸው ይመስለኛል። ምንም እንኳን የህወሓትን የበላይነት አስጠብቆ የማቆዬት ፍላጎት ከውስጣቸው ባይጠፋም አሁን የተጀመረውን የለውጥ ሂደት መግታት እንደማይቻል የተገነዘቡ ይመስላል። ከዚህ በተቃራኒው የሚወሰዱ ግምቶች “ፉርሽ” ናቸው ባይባልም በዚያ አቅጣጫ ነገሮችን ለጥጦ ማዬት አንዳችም ፖለቲካዊ ትርፍ የለውም።
በእኔ እይታ ግን ሁለቱ ሰዎች ተራማጆች ይመስሉኛል። ደግሞም የራሳቸው ተከታዮች ሊኖሯቸው እንደሚችሉ እሙን ነው። ስለሆነም የለውጥ ኃይሎችን ማበረታታት ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
በተለይም ደብረ ጽዮን ለመደመር ምክንያት አለው!!!
ከህውሃት 17 ቀናት ስብሰባ በፊት ምንም እንኳን ምክትል ሊቀመንበር የነበረ ቢሆንም ደፂ የህውሃት ቁንጮ ነበር። በዚያ ስብሰባ ላይ የአቦይ ቡድን ከመለስ ሞት ቡኋላ የመለስ ተሿሚዎችን የማፅዳት ስራ የመጨረሻውን ምዕራፍ አከናውኗል። በዚህም መሰረት የመለስን ሚስት አስለቅሶ፣ አባይ ወልዱንም ጨምሮ አስወገዳቸው። ሳሞራንም ለማንሳት ሌሎች ጀኔራሎች ተሰየሙ። በዚህ ሂደት የተረፈው ደፂ ብቻ ነበር። ደፂ የተረፈው አብዝሃኛው ትግሬ ስለሚደግፈው ስላልተመቸ ነበር። በመሆኑም ይጠበቅ እንደነበረው በስትራክቸር ላይ ደፂ ሊቀመንበር ሆኖ አደገ ተባለ። ይሁን እንጂ ክልላችንን እናጠናክር በሚል ሽፋን ከፌደራል ላይ ሲነሳ ሁሉንም ጉልበቱን(የቴክኖሎጂ ሚንስቴርነቱን፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር አማካሪነቱን፣ የመከላከያና ደህንነት ተጠሪነቱን ፣የቴሌ ቦርድ ሰብሳቢነቱን….  አስረክቦ ) መቀሌ ተቀምጦ የአንደርታ ወረዳን ሪፖርት እንዲያነብ አደረጉት። በቀጣይም እንዳያንሰራራ የኢሜል ሚስጥሮቹ ወጡበት… ለጠቅላይ ሚንስቴርነት ሲወዳደር። ከ45 የህውሃት ድምፅ 2 ድምፅ ብቻ ተሰጠው…..
እናማ ለመደመር ምክንያት አለው ለማለት ነው!!!
እነዚህን ሰዎች በስመ ህወሃት መግፋት  ፈተናችንን ከማብዛት የዘለለ ፋይዳ የለውም!!
 በነዚህ ሁለት  ሰዎች የምሬን ተስፋ አደርጋለሁ።አርከበ በአዲስ አበባ መስተዳድር ደብረፂዮን በቴሌ የለውጥ ሰብዕና እንዳላቸው አስመስክረዋል።አሁንም ቢያንስ በአደባባይ ከለውጡ ተቃራኒ ቆመው አላየናቸውም።ስሜታቸውም አካላዊ ቋንቋቸውም ለውጡ የጎረበጣቸው ሳይሆን የተስማማቸው ነው የሚመስለው።እነዚህን ሰዎች በስመ ህወሃት መግፋት ወደ ፅንፈኛው ጥግ እንዱወሸቁ አድርጎ ፈተናችንን ከማብዛት የዘለለ ፋይዳ የለውም።ዕድል ሰጥተን ልናያቸው ልንገፋፋቸውና ልናበረታቸው ይገባል።

የተወሰኑ የወያኔ አመራር አባላት ለለውጡ ድጋፍ እንዳላቸው መረዳት ጠቃሚ ነው!!!

ያሬድ ጥበቡ
መረጃው ባይኖረኝም አርከበን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባየሁት ቁጥር የሰውነት ወይም አካላዊ ቋንቋው (body language) ለውጡን የሚደግፍ መሆኑን ይናገር ይመስለኛል። አንዳንዴ ከአፋችን ከሚወጣው ይልቅ ሰውነታችን ይበልጥ የሚናገር ይመስለኛል። ለምሳሌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲመተ በአል ቀን ባለሥልጣናቱን ሲጨብጡ ልቡም እንደ አይኑ የታወረውን የአስመላሽን ጥላቻ የፊቱ ገፅታ ቁልጭ አድርጎ  ያሳይ ነበር።
በወቅቱ ደብረፂዮንን አልተከታተልኩትም፣ ግን ከኢህአዴግ 17 ቀናት ግምገማ በኋላ ወጥተው የአራቱ እህት ድርጅቶች ሊቃነመናብርት ሲናገሩ፣ ለውጡን ይደግፋል የሚል ስሜት ተሰምቶኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።  የተወሰኑ የወያኔ አመራር አባላት ለለውጡ ድጋፍ እንዳላቸው መረዳት ጠቃሚ ነው። ይበልጥ ግን እነርሱም እንደ አቢይ በነፃነት መናገር ቢችሉ ይረዳ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic