>

"የመደመር (ምድማር) መርህን እንደግፋለን"  (የኤ/ው/ጉዳይ ሚንስትር ኡስማን ሳልህ)

“የመደመር (ምድማር) መርህን እንደግፋለን” 
የኤ/ው/ጉዳይ ሚንስትር ኡስማን ሳልህ
“የዛሬው ቀን ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ያሳያል” 
ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከኤርትራ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ንግግር የዛሬው ቀን ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ያሳያል ብለዋል፡፡
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቁ የኢትዮጵያን የሰላም ጥሪ በመቀበላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ከኤርትራ ጋር በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በባህል ጉዳዮች ላይ ብዙ የሚያስተሳስሩን ነገሮች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠብ ለልጅ ልጆቻችን ማውረስ የለብንም ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት፣ ሰውን፣ ጊዜን እንዲሁም ጭንቅላትን የሚበላ ነውና መሻገር ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ከኤርትራ ወገኖቻችን ጋር በይቅርታ ልብ ተጸጽተን በፍቅር ከመጣን እንሻገራለን፤ እንደመራለን፤ ያለንን ተካፍለን በመተሳሰብ መኖር እንችላለን ብለዋል ዶ/ር አብይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም ቀጣዩ ጊዜ ለቀጠናው መልካም ጊዜ እንዲሆን ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳልህ በበኩላቸው ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግነው፣ የዶር አብይን የመደመር (በትግርኛ ምድማር) መርህ እንደግፋለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት ተዘግቶ አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያውያን ያለው የፍቅር እና የመተሳሰብ ፍላጎት በኤርትራውያን ዘንድም መኖሩን ክቡር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በዝግጅቱ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አንጋፋ አርቲስቶች እና አትሌቶች ታድመዋል፡፡
EPA /የኢትዮጵያ ፕሬስ ኤጀንሲ/
Filed in: Amharic