>

ሚዲያውን ለቀቅ፣ ቃልኪዳኑን ጠበቅ…(በፈቃዱ ዘ ሃይሉ)

ሚዲያውን ለቀቅ፣ ቃልኪዳኑን ጠበቅ…
በፈቃዱ ዘ ሃይሉ (ጦማሪ፣ የመብት ተሟጋች)
——–
የብሮድካስት ባለሥልጣን ነባሩን ዋና ዳይሬክተር በአዲስ ሲተካ ቃል የተገባው የሚዲያ ነጻነት ይረጋገጣል በሚል ተስፋ ተቀብዬው ነበር። ትላንት አደባባይ የወጡት ሁለት ደብዳቤዎች ግን አስደንግጠውኛል። ደብዳቤዎቹ ትግራይ ቲቪ እና ENN ቴሌቪዥን ባለፈው ቅዳሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረገውን ሰልፍ ቀጥታ ያላስተላለፉበትን እና ሽፋን ያልሰጡበትን ምክንያት እንዲያብራሩ ይጠይቃል። ይህ እርምጃ የማሸማቀቅ እርምጃ ይባላል።
በርግጥ የትግራይ ቲቪ እንደ አሳዳሪው ትሕነግ (TPLF) የታየው የለውጥ ጭላንጭል ተቃዋሚ ነው። ቢሆንም ግን እየመጣ ነው ብለን የምንጠብቀው ነጻነት ለደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚዎችም መሆን አለበት። በርግጥ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29/5 መሠረት በመንግሥት ድጎማ የሚተዳደሩ ሚድያዎች የተለያዩ አስተያየቶችን ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ በዚህ መለኪያ ተለውጧል እያልን የምናንቆለጳጵሰው ኢቲቪም ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠራት አለበት። ምክንያቱም ዛሬ ኢቲቪ የሚያስተናግዳቸው ድምፆች በፊት የታፈኑ ስለነበሩ ተሰውሮብን እንጂ የዛሬዎቹን ተቃዋሚዎች ድምፅ ለአፍታም አስታውሶ አያውቅም። የENN ማብራሪያ ለመስጠት መጠራት ግን ሙሉ እብደት ነው። ምክንያቱም እንደነጻ ሚድያ ያልወደደውን ዜና አለመዘገብ ሙሉ መብት አለው። ተመልካች በማጣት ከገበያ ከወጣ የራሱ ጉዳይ። መንግሥት የሐሳብ ገበያው በነጻነት እንዲጦፍ በማድረግ ገለባው ከፍሬው ተንጓሎ በራሱ ሰዐት እንዲወጣ ብቻ ነው ማድረግ ያለበት።
ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያስገደደኝ ይህ ብቻ አይደለም። ዋዜማ ሬዲዮ ላይ ዛሬ የወጣው ሪፖርት «እኛ በሰበር ዜና ቢዚ ሆነን ከጀርባ የሚሠራው እያመለጠን ይሆን እንዴ?» አስብሎኛል። ዋዜማ እንደሚለው ENN ቴሌቪዥን ሐምሌ 1፣ 2010 ይዘጋል። ምክንያቱ ደግሞ 1ኛ፣ ኢትዮቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሰጡትን ማስታወቂያ መልሰው ወስደውበታል፣ 2ኛ፣ ከዳሸን ባንክ ሊያገኘው የነበረውን ብድር ብሔራዊ ባንክ በትእዛዝ አሳግዶበታል፣ 3ኛ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መረጃ እየከለከሉት ተቸግሯል። እነዚህ ዘዴዎች ከዚህ ቀደም ሚዲያዎችን ለማግለል እና ከገበያ ለማስወጣት ሲሠራበት የነበረ አካሔድ ስለነበር ዜናውን ማመን አልከበደኝም።
ስለዚህ መንግሥት ሆይ፣ የፈለገ ቅዱስ ሐሳብ ይዘህ ብትመጣ እንዲቃወሙህ፣ የፈለገ እርኩስ መንፈስ ቢሰፍርባቸው ሕዝብ እንዲዳኛቸው፣ የሚድያዎች ነጻነት ይከበርላቸው።
Filed in: Amharic