>

ሀገር በትኔው ሊበን ዋቆ በዛሬ እለት ኢትዮጵያ  ገብቷል! (አቻምየለህ ታምሩ)

ሀገር በትኔው  ሊበን ዋቆ  በዛሬ እለት ኢትዮጵያ  ገብቷል!  
አቻምየለህ ታምሩ
ከታች በምስሉ  በቀይ ቀስት ተመልክቶ  የሚታየው  ሰውዬ  ሊበን ዋቆ ይባላል። ሊበን  «የኦሮሚያ ነፃነት ግንባር»  ወይንም በእንግሊዝኛ Front for Independence of Oromia [FIO] የሚባል አገር በትን ድርጅት አመራር አባል ነው። የድርጅቱ  ዓላማ «ነፃ የኦሮሚያ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክን» መመስረት ነው።
የዚህ  ድርጅት አመራር አባል የሆነው ሊበን ዋቆ በኦገስት 2016 ሎንዶን ላይ ባደረገው ንግግር፤
«ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገንባት የሚል ነገር የለንም፤ ኢትዮጵያን መበታተን ነው አላማችን።» ሲል የድርጅቱን አላማ አቅርቦ ነበር። ሊበን ዋቆ ይህንን የድርጅቱን አላማ   በለንደኑ የኦሮሞ ጉባዔ ሊያቀርብ  ከታዳሚው ደማቅ ጭብጨባ   እንደተበረከተለት እናስታውሳለን።
በዛሬ እለት ደግሞ «ኢትዮጵያ መበተን አለባት፤ ትግላችንም ለዚህ ነው» ሲል ለንደን ላይ ያደመጥነው ሊበን ዋቆ  ሊበትናት እየታገላት ወዳለችዋ ኢትዮጵያ በማቅናት «ትግላችንን አገር ቤት ለማድረግ  የሚያስችል እድል ስለተፈጠረ አገር ቤት ገብተናል» ሲል  በኢቲቪ  ዜና እወጃ ከተናገረው  የድርጅቱ የልዑካን ቡድን ጋር አዲስ አበባ መግባቱን በቴሌቭዥን መስኮት ተመልክተነዋል።
የኔ ጥያቄ በትኔው ሊበን ዋቆና ግብረ አበሮቹ  «ትግላችንን አገር ቤት ለማድረግ  የሚያስችል እድል ስለተፈጠረ አገር ቤት ገብተናል» ያሉን  ኢትዮጵያን የመበታተን አላማቸውን ይዘው ለመታገል ነው ወደ አዲስ አበባ ያመሩት?    ወይንስ «ነፃ የኦሮሚያ ዴሞክራቲክ ሪፑብሊክን» የመመስረትና ኢትዮጵያን የመበታተን አላማቸውን ቀይረዋል?   አላማቸውን ከቀየሩ «ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መገንባት የሚል ነገር የለንም፤ ኢትዮጵያን መበታተን ነው አላማችን።» ላሉትና በምስልና በድምጽ ለሚገኘው አፍራሽ አላማቸው፤ በተለይም ሊበን ዋቆ ለንደን ላይ ላደረገው ኢትዮጵያን የማፍረስ ንግግሩ ለምን  የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ አልጠየቀም?
Filed in: Amharic