>

ኢትዮጵያ ወደ ሃያ አንደኛዉ ክፍለ-ዘመን የገባችበት እለት፤ ሰኔ 11, 2010.... (ሃራ አብዲ)

ኢትዮጵያ ወደ ሃያ አንደኛዉ ክፍለ-ዘመን የገባችበት እለት፤

         ሰኔ 11, 2010 እ,ኢ,አ ቢባል ማጋነን አይመስለኝም። (ራ አብዲ)

ምነዉ ያ፤ ክረምት አግቢ በዚህ አምድ ላይ ብቅ ብሎ «ዶ/ር አብይ ዉስጤ ነዉ» ሲል ባስደመመን!!

እስኪ እንደ ጎጃሞች እንዳየን፤ እንዳየን፤

ነጭ ጤፍ እንብላ፤ ዘንጋዳዉ ይቆየን። የሚለዉ የህዝባችን ዜማ ሳላስበዉ በዉስጤ ሞላ። እንጉርጉሮዉ አልጠቅም ሲለኝ ነዉ መሰለኝ፤ ትንሽ ቆየት ብዬ ደግሞ፤

እኛም ወግ አየን እንደሰዉ፤(2)

”አምላክ ምስጋና ይድረሰዉ…!” የሚለዉን የአገኘሁ ይደግን ዝማሬ አስነካሁት! ሰኔ 11, 2010 እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለፌደራል የህዝብ ተወካዮች ያቀረቡትን የመጀመሪያ የስራ ዘገባ (ሪፖርት) እና ለቀረቡላቸዉ ጥያቄዎች የሰጡትን መልሶች የተከታተልኩት በሙሉ ሃሳቤና በሙሉ ልቤ ነበር።

ማክሰኞ ጁን 19,2018 እንደ ኤሮፓዉያን አቆጣጠር፤ ወይንም ሰኔ 11, 2010 እንደ ኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር፤ በረንዳየን ቀለም በመቀባት ላይ ሆኜ ነበር ንግግሩን የምከታተለዉ። በምኖርበት ”ፕሮቪንስ” ሰሞኑን ከፍተኛ ሙቀት ስለነበር የዚያን እለት 29 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ነበር።ጸሀይዋ የከረረችና ሙቀቱም ሀይለኛ የነበረ ቢሆንም፤ ትንሽ ነፋሻ ነበርና ያን ያህል አልተቸገርኩም ነበር። ይሁንና፤አይፓዴን (I Pad) ቀለም እንዳይንጠባጠብበት እና ድምጹም እንዳይርቀኝ ፤አጠገቤ አድርጌ ከቦታ ቦታ እያንቆራጠጥኩ ንግግሩን ስከታተል አይፓዱ ላይ መልእክት አነበብኩኝ። መልእክቱም እንዲህ የሚል ነበር። «አይፓዱ እጅግ ከመጋሉ የተነሳ፤ ወደ 31 የሚሆኑት ፕሮግራሞች ፍሪዝ ተደርገዋል።የስልክ ቁጥሮች ለማየት ካልሆነ በስተቀር አይፓዱን ለጊዜዉ መጠቀም አይቻልም» የሚል ነበር።

ሆሆይ! የኢትዮጵያ እና የአብይ አምላክ ጠብቆኝ ነዉ እንጂ፤ ይህ ጠራራ ጸሃይ አንድ 31 ጅማቶቼን ፍሪዝ ቢያደርግ ማን ይከለክለዋል? ብዬ፤ አይፓዴን ይዤ ወደ ቤት ገባሁ። እጆቼን ለቅለቅ አድርጌ ላፕ ቶፔን ከፍቼ ጥያቄና መልሱን ምጥጥ አድርጌ ሰማሁት።

ቀደም ባሉት ጊዜያት አንድ ወዳጄ እዉነተኛ ታሪክ ነዉ ብሎ የነገረኝ ነገር ትዝ አለኝና ብቻዬን በሳቅ

ብ-ት-ን አልኩኝ። ወደ አሜሪካ ከመጣ ብዙም ያልቆየ አንድ ጎበዝ፤ «አንጀቴ ቅቤ ጠጣ» የሚለዉን አባባል «my intestine drinks butter» ሲል ተረጎመዉ አሉ ፤በማለት የነገረኝ መሆኑ ነዉ።

«አሸባሪዉ ማነዉ?»~~~ህገ-መንግስቱ፤ ሰዉን ጭለማ ቤት አስገቡ~~ግረፉ ይላል እንዴ?~~»

እኛስ ታዲያ አንጀታችን ቀላል ቅቤ ጠጣ እንዴ?? ከእንግዲህ፤ አብይ የሚባል ስም በትዉልዳችን ዘመን ሁሉ የተወደደ ስም ይሁን!!! ሃራ አብዲ እባላለሁ፤ ይህን ሃሳብ እደግፋለሁ።( My name is Hara Abdei; I approve this message).

በሀገራችን ታሪክ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ ግልጽነት አጠገበን። ምህረት ምን ማለት እንደሆነ በእጁ እያስነካ አሳየን።ርህራሄን ከሸፍጥ ፖለቲካችን ዉስጥ እንደምንም ብሎ ስፍራ አገኘለት። ኢትዮጵያ፣ እስከማዉቀዉ ድረስ እንደዚህ አይነት ቅንነት የስብእናዉ ዋልታ የሆነ መሪ ተፈጥሮባት አያዉቅም።( አንቱታ ክብር ነዉና በመግቢያዬ ተጠቅሜበታለሁ።አንተ ማለት ደግሞ የጀግኖችና የጥበብ ሰዎች  መለያ ነዉ ~~በዚሁ ልያዘዉ)።

«በእያሱ ዳቦ ነዉ ትራሱ፤ በተፈሪ ጠፋ ፍርፋሪ» ይባል ነበር ብለዉ አርበኛዋ ሴት አያት ያጫወቱኝን ታሪክ አልረሳዉም። እኔም በተራዬ ለልጅ ልጆቼ የማሳልፈዉ ጣፋጭ ታሪክ በጆሮዬ ገባ፤በአይኖቼም አየሁ።«አብይ የሚባል አርቆ አሳቢ፤ ምሁር፤ ይቅርታን የሚወድና እግዚአብሄርን የሚፈራ ሰዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ,,,,,,»

እርግጥ ነዉ የአብይ ዘመንና ቀደም ያሉት መሪዎች ዘመናት በእጅጉ ይለያያሉ። በትምህርት፤ በስልጣኔ እና ከሌሎች ልምድ ለመቅሰም በነበረ እድልም  ከቶ አይገናኙም።እነዚያም የራሳቸዉ በጎ ማንነት ነበሩዋቸዉ።በአመዛኙ ግን የጦረኝነትና ፤አንዱን ጥሎ የማለፍ እኩይ ታሪክም ሞልቶባቸዋል።

የአብይ ግን የተለየ ሆኖብናል። ኢትዮጵያ በረዘመዉ የምጥ ዘመን ዱብ ያደረገችዉ ደጎል አንበሳ ነዉ!!

ሰኔ 11, 2010 እ,ኢ,አ እጅግ ልዩ ቀን ነበር። የደስታ ስሜቴን በወቅቱ ለማንም ማጋራት አልፈለግሁም።

በዉስጤ ሃሴት እያደረግሁ ማምሸት ነበር የመረጥኩት።ሲደወል አላነሳሁም፤ እኔም ለማንም ስልክ አልደወልኩም።ደስታዬ ከስሜታዊነት ብቻ የመነጨ አልነበረም። ከዶ/ር አብይ ንግግሮች ጀርባ ማየት የቻልኩት ነገር ያለ ስለመሰለኝም ጭምር ነዉ። ሰዉ በልቡ የሞላዉን ያንኑ ይናገራል እንደሚል መጽሀፍ ቅዱስ ዶ/ር አብይ  በስልጣን ሳይባልግ፤ከዝርፊያና ከወንጀል ራሱን ገዝቶ፤ ተጠንቅቆ ባይኖር፤ እንደዚያ አይነት ድፍረትና ግልጽነት ማሳየት አይችልም። ለነገሩ፤ አንዳች ቢያገኙበት ኖሮ ገና ድሮ አብጠልጥለዉ «ለጥብስ» ያቀርቡት ነበር፤ሌቦቹ። ይህ ሰዉ ታሪክ ይሰራል፣ባገራችን፣በአፍሪካ,,,,

«ቀድሞ ማመስገን ለሁዋላ ሀሜት ይቸግራል» ይሉት አባባል ብዙዎችን እንዲቆጠቡ አድርጎአል። ማለፍያ ነዉ!! ከእንግዲህ ያለዉ ይበልጣል!!እነዚያ የቀን ጅቦች መግቢያ ቀዳዳ እስኪያጡ ድረስ ከጠ/ሚ/ር አብይ ጎን በመሆን ትግሉን ልንደግፍ ይገባል።«ሰርቀዉም ዝም የማይሉ» ነዉረኞች ለጥፋት ሸብረብ በማለት ላይ ባሉበት ወቅት ሀገሩንና ወገኑን የሚወድ ዜጋ ሁሉ አብይን በመደገፍ የተጀመረዉን ለዉጥ ማፋፋት ይጠበቅበታል። ስዩም መስፍን ከህወሃት ጄኔራሎች ጋር በሚስጥር እየመከረ መሆኑ ተደርሶበታል።አጥፍተን እንጥፋ ካሉ፤ የሚጠፉት እነሱ ይሆናሉ። እኛ ከብዛት እንተርፋለን!!!! ይህን ዘመን ያመጣልን የእግዚአብሄር ጣልቃ-ገብነት ነዉ።በሃያ አንደኛዉ ክፍለዘመን የአለም ህዝብ በዲሞክራሲያዊ መብቱ የሚጠቅመዉን ሲመርጥ፤የማይፈልገዉን በነጻነት ከስልጣን ሲያነሳ፤ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፤ፕሬዚዳንት፤ ለህዝቡ ድምጽ ሲንበረከክ፤ እኛ ግን የሶስት ሽህ ዘመን እድሜ ያስቆጠርን ሆነን፤ማንም አልባሌ ነፍጥ በማንገቡ ብቻ ሲረግጠን ኖሮአል።ኦሮማይ (በአሉ ግርማ)

እንግዲህ፤ እዉነት የማይመስል እዉነት የሀገራችንን ሰማይ ሞልቶታል። እኛም በሌሎች ሀገራት እንዳየነዉ ወግ ደርሶን ህዝቡን ይቅርታ የሚጠይቅ መሪ ቤተ-መንግስት ተሰይሞአል።

ኢትዮጵያ ወደ ሃያ አንደኛዉ ክፍለ-ዘመን  በተግባር የገባችበት እለት፤ ሰኔ 11, 2010 እ,ኢ,አ ቢባል ማጋነን የማይሆነዉ ለዚህ ይመስለኛል።

እንደ ክረምት አግቢ ብቅ እያለ የሚጎነትለን አንድ ወገን አለ።«ዶ/ር አብይ ዉስጤ ነዉ»

እስኪ ሰሞኑን ብቅ ብሎ ያችን አባባሉን ይድገማት። ከምር አጻጻፉን እወድለታለሁ።

«እኛም ወግ አየን እንደ ሰዉ፤ አምላክ ምስጋና ይድረሰዉ»

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ይባርክ

Filed in: Amharic