>

በደሴትነት ካለ ‹አስተዳደር› መላ አገርን ወደመቆጣጠር (ከይኄይስ እውነቱ)

በደሴትነት ካለ ‹አስተዳደር› መላ አገርን ወደመቆጣጠር

ከይኄይስ እውነቱ

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የሚከታተል ኹሉ የዶ/ር ዓቢይ ‹አስተዳደር› ከሚገጥሙት/እየገጠሙት ካሉ ፈተናዎች ዋናው የአገራችንን ህልውናና የሕዝባችንን ደኅንነት ላለፉት 27 የግፍ ዓመታት ሲፈታተናት የቆየውና አሁንም እየተፈታተናት ያለው የወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) ቡድን እና ይኸው የወንጀለኞች ጥርቅም የጣለላቸውን ሽርፍራፊ ሥልጣንና የዝርፊያ ሀብት ፍርፋሪ ለማስጠበቅ በታማኝ አሽከርነታቸው እስከ መጨረሻው ለመዝለቅ በሚፈልጉ ኅሊና ቢስ ሆዳሞች መሆኑ ይታወቃል፡፡

ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል እንደሚባለው ሰሞኑን ወያኔ ትግሬ በሠለጠነበት የተንኮልና የድንቁርና ስሌት ሁለት ብሔራዊ አጀንዳዎችን በአመዛኙ ራሱ በሚቆጣጠራቸውና ከፍ ብለን በጠቀስናቸው አሽከሮቹ አማካይነት የፓርቲ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ውሳኔው (ለድርጅቱ አዲስ እንዳልሆነ ተነግሯል) መሠረቴ ነው ከሚለው የትግራይ ክፍለ ሃገር ሕዝብ ጋር ያጋጨኛል ብሎ ሲያስብ ደግሞ ወደ መንተባተብና መዘባረቅ እንደገባ ታዝበናል፡፡ በእኔ እምነት ዶ/ር ዓቢይ ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻሻልና በሁለቱ አገሮች መካከል የዘለቀው አለመግባባት በሰላም እና የሁለቱንም አገሮች ሕዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲፈታ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ የወያኔ ትግሬ ስሌት ግን አዲሱን ‹አስተዳደር› ከሕዝብ ጋር ለማቃቃር ያለመ እንደነበር መግለጫ ተብዬውም ሆነ የወያኔ የሽብር ተግባራት ምስክሮች ናቸው፡፡ በቀጣይ አዲሱ ‹አስተዳደራቸው› ቀደም ሲል በወያኔ ትግሬ የበላይነት ውሳኔ ያረፈባቸው ወይም በይደር የቆዩ ጉዳዮችን የመቀበል ግዴታ አለበት ብዬም አላምንም፡፡ ምክንያቱም አሸባሪው ሕወሓት መቼም ቢሆን ለኢትዮጵያና ሕዝቧ የሚበጅ ውሳኔ ሊያስተላልፍ አይችልምና፡፡ ስለዚህ አሁንም እውነተኛ ሥልጣን፣ ጉልበትና የኢኮኖሚ አቅም በማን እጅ ነው? የሚለው መሠረታዊ ጥያቄ የዶ/ር ዓቢይን ‹አስተዳደር› ብዙዎቻችን እንደገመትነው (ዶ/ር ዓቢይም ጠንቅቀው እንደሚያወቁት) በአውሬዎች የተከበበ ደሴት አድርጎታል፡፡ አውሬዎቹና የግድያቸው ተቀራማቾች አሁንም በየሥልጣን እርከኑ በዶ/ር ዓቢይ አስተዳደር ጭምር ስላሉ ጠ/ሚኒስትሩ ሥራቸውን ሀ ብለው ከጀመሩበት ዕለት አንስቶ የማደናቀፍ ተግባራቸውን አላቋረጡም፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ጭንጋፎች የሚበረታቱ የለውጥ ጅማሮችን በማሳየት ግስጋሴ ላይ ያለውን ለዚህም በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ እውቅናና ተገቢውን ምስጋና እያገኘ ያለውን የዶ/ር ዓቢይ ‹አስተዳደር› ባጭር ለማስቀረትና የአፓርታይድ ሥርዓታቸውን አንግሠው ለማስቀጠል በትግራይ ሕዝብ ስም ግልጽ ጦርነት ከሰሞኑ ከፍተዋል፡፡ በየክ/ሃገሩም በነሱና ታማኝ አሽከሮቻቸው ቀስቃሽነት የሰው ሕይወትንና ንብረትን የጠየቀ የጎሣ ግጭቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ይህም የዶ/ር ዓቢይ ‹አመራር› ሠራዊቱንና የጸጥታ ክፍሉን በዚህም አማካይነት በኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ያሉ ሕወሓት-ሠራሽ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት የጸጥታ ችግሮችን ለጊዜው የመቆጣጠር አቅም እንደሌለው ታይቷል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም መንግሥታዊ (ቢሮክራሲው) መዋቅሮች ከአዲሱ ‹አስተዳደር› ይልቅ የወያኔ ትግሬ መዋቅሮች ተንሰራፍተው እንደሚገኙና በነዚህም ‹አስተዳደሩ› ሥር እንዳልያዘ አመልካች ነው፡፡ ስለሆነም የአዲሱ ‹አስተዳደር› ደሴትነት በውሸት ፌዴራሊዝሙ አንፃር ሲታይ በ‹ፌዴራሉም› ሆነ በየአካባቢው ባሉና ወደ ዘመነ መሳፍንታዊ አካሄድ እያዘመሙ ባሉ የክፍለ ሃገራት አገዛዞች ላይ እንደ አንድ አገር በበላይነት ‹ለመምራት› እጅግ ፈታኝ መሰናክል እየገጠመው ነው፡፡

የዶ/ር ዓቢይን ‹አስተዳደር› እስካሁን በወሰዳቸው አዎንታዊ ርምጃዎች እያመሰገንና እንዲቀጥልበት እያበረታታን፤ ታላላቆች እንደ መልካም አባት እየመከርንና እየገሠፅን፣ ከመንገዱ ሲናጠብ እየሞገትንና እያስጠነቀቅን፤ መዳረሻችን ነፃነት፣ እኩልነት፣ የሕግ የባለይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሆኑን ሁሌም እያሳሰብን፤ ዶ/ር ዓቢይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ እንዳሳወቀን ከወያኔ ትግሬ እየገጠመው ያለውን ፈተና በሚመለከት የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ ከዶ/ር ዓቢይ ጋር ባንድነት እንድንቆምና የወያኔ ትግሬን አፍራሽ የሽብርተኝነት ድርጊት በዓይነ ቁራኛ መከታተል ብቻ ሳይሆን በየክፍለ ሃገራቱ በዚህ አጥፊ ተግባር የተሰማሩትን ወያኔና አሸከሮቻቸው በዝርፊያ የተቆጣጠሩት ሀብት በሕዝብ ተወርሶ ለመሬት ወረራና ለዝርፊያ ከተሰማሩባቸው ቦታዎች በማባረር ለሕግ አሳልፎ መስጠት ይኖርብናል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን ለዶ/ር ዓቢይ ‹አስተዳደር› አቅም በመሆን የለውጥ ርምጃዎችን  በማፋጠን የመዳረሻችንን ጉዞ ማሳጠር እንችላለን፡፡ በተለያዩ ጽሑፎቼ ደጋግሜ እንደገለጽኩት የወያኔ ትግሬ ቡድን አይታረምም፤ ፍቅር፣ ሰላም፣ ይቅርታ፣ ዕርቅ በመዝገበ ቃላቶቹ የሉም፡፡ ስለሆነም በዚህ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ድርጅት ላይ ሕዝብ ተባብሮ ባንድነት ከተነሳ ሽብር ፈጣሪ ቀንደኛ አባላቱን አደብ ማስገዛት ይቻላል፡፡ አላስፈላጊ ጥፋትን ለመቀነስ፤ ከሁሉም በላይ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያና ለቀጣዩ ትውልድ መለያየትንና ጥላቻን ያራቀ ዘላቂ መደላድል ለመፍጠር በማሰብ እንጂ አላርፍ ካለ ይህንን የአጋንንት ስብስብ በዚህች የተቀደሰች ምድር ዳግም እንዳያንሠራራ በማድረግ ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት መጣል እንደምንችል ሊገነዘብ ይገባል፡፡

በሌላ በኩል ሥልጣንና ጥቅማችን ተነክቶብናል በሚል የለውጥ ርምጃዎችን ቀልባሽ ለሆኑ የሕወሓት አሸክሮች (ወያኔ ትግሬ በፈጠራቸው የትኛውም ድርጅቶች ውስጥ አባል ይሁኑ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ምህረት የለውም፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሕዝብ ውክልና አለመኖር ብቻ ሳይሆን ላለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ በመስጠት የሚታወቀው የቁም ሙቶች መሰባሰቢያ የሆነው የውሸት ፓርላማ የሕወሓት አሽከሮች ‹ጋጣ› መሆኑ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያውያን ጸሎት ፈጣሪ የገላገለን መርዘኛው መለስ፣ የእንጨት ሽበት ይዞ በድንቁርና የሚደነፋውና የ‹ሕግ ባለሙያዎችን› በመቅጠር ቀጥተኛ ኀላፊ የነበረው ስዩም መሥፍን (አቅደው፣ ሆን ብለውና ፈቅደው የኢትዮጵያን ግዛቶች ለኤርትራ አሳልፎ በመስጠት) በዋናነት፤ እና በሂደቱ በሕግ አማካሪነት ተሰይመው የነበሩት አምባሳደር ፍሥሓ ይመርና ሰይፈሥላሴ ለማ በግብርአበርነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ለተደረገው የአልጀርሱ የድንበር ስምምነት ቅሌት ተጠያቂነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ መጥፎ ስም ያለውና ከመነሻው አስፈላጊ ያልሆነ ስምምነት ውጤቱ በይፋ ሳይታወቅና ሳይፈረም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ተፃርሮ በዓዋጅ ያፀደቀ ‹ፓርላማ› የምኖች ስብስብ ሊባል እንደሚችል ሕዝብ ይፍረደው፡፡ ይህ የድውያነ አእምሮ መቀመጫና ማንቀላፊያ ሙት ፓርላማ የስምምነቱ ሰነድ በሌለበት ምን ዓይቶ ነው የማፅደቂያ ዓዋጅ ያወጣው፡፡ ስምምነቱ የተፈረመው እ.አ.አ. ዲሴምበር 12/2000 ሲሆን፣ የሕግ አውጭ የሚለውን ትልቅ ስም የተሸከመው የይስሙላ ፓርላማ ስምምነቱን በዓዋጅ ቊጥር 225 ያፀደቀው እ.አ.አ. ዴሴምበር 8/2000 ነው፡፡ ባልተለመደ መልኩ ከ4 ቀናት በፊት፡፡ ለምን አስቀድሞ ማፅደቅ አስፈለገ? ይህንን አሠራር ሥነ ሥርዓታዊ ፍትሕ ይፈቅደዋል ወይ? እልፍ አእላፋት ኢትዮጵያውያን የተሰዉበትና ድል ያደረጉበት ጦርነትን ተከትሎ የተደረገ ስምምነት  ይዘት ሳይታወቅና ሳይመከርበት በዓዋጁ መግቢያ አንቀጽ ላይ ‹‹… የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር…›› ተብሎ መገለጹ ምን ዓይነት ፌዝ ነው? የተጫኑትን ባግባቡ እንኳን ለማራገፍ የማይችሉ ወራዳዎች ሳይመክሩበት ‹ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር› ብለው በታዘዙት መሠረት ካፀደቁ በኋላ ስምምነቱ ለምን ይፈጸማል ብሎ ዶ/ር ዐቢይን መጠየቃቸው ምን ዓይነት መዝቀጥ ነው፡፡ ማፈሪያዎች!!! ይሉኝታ የሚባል ያልፈጠረባቸው ጉዶች!!! ታዲያ ይህ የ‹ከብት› ጋጣ እንጂ እንዴት አገራዊ ጉዳይ የሚመከርበት ሸንጎ ይሆናል? ከዚህም በላይ ገና ይዘቱ በይፋ ያልታወቀ ዓለም አቀፍ የሁለትዮሽ ስምምነት በዓዋጅ ማፅደቅ ሕጋዊ ነው ወይ? በወያኔ የይስሙላ ሕገ መንግሥት አግባብ እንኳን ፀድቋል ማለት ይቻላል ወይ?

ይህ አስተያየት አቅራቢ የመንግሥት ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ (ለሕይወት በሚያሰጋ ሁኔታ ከወያኔ ካድሬዎች ጋር ሲላተም ከቆየ በኋላ በዚህ የወንበዴዎች ሥርዓት ውስጥ ለአገር እሠራለሁ ማለት ራስን ማታለል ስለሆነበት – በግሉ ግፍና በደልን እየተቃወመ – ከማኅበረ እኩያን ራሱን አግልሎ ይገኛል፡፡) የወያኔ ሚኒስትሮች ም/ቤት እና ‹ፓርላማ› ባስረጅነት በቀረበባቸው አጋጣሚዎች በተግባር ማኅተም ማሳረፍ ብቻ ዋናው ሥራው የሆነው ‹ፓርላማ› በሕግ የተሰጠውን እውነተኛ ሥልጣን እንዲጠቀምበት ቢደረግ እንኳ አብዛኛዎቹ የእውቀት ጦመኞች በመሆናቸው አይደለም ዓለም አቀፍ ሕግን በይስሙላ ሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን ሥልጣን በውል የማያውቁት ጥቂት አይደሉም፡፡ ባንፃራዊነት ፊደል የቆጠሩ ግለሰቦች ስብስብ የሆነው ካቢኔው ሰለሚወያዩበት ነገር በቂ ግንዛቤ የሌላቸው፣ ከየመጡበት የሚኒስቴር መ/ቤት ያሉ የሕግና ሌሎች ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን ባለሙያዎች ሳያማክሩና፣ ሳይዘጋጁ የሚገኙ፤ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ለመጪ ትውልድ ጭምር ዓለም አቀፍ ግዴታ ውስጥ የሚያስገቡ ዓለም  አቀፍ ስምምነቶችን እግረ መንገድ እየፈረሙ የሚመጡ ጥቂት የማይባሉ (የሚኒስቴር መ/ቤት የሚመሩም ሆኑ የማይመሩ) ሚኒስትሮች እንዳሉ ታዝቧል፡፡ የአምባሳደር ተብዬዎቹማ (የአብዛኛዎቹ) ባይነሳ ይሻላል፡፡ በታሪካችን እንደ ወያኔ ዘመን ኢትዮጵያችን በዲፕሎማሲው መስክ ያፈረችበት፣ የተሸማቀቀችበትና የተዋረደችበት ጊዜ የለም፡፡ በተለያዩ መስኮች እውቀቱና ልምዱ ያላቸው ለዓለም የሚተርፉ ባለሙያዎች ያሏት አገር ቋያ በቅሎባት ተፈታ ማየት በሽተኛ አያደርግም ትላላችሁ? ይህ አስተያየት ቅድመ-ዐቢይ ያለውን ጊዜ ይመለከታል፡፡ ድኅረ-ዐቢይ የሚኖረውን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አሁን የሰበሰቧቸውን (አብዛኞቹን) የሚኒስትሮች ም/ቤት አባላትና ይህንን ማፈሪያ የይስሙላ ፓርላማ ይዘው የጀመሩትን በጎ የለውጥ ሂደት ለማስቀጠልም ሆነ ሕዝብ የሚፈልገውን መሠረታዊ ለውጥ (የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት) ለማምጣት (የወያኔ ተግዳሮት ተጨምሮበት) እንደሚቸገሩ በሚገባ ያውቁታል፡፡ በሌላ ወገን በየጊዜው ከሚያደርጓቸው ንግግሮች እንደተረዳኹት የተለያዩ ጊዜያዊ ግብረ ኃይሎችን ወይም ኮሚሽኖችን በማቋቋም ከሥር መሠረቱ የተበላሸውን የፍትሕ ሥርዓቱን፣ ለጎሣ ግጭት መንስዔ በመሆን የዘመናት አብሮነታችንን ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ የጣለውን የማንነት ፖለቲካ (በጎሣ/ቋንቋ ላይ የተመሠረተው የውሸት ፌዴራል ሥርዓት) ወዘተ. ለማስተካከል ማቀዳቸውን፣ ጥናቶችም እየተካሄዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከእስካሁኑ መልካም ንግግርዎ፣ ከፈጸሟቸው በጎ ተግባራት፣ የሕዝብን ፈቃድ ለመፈጸም ካሳዩት ቅንነት፣ የመንግሥት አሠራር ግልጽ እንዲሆንና ተጠያቂነትንም ለማስፈን ካልዎት ፍላጎት በመነሳት፤ ብሔራዊ ችግሮቻችንና ተግዳሮታችንን (ከሰሞኑ የፓርቲ ውሳኔ ያረፋባቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት፣ ቊልፍ መንግሥታዊ ድርጅቶችን ባለቤትነት በከፊል ለግል የማዛወሩ ጉዳዮችን ጨምሮ) ለመፍታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ኹሉ የሕዝብ (ተራው ሕዝብ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ አገር ወዳድ ምሁራን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የማኅበረሰብ/ሲቪክ/ ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች ወዘተ.) ተሳትፎን ማረጋገጥ ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ ይህንን ጅምር ለማየት ሕዝባችን ናፍቋል፡፡ ተማክረው ያደረጉት መፍትሄ ተቀባይነት፣ ዛላቂነትና አስተማማኝነት ይኖረዋልና፡፡ እንዲህ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁኑም በላቀ ሁኔታ ከጎንዎ ይሆናል፡፡ ‹ለአስተዳደርዎም› ዘብ ይቆማል፡፡ በጎ ለውጦቹኑም እንደ ዓይኑ ብሌን ይጠብቃል፣ ይከባከባል፡፡ ‹አስተዳደርዎም› ከደሴትነት ወጥቶ ሁሉንም የኢትዮጵያ ግዛቶች በመቆጣጠር ሕግና ሥርዓትን የሚያሰፍን ይሆናል፡፡

በመጨረሻም ለእስካሁኑ የሚያበረታቱና ተስፋ ሰጭ ርምጃዎች እንደ አንድ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማየት የሚናፍቅ ዜጋ ከልብ እያመሰገንኩ፣ ለወደፊቱ ደግሞ ከእስካሁኑም የላቁና በኢትዮጵያዊነታችን  እንድንኮራ የሚያደርጉ የለውጥ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ ተስፋ አለኝ፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ አምላክ በቸርነቱ አይለይዎ፡፡

Filed in: Amharic