>

ኢትዮጵያን ከማንነት ፖለቲካ መርዝ (De-ethnifation) ማፅዳት! የዓብይ ዓብይ ተግባር [የሱፍ ያሲን -ኦስሎ]

ኢትዮጵያን ከማንነት ፖለቲካ መርዝ (De-ethnifation ) ማፅዳት

የዓብይ ዓብይ ተግባር

የሱፍ ያሲን ኦስሎ
አሁንም ተስፋና ስጋት ጐን ለጐን እየተጓዙ ናቸው፣ በኢትዮጵያችን። እርግጥ ተስፋው እየፈካ፣ ስጋቱ እየደበዘዘ ይገኛል መባሉ ተገቢ ይመስለኛል። ምክንያቱ እውነታውን የሚያንጸባርቀው እሱ ነውና። ስጋቱ እየተነነ፣ ተስፋው ምህዳሩን ሙሉ በሙሉ እየተቆጣጠረ ነው የሚል ተስፋ ያላሰነቀ ኢትዮጵያዊ ማግኘቱ እያስቸገረን ሆኗልና። የኻይር ወሬ በሽበሽ ነው፣ አልፎ አልፎ የግጭቶችና መፈናቀሎች ዜና ቢያስበረግጉንም ቅሉ።
ዛሬ ለለውጡ ተስፋችን በሚደበዝዙ አለመረጋጋቶች እንጀምር መሰለኝ። ሕገ መንግስቱን አውጀናል ያሉት ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦቻችን እየተጋጩ ናቸው፣ በአራቱ የሃገሪቷ ማዕዘናት። የማንነት ፓለቲካው ምስቅልቅሎች አሁንም እየመሰቃቀሉንና እያተረማመሱን ናቸው። በአዋሳ ከተማ፣ በወልቂጤና ወላይታ እየታየው ግድያና መፈናቀል አብሮነታችን መልካም ምልእክቶች አይደሉም። ድንበር እየተጋፉ ናቸው። ክ80 በላይ ናቸው ከሚባሉት ብሔር ፣ ብሐረሰቦችና ሕዝቦች 2/3ኛው የሚገኘው በዚሁ በደቡብ ክልል ነው። ከ 65 በላይ የሚሆኑቱ። አንዱ የክልል ጥያቄ ይዞ ብቅ ብሏል፣ ሌለኛ የዞን ጥያቄ። ሁለቱም ራስን በራስ የማስተዳደር እርከኖች ጥያቄ ናቸው። ከዚያም አልፎ ባንድ ኢትዮጵያ በምትባል ሃገር አብረን መኖር ወስነናል፣ ፈቅደናል ካለን በኋላ አብሮነታችን በምን መልክ ይደራጅ በሚለው ላይ ገና እልባት ያላገኙ ጉዳዮች አሉ ማለት ነው። እውነት እነዚህ ችግሮች የአከላለል ችግሮች ናቸው። አንዳንድ ጥያቄዎች የፌዴራል ስርዓቱ አብሮ ወለድ (in herent) ባሕርያት ጋር የተቆራኙ ችግሮች ይመስላሉ።
አዲሱ ጠቅላይ አጭርና ረዥም መፍትሔ ሓሳቦች አላቸው። ባጭሩ፣ እይታ በህዝቦች ችግር የሚነግዱትን የክልል አስተዳዳሪዎች ስልጣናቸውን ”በገዛ ፈቃዳቸው” እንዲለቁ መገፋፋት። ይሰራ ይሆን? ዓብዲ አሌ፣ በገዛ ፍቃዱ ሥልጣን ይለቃሉ ብሎ ማሰቡ ተኣምር መጠበቅ ነው። የዋህነትም ይመስላል። በረዥሙ ግን የአከላለሉና የፌዴራል ሥርዓቱን እንደገና መፈተሹ ነው ተብሏል። ይህ ተገቢና ወሳኝ እርምጃ ይሆናል። ይቋቋማል የተባለው ኮሚሽን አከላለሉን ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥቱ ማሻሻሉ ቢያካትት ሥር ነቀል መፍትሔ አይሆንም ወይ? ምናልባት ከምርጫው በኋላ ወደ አዲስ ህገ መንግስት ቀረጻ፣ መንደፍና ማጽደቁ የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ሃሳብ ለማቅረብ ነው። ሌንጮ ለታ ”ችግሩ የአከላለልና የፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር ሳይሆን ስርዓቱን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ አለመቻሉ ላይ ነው ” የምትል ሃሳብ ሲደጋግሙ ሰምቼአለሁ። ህገ-መንግስቱ እስከሚሻሻል ድረስ ዲሞክራታይዝ መድረጉን በምር መያያዙ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ያም ሆነ ይህ ጉዳዩ ስር የሰደደ ችግር። በዚያኑ መጠን ስር- ነቀል መፍትሔን ያሻል። የይድረስ ይድረስ ሳይሆን የጥናት ውጤት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ይሁንታ የታከለበት መሆን ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከማንነት ፖለቲካ ምስቅልቅልና መርዝ ማጽዳቱ (De-ethnifation of Ethiopia politcal landscape) ተግባር ቀላል ተግባር አይሆንም።የሰሞኑ ግጭቶች ብቻ ሳይሆን ከላይ በላይ የሚጨመሩ ማንነት ፖለቲካ ማጠንጠኛ መንቀሳቀሳቸው ያደረጉ ድርጅቶች ተግባሩን ያካብዱታል፣ ያወሳስቡታል። የእነዚያ ጉዞ በተገላቢጦሹ አቅጣጫ ነውና። ይህ ድርጊታቸው አንድ የአረቦች ይትበሃል ያስታውሰኛል።
ሓጂ ዘየራቸው አድርሰው በመልስ ጉዞ ላይ እያሉ ገና ወደ ሓጅ ከሚተሙ ተጓዦች (ሓጃጆች) በመንገድ ላይ ይተላለፋሉ የምትል አስተዛዛቢ አባባል። ”ያሕጁና ዋናስራጂዓ” በዓረብኛው የሚባልላቸው ሓጂዎች።
ገና ሥልጣን ሳይጨበጡ ”በአርሒቡ” ዘፈናቸው ጓደኞቻቸው ”ያንዣበበው ስጋት በፍቅር አስወጋጅ” ተብሎ የተዘፈነላቸው ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅር መስበኩን ቀጥሎበታል። የሃይማኖት መሪዎች እንኳን ዋና ስራቸው (ፍቅር መስበክ?) በዘነጉባት ሃገር። የኢትዮጵያ ሕዝብ የራበውም እሱ ነበር። ይህ ተግባር ድልድዮችን መገንባት ብቻ የጥላቻ ግርግዳዎችን ማፍረስን ይጨምራል ተብሏል። እየገነቡም እያፈረሱም ናቸው። ሽግግሩ ሊቀለበስ ወደማይችለው ደረጃ መሸጋገሩን ማረጋገጥ ነው አንዱ ማስተማመኛው። ወደዚያ ደረጃ ገና አልደረስንም። የቅዳሜው ከጎናችሁ አለን የድጋፍ ሰልፍም አደናቃፊዎችን ያደናብራል፣ የኃይል ሚዛኑንና አሰላለፉን ጥርት አድርጎ ያሳያል ተብሎ ተገምቷል። ከተለመደው የፍርጃ ባህል በፀዳ ነገር ግን ለመነጋገር የምንሸማቀቅባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መኖር ሳይገባ ግልጥልጥ፣ ፍርጥርጥ አድርገን እንወያይ፣እንነጋገር፣በሁሉም መድረኮች፣ በተገኙ አጋጣሚዎች ሁላ! በተለያዩ ምክንያቶች አንዴም፣ ሁለቴም፣ ሶስቴም መልካም ዕድሎች አመለጡን ብለን እንቆጫለን። የጀርመኑ ባለቅኔና ፈላስፋ ፍርድሪሽ ሺለር (1759-1805)  (Great moment has found little people) (ታላላቅ ኩነቶች ተከሰቱና ታናናሽ ሰዎች አስተናገዷቸው) እንዳለው ሳይሆን (አሰባሳቢ ማንነት ባንድ ሀገር ልጅነት ገፅ 416) ባሁኑ ጊዜ ለታላቁ ኩነት (Great moment ) ታላቅ ሰው አለን ብለን አፍ ሞልተን መናገር እንችል ይሆን ወይ እላለሁ። እቆዝማለሁ። ዶ/ር አብይ እንደማያሳፍረን እምነቴ የፀና ነው። 
Filed in: Amharic