>

አብይ እና ትራምፕ  (ደረጄ ደስታ)

ደግሞ ምኑን ከምን ትሉ ይሆናል። እስኪ ተረጋጉ። ሰዎቹ እንደሚለያዩ መቸም ታውቃላችሁ። እሚመሳሰሉበትስ ነገር እንዳለ አስባችው ታውቃላችሁ? እነሆ ለጨዋታው ድምቅት-
በመሪዎቻቸው የተነሳ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ቦታ እየተለዋወጡ ይመስላል። ሁለቱም አገራቸውን አንዳቸው ወደ ጨለማ አንዳቸው ወደ ብርሃን እየመሯት ይሆን? ያን ለማድረግ ግን ሁለቱም ገና ብዙ ርቀው መሄድ ይኖርባቸዋል።
ሁለቱም እሳት የጎረሰ ደጋፊ አላቸው። የሁለቱም የጥንካሬ ምንጭ ህዝቡ ነው። ትራምፕን ለፕሬዚዳንትነት ያበቃቸው ህዝቡ ሲሆን አብይንም ቢሆን ህዝብ አልተለያቸውም። አሜሪካ በድምጹ ኢትዮጵያ በአመጹ መሪውን አንግሷል። ዋ! የተነኩ ቀን።
ሁለቱም ደፋር መሪዎች ልማዳዊ ሥርዓትና አስተዳደርን መገለባበጥና መነቀቃል የፈለጉ ይመስላል። ልዩነቱ የአሜሪካ ተቃዋሚዎች ሥራችን ሊነቀል ነው ብለው ሲሰጉ ፣ የኢትዮጵያዎቹ ደግሞ ቅርንጫፉን እንጂ ሥሩማ ገና መች ተነካ ባይ “ሥር ነቀሎች” መስለዋል።
ሁለቱም ፓርቲዎቻቸው ላይ ያመጹ አርበኞች መስለዋል። አብይ የውስጥ አርበኛ ሲሆኑ ትራምፕ ከውጭ ነው የመጡት። አብይ በድርጅታቸው ይመረጡ እንጂ ሁለቱንም ለአገር መሪነት አጭተው ያቀረቡት ድርጅቶቻቸው ሪፐብሊካን እና ኢህአዴግ ናቸው። ሁለቱም ምን ሲያቀብጠን መረጥናቸው ሳይሉ አልቀሩም።
ወፈፈም ያደረጋቸው ትራምፕ ጠብ ያለሽ በዳቦ ሲመስሉ አብይ የሰላም ዘማሪ መስለዋል፡፡ ትራምፕ እንደ ወፍጮ ቤት የበረንዳ ፍየል ያገኙትን እየደረማመሱ እሚሄዱ ሲሆኑ፣ አብይ ግን የተደረማመሰውን ህዝባቸውን መልሰው መጠጋገን እሚመኙ አስተዋይ መሪ መስለዋል።
ትራምፕና አገራቸው ገንዘብ ተርፏቸው አገራትን ለመቅጣት የገበያ ጦርነት ሲከፍቱ አብይና አገራቸው ገንዘብ ቸግሯቸው ከሌቦች የተራረፈቸውን የጉሊት ኢኮኖሚያቸውን መልክ መልክ ለማስያዝ እሚባዝኑ መስለዋል።
ትራምፕ ችግር መፍታት ሲያምራቸው ችግር ፈጥረው ይፈታሉ። አብይን ግን እንኳን ችግሩ ዘንድ ሊደርሱ የታሰረውን ሰው እንኳ ገና ፈተውና አስፈትተው አልጨረሱም። ትራምፕ አሜሪካ ተቀምጠው ከሰሜን ኮሪያ እስረኛ አስፈትተው ሲያስመጡ፣ አብይ ግን በየአገሩ እየዞሩ ይለቅማሉ።
ትራምፕ ልቅ ሲሆኑ አብይ ሊቅ ይመስላሉ።
ትራምፕ እንደ አገራችን መሪዎች የጃጁ እምቢ አላረጅም ባይ አጁዛ ናቸው። አብይ ግን ገና ሮጠው ያልጠገቡ ተፌ ጎረምሳ ናቸው።
ትራምፕ ለጋዜጠኞቻቸው እማያልቅ ርዕስ ሆነው ሲያስቸከችኩ ይውላሉ። አብይ ደግሞ አፍዘው አደንግዘው እንኳን ለመቃወም ለመደገፍ እንኳ እሚባል እስኪጠፋ ድረስ አፍ ያሲዛሉ። ደግነቱ ህዝብ አጨብጮ እስኪጨርስ መጠባበቅ ያለ ነው።
ወይ ደግፈን ወይ ነቅፈንማ ካልጻፍን ጋዜጠኝነትና ጸሐፊነቱን ምን ልናደርገው ነው? መደገፍን እና መንቀፉን ትተን ያለውን እንዳለና እንደሆነው አድርገን ለመዘገብ ግን ትክከለኛ ጋዜጠኞች መሆን ይኖርብናል። ትራምፕ ጋዜጠኞችን ቱልቱላ ሁላ (ፌክ ኒውስ) ሲሉ አብይም “የሚዲያ ሰዎች ሚዛናዊ ሁኑ” እሚል መልዕክት አስተላልፈዋል። ለአስተያየትና ለዘገባ ሚዛናዊነት ግን መረጃን እንደልብ የማግኘት ነጻነት ያስፈልጋል። እኛ መንግሥትን ሚዛናዊ ሆነን እንድናየው ከተፈለገ መንግሥትም ጋዜጠኞችን በሚዛናዊ ዓይኑ ሊመለከታቸው ይገባል። ትራምፕ እማልፈጋቸውንማ ጋዜጠኞች በመቃብሬ ላይ ሲሉ ፣ በሰዎቻቸው የቁም መቃብር ላይ የቆሙት አቶ አብይ ግን ጋዜጠኞች መምረጥ እስኪታክተን ድረስ በኢንፎርሜሽን ያንበሸብሹናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አይ የኛ ነገር ለካ ረስቼው ነው – አብይም እንደትራምፕ ኢንፍሮሜሽንን አናት በአናቱ አከታትለው በቀጥታ እየለቀቁ ነው። የአብይ ግን ከትራምፕ ትዊተርም የፈጠነ መሰለኝ። አይደል?!
ቀጥሎ ያለውን ሊንክ ይጫኑ። ትራምፕ ስለ ጠሚ አብይ አህመድ ከ ኤን ቢሲ ቴሊቪዥን ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመመልከት።
Filed in: Amharic