>
5:13 pm - Thursday April 20, 7865

አብይና የነገው አስቸኳይ የፓርላማ ጥሪ!

አብይና የነገው አስቸኳይ የፓርላማ ጥሪ!

ደረጄ ደስታ
እኔ እበላው ሳጣ ፓርላማው ጥርስ አወጣ! ፓርላማችን አደገች መባሉ ነው። አንድም ቀን አቶ መለስ ዜናዊን ጠርታ አታውቅም። እንዲያውም ተጠሪነቷ ለአቶ መለስ ሆና የኖረች ይቺው ፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ለአስቸኳይ ማብራሪያ ጠርታለች ሲባል ሰማን። ሰውየው ነገ ቀርበው ስለ ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ስለባድመና ስለ እሚሸጡ ንግድ ድርጅቶች ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። ውሳኔዎቹ የተላለፉት በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት መሆኑ ይታወቃል። ውሳኔዎቹ የተላለፉት በድምጽ ብልጫ ይሁን በሙሉ ድምጽ አልተገለጸም። ግልጽ እየሆነ የመጣው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ገትሮም ሆነ አሸቀንጥሮ ለመጣል የተገኘውን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም ነው። ቢቻል በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ካልሆነም በፓርላማው ከፍ ካለም በህዝባዊ ተቃውሞ ለመጣል ፍላጎት መኖሩ እየታየ ነው። በህወሓት መግለጫ ለነባርና አንጋፋ አመራር አባሎቻችን እውቅና ይሰጣቸው ከተባሉት ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ ሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ እንዳይገቡ ተብለው በአብይ መከልከላቸው ይታወቃል። ሥራ አስፈጻሚ አባል ካልሆኑ ምን ያደርጋሉ? ከሌሎችም ድርጅቶች እነበረከት እነ ካሱ ኢላላ አሉበት። እጅግ ከሚናፍቁት ከፓርቲያቸው ጠቅላላ ጉባኤ ሌላ አብይን በቀጥታ ገብተው ሊሞግቱ ካልሆነም ሊያስሞግቱ እሚችሉበት መንገድ አንዱ ፓርላማ ነው።
ሰዎቹ ደግሞ ከሁሉም በላይ ድምጽ ለመሰብሰብ አሁንም በብአዴን አባላት ተስፋ አልቆረጡም። ደቡብን ይዘው ከብአዴን የቻሉትን ዘግነው ከአብይ ጋር የቆሙትን ኦህዴድና ከፊል የብአዴን አባላትን በድምጽ ብልጫ ገፍተረው ለመጣል እየሞከሩ ነው። ምንም እንኳ በአብይ ውሳኔዎች ባንስማማም ወይም ፓርላማው ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ባንቃወመም፣ አብይ ሆነ ተብሎ እንዲነከሩበት በተደረጉ አጀንዳዎች ተጠልፈው መውደቃቸውን አንሻውም። የሰዎቹ ጥያቄና ስጋት የአብይ ውሳኔዎች ሳይሆኑ አብይና ከኋላቸው ያለው የህዝብ ድጋፍ ነው። ውሳኔዎቹማ ድሮ የተወሰኑ የራሳቸው ውሳኔዎች ናቸው። ያልተፈለጉት አብይና እሳቸውን ተክትሎ የመጣው ለውጥ ነው! ከኢህአዴግ ፓርላማ ህዝብ ይበልጣልና ህዝቡ የበላይነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በየአካባቢው ያሉትን የፓርላማና የኢህአዴግ አባላትን በሙሉ በማስጨነቅ ተቃውሞውን ማሳየት አለበት። የህዝብ ፓርላማ እስኪመሰረት በራሳቸው ፓርላማም መጫወት ጥበብ ይመስለኛል።
Filed in: Amharic