>

ህወሓት በራሱ ልክ ያሰፋው ቁምጣ እና መዘዙ (ስዩም ተሾመ)

በቀላል አገላለፅ እና አቀራረብ ድብቁን እና ረቂቁን አጉልቶ በማሳየት ይህንን ሙህር የሚያህሉት ውህዳን ናቸው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ሙህሩ ዶክተር መረራ በተለያዩ ጊዚያት የተናገሯቸው ነገሮች ሲፈፀሙ አይተናል፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ነገር በሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠረ ቁጥር የሆነ ወቅት ዶ/ር መረራ ካሉት ጋር እየተመሳሰለብን ማሰላሰላችን አልቀረም፡፡ እኔም ዛሬ በሀገራችን እየሆነ ያለውን ከተመለከትኩ በኋላ ያስታወስኩት እርሳቸው ባንድ ወቅት ኢሕአዴግ የአለም ምርጡ ሕገ-መንግስት ነው ብሎ የሚመፃደቅበትን እና ከርሱ በኋላ ያቋቋማቸውን ተቋማት፣ አሰራሮች እና ስርአቶችን ካስተዋሉ በኋላ “የኢህአዴግ ቁምጣ፤ ብሉኮ” የሚል አጋለፅ እንደተጠቀሙ አስታውሳለሁ፡፡ ኢህአዴግ ሀገር ሰፍቶ እንዲያለብስ ታሪክ የጣለበትን አደራ ለራሱ በሚመጥነው መልኩ ሰፍቶ በመልበስ እና ሀገር ራቁት በማስቀረት የተካነ ድርጅት ነው፡፡ ሀገርም ካረጀና ከተበጣጠሰ ብልኮዋ ጋር ቁር ውስጥ ተዘፍቃለች፤ አብይ የተባለ ብላቴና ደግሞ ሀገር በብርድ እንዳትሞት ከላይ ከታች ይዋትታል፡፡

ህወሓት ምንን ይመስላል? ተፅእኖ ፈጣሪዎችን
ህወሓት/ኢሕአዴግ በሀገር ላይ ያሻውን እንዲየደርግ ሁኔታዎች ፈቅደውለት ነበር፡፡ እርሱ ሁሌም እንደሚለው ምርጥ ፖለቲካ ርእዮተ አለም (መስመር) ስለሚከተል አይደለም፤ ሕህብ ስለወደደው ወይንም ስለመረጠው አይደለም፡፡ የመጀመሪያው የኢህአድግ ጥንካሬ የሚጀምረው ሁሉንም ነገር ለድርድር ለማቅረብ ከመቁረጡ ነው (እናቱን ለቁማር እንደሚያስይዝ የቁማር ሱሰኛ ነው)፡፡ እስካሁን ያልተፈታው የኤርትራ ችግርም ከዚህ የሕወሓት ባህሪ የተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ገዥ ነበርች ብሎ መስበኩ፣ ይግባኝ የሌለው የድንበር ማካለል ስምምነትን በአልጀርስ ፈርሞ መስጠቱ እንዲሁም የኤርትራ ነፃነት መቀበሉ አንድ ነገር ሆኖ የሀገርን ቋሚ ጥቅም በሂደቱ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ቀጣይ ችግሮችን በሚፈጥር መልኩ ተንበርካኪነት በማሳየት አሁን ያለንበት ውስብስብ ችግር ውስጥ ከቶናል፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ከደርግ ውድቀት በኋላ ሻእቢያ እስከ ጦርነቱ ድረስ ሁሉን አድራጊ ሁሉን ፈጣሪ ነበር (የፈለገውን ይገድላል፣ ያሳድዳል፣ ይዘርፋል)፡፡ በጦርነቱ ማግስት ደግሞ ህወሓት በሀገር ሉአላዊነት መደፈር ጥሩንባን ደጋግሞ በመንፋት የሕዝን ድጋፍ በማሰባሰብ ስልጠን ጠቀለለ፡፡ ለስልጣኑ ጠንቅ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን የራሱን አባላት ዘብጥያ አወረደ፣ አባረረ፣ አገለለ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ቅድሚያ የተሰጠው የተወሰኑ ግለሰቦች የስልጣን ጥም ማርካት ብቻ ነበር፡፡
ደርግ ሲወድቅ (ለስሙ ጉባኤ አድርጓል) ሁሉንም ገለል አድርጎ ኢህአዴግ የሚባለውን ግንባር በራሱ ልክ ከመስፋት ጀምሮ ሁሉንም በሀገሪቱ የተወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ በራሱ ባህሪ አምሳል የተሳሉ አርድጓቸዋል (ከዚህ በፊት የተፃፈ የእንግሊዝኛ ፅሁፍያንብቡ)፡፡

በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ህዝብ ያነሳቸው የነበሩ ጥያቄውችም በራሱ ልክ እየሰፋ ተጠቅሞባቸዋል፡፡ ህወሓት ሲጀመር የራሱ ሀሳብ ኖሮት አያቅም፡፡ ከስልጣን ውጭ ሁሌንም ሀሳቦች ሰርቆ/ጠልፎ ለስልጣኑ ድልድል ይጠቀምባቸዋል፡፡ ለማሰታዎስ ያክል የብሄር፣ የመሬት ጥቄዎችን ጠልፎ በመውሰድ ስልጣኑን ለማጠናከር እና የፈልገውን ለመጥቀም ያልፈለገውን ለመጉዳት የሚያገለግል መሳሪያ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ ያክል ብሄርን መሰረት አድርጎ ያስተዳደር ክልል ሲያቋቁም 20 ሺህ ለሚሆኑ ሀረሪዎች በስራቸው 100 ሺህ ኦሮሞ፣ 60 ሺህ አማራ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጉራጌ ተጠቃሎ ክልል ሲደራጅላቸው፤ በተቃራኒው ደግሞ ለሰሞኑ ግጭት ምክንያት የተደረገው የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ እና ሌሎች ሕዝቦች በአንድ ላይ በማጨቅ ድቡብ የሚባል ክልል አቋቁሞ ለራሱ አገዛዝ እንዲያመቸው አደራጅቷል፡፡

በተቋማት ደረጃም ስናይ ቀደም ሲል ከጣልያን ወረራ በኋላ የተቋቋመውን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ዘመናዊ የመከላከያ ሰራዊት በማፍረስ በማሌሊት አይዲዎሎጂ የሰለጠኑ ፖለቲከኛ-ጀኔራሎች የሚመሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አቋቁሟል፡፡ ይህንን ተጠቅሞም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን ፍትሀዊ ምርጫ በ1997 አፍኗል፤ በተደጋጋሚ ሀሳብን በጉልበት በመደፍጠጥ ሕዝብ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ የአመፅ እና የብጥብጥ ጎጅ ልምድ እንዲያጎለበት አድርጎታል፡፡ የደህንነቱ ክፍልም እንዲሁ ደርግ ለህዝብ ማሳደጃ የተጠቀመባቸውን ስልቶች በእስር ላይ ከነበረው የደርግ ደህንነት ሚኒስትር በመማር የራሱን ያፈና መዋቅር አቋቁሟል፡፡ እነዚህን ውርስና ቅርሶች ይዞ ቀጣይ ሁሉን ያሳተፈ ኢትዮጵያ ለማስመር አንድ ብላቴና ይዋትታል፡፡

ፖሊስ እና አቃቢ ህግ ለህዝብ ከመወገን ይልቅ የገዥ ስልጣን ማስተበቂያ ሆነዋል፡፡ በፖሊሲ ስልጠና ሰበበብ ሙሉ በሙሉ በህወሓት አይዲዎሎጂ የሚመሩ የህዝብ ተቋማት ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም ህወሓት እና እርሱ የሰራው ስርዓትን መተቸት በእንጀራው እንደመጣህበት የሚስብ መርማሪ ፖሊስ፣ አቃቢ ህግ እና ዳኛ ፈጥረዋል፡፡ ለነዚህ ሰዎች የሽማግሌዎቹን ጥቅም የሚያስጠብቀውን ስረዓት መተቸት ማለት ሽብርተኛ፣ ፀረ-ልማት መሆን፣ እንዲሁም ሀገር መካድ ነው፡፡ ሲጀመር እነዚህ ሰዎች በየተቋሞቹ ለህዝብ ሙያዊ አገልግሎት መስጠት ሲጠበቅባቸው፤ ከሙያቸው ይልቅ በአመለካከት (አይዲዎሎጂ) ተመልምለው የበላይ የሆነው ቡድን ስልጣን እና ጥቅም አስጠባቂ ሆነው አገልግለዋል፡፡ የገዥ ቡድን ወንጀልን ሸፍነዋል፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ጥስዋል(ትናንት የተፈታውን ሁለት እግሩን በነሱ ያጣውን ከፍያለውን፣ እንዲሁም ቂሊንጦ የሚገኘውን ዮናስ ጋሻውን ማስታወስ በቂ ነው)፡፡ እነዚህ ተቋት እና ግለሰቦች ከለውጥ ጋር እንዴት ይለወጣሉ ዋናው ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ በሽግግር ወቅት የቀድሞ አለቆቻቸውን ማገልገላቸው የማይቀር ነው፡፡ አሁንም ከህዝብ ይልቅ ለቡድን ጥቅም መቆም ይበልጥ ግላዊ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው የሚያስቡ ብዙዎች ናቸውእና፡፡

የህወሓት ሙጋቤዎች
የኢትዮጵያ ህዝብ ባለማቋረጥ ሲያደርገው የነበረውን ትግል ባለፉት ሶስት አመታት አጠናክሮ በመቀጠሉ ከራሳቸው ስልጣን እና ከኢኮኖሚ ጥቅም ውጭ ምንም የማያሳስባቸው ሽማግሌዎች መንግስታዊ ስልጣኑ ተነጥቋዋል፡፡ ምንም እንኳ ህወሓት በተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ኪሳራ ባጋጠመው ቁጥር የትግራይ ሕዝብ ጉያ ውስጥ እየሮጠ ቢሸሸግም ሽማግሌዎቹ ለትግራይ ህዝብ ቅንጣት ታክል እንደማይጨነቁ ባድመን ላይ የሰሩት ታሪካዊ ሸፍጥ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች ለትግራይ ህዝብ ጥቅም እንደሚሞቱ ቢናገሩም የትግራይ ህዝብ ቋሚ ጥቅሞችን አሳልፈው በተደጋጋሚ ሸጠዋል፡፡ ለመሬቱና ለሉአላዊነቱ ቀናኢ የሆነው የትግራይ ሕዝብን የሚጎዳ ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ዋሽተል፣ ለአስራ ስድስ አመታ ድንበሩ በመዘጋቱ ምክንያት ትግራይ በኢኮኖሚ እንድትጎዳ ሆኗል፡፡ እነርሱ ሳይፈቱ ያሳደሩትን ችግር እንደመነሻ በማድረግ አሁንም የትግራይ ህዝብን በመቀስቀስ ሊጠቀሙበት ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ጩኸታቸው ውስጥ ግን ከስልጣን እና ከጥቅም ገለል ከመደረጋቸው ውስጥ የሚያሳስባቸው የትግራይ ህዝብ ቋሚ እንዳሆነ ያሳብቅባቸዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ ጥቅም የሚከበረው ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እዲሁም ከአካባቢው አገሮች ጋር በሚያደርገው ትስስር እንጅ እነርሱ በሚፈጥሩት ቁርሾ አላስፈላጊ ግጭት በመግባት እና በመቆራረጥ አይደለም፡፡ የትግራይ ሕዝብ የተሻለ አዕምሮ ያላቸው ወጣቶችን እንዳያፈራ በአረጀ አስተሳሰባቸው ብቻ እንዲመራ ተውልድ የማምከን ስራ ለሩብ ምዕተ ዓመት ሰርተዋል፡፡ የተሻለ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶችን አግሏል፣ አሳዷል፣ አስሯል፡፡ ለትግራይ ቀናኢ የሆኑ ልጆች ተፈርጀዋል፣ ከትግራይ ህዝብ ጋር እንዲቆራረጡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ነዝተዋል፡፡ እነርሱ ለሚያልፍ ስልጣናቸው ብቻ ሲሉ የተለያዩ የኢትዮጵያ ህዝቦችን በጠላትነት በመፈረጅ፣ ስም በመስጠት እና በማጥላላት ቋሚ ቁርሾ ለትግራይ ህዝብ አውርሰዋል፡፡ በትግራይ ህዝብ ስም ድርጅት ከፍተው ነግደዋል፣ትርፉን በስጋና በስልጣን ለሚዛመዷቸው ብቻ አካፍለዋል፡፡ በሌላ ኢትዮጵያም ሆነ ትግራይ ውስጥ መሬት ዘርፈዋል፡፡

አነዚሁ ሽማግሌዎች አሁንም በቅልብ ካድሬዎቻቸው በመደገፍ በደል እንደተፈፀመባቸው በተጨማሪም ትግራይ ህዝብ ላይ ችግር እንዳንዣበበ ያስወራሉ፡፡ የሚገርመው እነዚህ ሽግሌዎች ከፌደራል መንግስት ስልጣን ገሸሽ ቢደረጉም አሁንም የህወሓትን ድርጅታዊ የመወሰን አቅም ሙሉ በሙሉ ተቆጠጥረውታል፡፡ ጥቅማችን ተነካ የሚል ድፃቸው በቅርቡ በወጣው የህወሓት ድርጅታዊ መግለጫ ጎልቶ ተሰምቷል፡፡ የትግራይ ህዝብ ሕወሓትን የሚፈልገው ከሆነ ከነዚህ ሽግሌዎች ሊታደረገው ይገባል፡፡ ሙጋቤም እደዚሁ እኔ ከሌለሁ ዚምባብዌ የለችም ይል ነበር፤ ያው ሙጋቤ ሲያልፍ ዚምባብዌ ግን ቀጥላለች፡፡ በዚምባቤዊውያን ላይም ምንም የመጣ ችግር የለም ይልቅስ ብሩህ ቀን ፊታቸው ላይ አለ፡፡

በመጨረሻም
አንዳንዴ በበሽታ (ኢቦላ እና መሰል አደገኛ ተላላፊ በሽዎች) የተለከፈ ሰው በቋሚ ማቆያ ገለል ተደርጎ የሚቀመጠው ጥፋት ስላጠፋ ሳይሆን በሽታው ተዛምቶ በአብዛኛው ሕዝብ ጉዳት እንዳያደርስ እና ኪሳራው እንዳይገዝፍ ነው፡፡ በሽግግር ጊዜ በአንድ ደብዳቤ ከሚሰጥ ስልጣን በላይ ለዘመናት የቆየው የማዘዝ እና የመወሰን ተፅእኖ (ዲ ፋክቶ ሊደርሽፕ የሚሉት) አቅም ሊገዝፍ እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አንድ ተቋም የበላዩ ስለተቀየረ ብቻ አሰራሩና ወገንተኝነቱ ይቀየራል ማለት አይቻልም፡፡ ለመገንባት ጊዜ እንዳስፈለገ ሁሉ ለማፍረስም ሆነ ለማደስ ያንኑ ያክል ባይሆንም አንፃራዊ ጊዜ ያስፈልጋል፡፡

Seyoum Teshome | June 16, 2018
Filed in: Amharic