>

ከመቀሌው ዱለታ በስተጀርባ ያሉ እውነታዎች (ክንፉ አሰፋ)

      የህወሃት መግለጫ በመስመሮች መካከል ሲነበብ በተቀማ ጩኸት ሊመሰል ይችላል።  

         ከመቀሌው ዱለታ በስተጀርባ የነበሩ እውነታዎችን ለመዳሰስ የፖለቲካ ሊቅ መሆንን አይጠይቅም። ህወሃቶች አብረው ወስነው ያስተላለፉትን ጉዳይ እንደመጋዣ አኝከው ሲያበቁ፤ ከብዙ ገጽ የክስ ቻርጅ ጋር ብቅ ብለዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማስጠቆር የሄዱበት ርቀት ግልጽ እና መሳጭ ነው።  ሰማይ ወጥተው ቁልቁል ቢወርዱም ግን ከቶውንም የህዝብ ቀልብ ሊስቡ አይችሉም። እኛ ከሌለን ሃገር ጥጠፋለች ይሉት የነበረው ቁንጽል እሳቤ፤  እነሆ ፉርሽ ሲሆንባቸው፤ አዲስ ካርታ መዘዙ። የአዲሱ ትውልድ መሪዎች፤  ሕዝብን በሃይል ሳይሆን በፍቅር መምራት እንደሚቻል ሲያሳዩዋቸው፣ ወደ ኦሪት ዞር ብለው ከዘፍጥረት መጀመራቸው ይሆን? በአዲሱ ዜማቸው፤  ኢትዮጵያን ትተው ስለ ትግራይ መጮህ የያዙ ይመስላል።  

         “ለነባር አመራሮቻችን እውቅና ይሰጥ” የምትለዋ ሃረግ ግን ብዙዎችን አስደምማለች። እውቅናውስ ይሰጥ። ግን ማን ነው ሰጭው? ዶ/ር አብይ አህመድ ወይንስ የአሜሪካ መንግስት?  

         እውቅና ሲሉስ ምን ማለታቸው ይሆን? ሰዎቹ ያካበቱት እና የተካኑበት ነገር ቢኖር ሱስ እና ዝርፊያ ነው። ለሌብነት የሚሰጥ የስራ ፍቃድ ማለታቸው ይሆን? የቃሉ ሰምና ወርቅ ፍቺ ይህ ከሆነ፤ ጥያቄው በአግባቡ መታየት አለበት። በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አግባብ።

         ሰጭው እና ከልካዩ ዶ/ር አብይ ከሆኑ ግን ለ27 ዓመታት ሳይታክቱ ሃገር በመዝረፍ እና ዜጋን በመግደል፤  ላደረጉት አስተዋጽዖ ከዝምታ ይልቅ እውቅናውን ቢሰጡ ይመረጣል። ጥያቄውን ተቀብለውበአቃቤ ህግ በኩል ቢያሳውቁ፤ ከእንደዚህ ዓይነት ክስ ይድኑ ይሆናል።  

         እጃቸው ላይ በከንቱ የፈሰሰ የንጹሃን ደም እና የሕዝብ ሃብት መያዛቸውን ለአፍታ እንኳ ዘንግተው፤ ለወንጀላቸው እውቅና ሲጠይቁ እፍረት እንኳ አይታይባቸውም። ክብር ለሚገባው ክብር ይሰጠዋል። የዘረፈ እና የገደለ ደግሞ ለፍርድ ይቀርባል።  “ዘመኑ የይቅርታ እና የፍቅር ነው” በሚል እሳቤ ቅሊንጦ እና ዝዋይ የሚገባቸውን ለቦች፤ በማክበር በጡረታ ስለሸኙዋቸው ብቻ መቀለድ ጀመሩ። ግዜውን ሳይዋጁ መቀለድ ደግሞ መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ህጻን ልጅም መገመት አያቅተውም።  

         መንጌ በአንድ ወቅት ካቢኔውን ሰብስቦ፡  “ወደዳችሁም-ጠላችሁም፣ ይህ ሕዝብ የምትነዱትን መኪና፣ የምትኖሩትን ሕይወት፣ የምትኖሩበትን ቤት… ጠንቅቆ ያውቃል” ብሏቸው ነበር።   አንዳንዶችዝቅ ብለው ሌሎች ደግሞነ ከፍ ብለው ይብረሩ እንጂ፤   ከሕዝብ ራዳር ውጭ ያለመሆናቸውን ገና የባነኑ አይመስልም።

         ዛሬ ደርሰው ይህን ሲሉ፤ ይህ ግዜ የሚሉት ተረኛ በማማው ላይ ከፍ አርጎ ስላስቀመጣቸው ብቻ ሕዝብን በጅምላ ናቁት።  ወገንም እያየ እንዳላየ፤ እየሰማ እንዳላዳመጠ እንጂ  የጠጡትን ውስኪ፣የዘረፉትን ዶላር፤ ምን ያህል እንደዘረፉ፣ዶላሩን ያስቀመመጡበት ሃገር ጭምር ያውቃል። ይህ ሕዝብ ግዜ ይሰጠው ቅል አይነት እንዲያው ዝም ይበል እንጂ በነሱ የተገደለን ዜጋ ሁሉ፤  የተሰቃየ እና  እናበግፍ የታሰረውን ሁሉ  በቁጥርም ያውቀዋል። 

         እንደ ሞደል አርሶ አደር “እውቅና ይሰጠን” አሉ። ጥሩ ጥያቄ ነው። ግን ምን አስቸኮላቸው። ግዜው ሲደርስ፤ ሪከርዳቸሁ ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ከፍሪደም ሃውስ ዳታቤዝ ውስጥ እየወጣ እውቅናውን ያከናንባቸው የለ? 

         ጥቂቶች ብቻ ይዘውሩት የነበረ መልህቅ አልባ መርከብ፤ በባሕር ሞገዶችና ከጎን በሚነፍሱ ወጀቦች ክፉኛ ሲወዘወዝ በግልጽ ይታያል። መርህ አልባ ያሉት ጉድኝት፤  ራሳቸውን ቆላልፎ ፍጹምከማይወጡበት ማጥ ቢዶላቸውም፤  ካሁን በኋላ የኋሊዮሽ ሊመለስ ከቶም እንደማይሻ ግን ገና የተረዱት አይመስልም።  

         እርግጥ ነው። ህወሃቶች ተከፋፍለዋል። ስለዚህም ከሕዝብ ጋር በጀመሩት ሌባና ፖሊስ ጫዋታ ብዙ ሊገፉበት አልቻሉም።

         “አውሬውን አቁስለነዋል!” ብለው ነበር ኦቦ ለማ መገርሳ። አውሬው ቲም ለማን መልሶ ለማጥቃት ቁስሉ እስኪሽርለት እንኳን አልጠበቀም። 

         የዘረፋ ቡድን መቀሌ ላይ መሽጎ ሲዶልት የነበረውን ሁሉ አደባባይ አውጥቶታል። በመቀሌው የግንቦት 20 የፓናል ውይይት ላይ ህላዌ ዮሴፍ፣ ጌታቸው ረዳና ስዩም መስፍን የተናገሩት አስደምሞን ሳያበቃ፤ እነሆ “ያሁኑ ይባስ” የሚያስብል መግለጫ ጀባ ብለውናል።  አስቀድሞ በነ ህላዌ ዮሴፍ፤ በነ ስዩም መስፍን ማማሟቂያ ተለቀቀ። ህላዌ ዮሴፍ ቋንቋችንን ተቀማን፤ “ጽንፈኛ፣ ሽብርተኛ፣ አክራሪ፤ ወዘተ” ብለን ለመሳደብ የምንሳቀቅበት ዘመን ደረስን ሲል ነበር ያማረረው። ኢትዮጵያ ብለው ለመጥራት የሚጸየፏትን ሀገር ለሃያ ሰባት ዓመታት መግዛታቸው ሳያንስ፤ ሕዝቧ ላይ ለምን አልተሳለቅንም ሲሉ ቀለዱብን።

         የህወሃቱ መግለጫ፤ በአንድ እጁ ጎራዴ በሌላ እጁ የመላእክትን ሰእል ይዞ እንደሚለምን ተመጽዋች አይነት ነው። በልመና ሃረጎች ታጭቋል። ኢሃዴግ ተሰብስቦ ይምከርም ይላል። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል በተማጽኖ ይጠይቅና እዚያው ላይ የጦርነት ጥሪ ሊያስተላልፍ ይሞክራል።  “የትግራይ ህዝብን ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ያሉት ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሶች ህወሓትከህዝቡ ጋር በመሆን በፅናት ለመታገል ወስኗል።” ይለናል። በእርግጥ ዳጀን ያሉት ትግራይ ሕዝብ  ለነዚህ ቡድኖች የስልጣን ሱስ ብሎ ዳግም ልጆቹን ይገብራል ብለው ማሰባቸው ሕዝቡን መናቅ አይሆንም? ይህንን ሕዝብ ከስንቱ ጋር ሊያጋጩት አቅደው ይሆን?

         በብሄራዊ ቴሌቭዥን ላይ የለቀቁትን ሰበር መግለጫ፤ “አንቺው ታመጭው አንቺው ታሮጪው” ሆነና ግራ አጋባን። ለመሆኑ ህወሃት ስንት ነው? የኢሃዴግ አባል ድርጅት ሆኖ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔያስተላለፈው ህወሃት መቸም  ከማርስ አልመጣም።

         ጫወታው ወዲህ ነው። እነሱ ለመግደል የሞከሩትን ኢትዮጵያዊነት፤ እነሱ ያንቋሸሹትን የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ቲም ለማ ከፍ አድርጎ ሲያነሳ እና ታሪኩን በደማቅ ቀለም ሲጽፍ፤ ፊታቸው ጠቆረ። አይናቸውም ደም ለበሰ። ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢ እያሉ ያሞካሹት የነበረ ስራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የተደራጀ ሌብነት” በሚል አደባባይ ላይ ሲሰጣ አላስደሰታቸውም።  “ልማታዊ መስመራችንከቅርብ ዓመታት ወዲህ አደጋ ውስጥ የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል።” ማለታቸው ይንን ያመላክታል። በሃገሪቱ ብሩህ ነገር መታየቱም አስጨንቋቸዋል፤ አመራሩ ከገዢነው ወደ መሪነት መቀየሩአስደንግጧቸዋል። 

         የህወሃት መግለጫ በዶ/ር አብይ ላይ ብቻ ሳይሆን በሃገር ላይ የታወጀ ጦርነት ነው። ከአስር የማይበልጡ ሌቦች ያወጁት ጦርነት። የፍጻሜ ጦርነት።        

         መግለጫው ሲደመድም፤ “ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።” ይላል።

         ለዚህ ቀደም እንዲህ አይነት መግልጫ እንሰማ የነበረው ከተቃዋሚዎች ነበር። እነሆ ዘመን አልፎ ይህን ለቅሶ ከህወሃት ያስማን ጀመር። ተመስገን ነው።

         የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን አንድ መልካም እድል ገጥሞታል። ህወሃቶች ቢያውቁበት ይህ መልካም እድል እነሱንም ነጻ ያወጣቸው ነበር። ይህንን እድል በሁለት እጃቸው ከመቀበል ይልቅ ሲያጣጥሉት እና ሊያኮላሹ ሲሞክሩ ማየቱ የበለጠ ያሳምማል።  አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል እንዲሉ፤ ይህንን ሕዝብ ባይፈታተኑት የሚበጃቸው ይሆናል።

Filed in: Amharic