>
5:13 pm - Wednesday April 19, 8795

የህዝብ ተሳትፎ የሌለበት ውሳኔ፤ መፍትሄ አያመጣም (ሸንጎ)

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

ሚዳቋ ወዲህ፤ ቅዝምዝም ወዲያ እንዲል ያገራችን ሰው፤ የሰሞኑ የኢሕዴግ መንግስት አካሄድም ከህዝብ ፍላጎትና ከህዝብ ጥያቄ ጎን ሲለካ ወዲያና ወዲህ ሆኖ አግኝተነዋል። ህዝብ የሚጠይቀውና የሚፈልገው አንድ ነገር፤ መንግስት አደርጋለሁ የሚለው ሌላ ነገር። ይህም በተለይ ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ያሰሙትን መግለጫ ይመለከታል።

በርካታው የአገራችን ህዝብ ምንም እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትሩን የውሳኔ አሰጣጥ ስልት ትክክለኛ ነው ብሎ ባይቀበልም፤ የሚያሰሟቸው ንግግሮችና እስካሁን የወሰዷቸው እርምጃዎች፤ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ድጋፍና አድናቆት ሲሰጣቸው ቆይቷል። የተቃዋሚውም ጎራ፤ ሸንጎን ጨምሮ ለፈጸሙት መልካም ድርጊት ሁሉ ድጋፍና ማበረታቻ አልነፈጋችውም። እስካሁን ከተወሰዱት እርምጃዎች፤ ለምሳሌ ታዋቂ እስረኞችን መፍታት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማንሳት ወዘተ… እሰይ የሚያሰኙ ውሳኔዎች ቢሆኑም፤ አሰራሩ በበጎ አድራጊነት መንፈስ ላይ የተቃኘ ሰለሚመሰል፤ የጎደለው ነገር እንዳለ ያሳብቃል። በሌላ አነጋገር በጎ አድራጊው ሰው ወይም ቡድን ከመድረኩ ላይ ዞር ካለ፤ ነገሮች በቅጽበታዊ ፍጥነት ቀድሞ ወደ ነበሩበት ይዞታ እንዳይመለሱ የሚያግዳቸው ስርዓት አልተበጀም ማለት ነው። ያም ሆኖ መልካም ስራ ሁልጊዜም መልካም ነውና፤ በመልክ በመልኩ ሊወደስ ይገባል።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ እንዲያው እንደዋዛ ሰለ አልጄርሱ የድንበር ውሳኔና በመንግስት ቁጥጥር ስር ስለሚገኙ ትልልቅ ኩባንያዎች መሸጥ፤ የኢሕአዴግ አመራር ኮሚቴ ውሳኔ ነው ብለው ያስተላለፉት መግለጫ፤ እስካሁን ስለ እርሳቸው ያለውን የህዝብ እይታ በእጅጉ የሚቀይረው ይሆናል ብለን እንገምታለን። በኛ አስተያየት አሁን፤ ዛሬ በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ሁኔታ ባለመኖሩ፤ ኢሕአዴግ በዚህ ላይ ወደፊት ከመግፋት እንዲያቆም በጥብቅ እናሳስባለን። ከዚህም አስተያየት ላይ እንድንደርስ የገፋፉን በርካታ ምክንያቶች አሉ።

  • ሁለቱም ጉዳዮች እጅግ ግዙፍ የአገር ጉዳዮች በመህናቸው ህዝብ ሊመክርባቸው ስለሚገባ
  • አሁን ያለው መንግስት፤ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የተመረጠ፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎችን ለመውሰድ ውክልና የሌለው በመሆኑ፤ ውሳኔው አዲስ መንግስት እስኪመረጥ መጠበቅ ስላለበት፤
  • በተለይ የድንበሩ ጉዳይ በጣም አወዛጋቢና በርካታ የታሪክ፤ የጂኦግራፊና የባህል ጥያቄዎችን የሚያስነሳ በመሆኑ፤ ሰፋ ያለ ምክክርና ውይይት የሚያስፈልግ በመሆኑ፤
  • ከሁሉም በላይ ግን ያአልጀርሱ ስምምነት ፍትህ የጎደለውና ያኢትዮጵያን ጥቅም የማያሰከብር ስለሆነ ልንቀበለው አይገባም፤
  • ገና ከጅምሩ የህዝብ ንብረት ሆነው የቆዩ፤ አገሪቱን የሚያስጠሩ፤ አትራፊ ኩባንያዎች፤ በከፊልም ሆነ በሙሉ መሸጥ ምናልባት ቢያስፈልግ እንኳን፤ እንዲህ በችኮላ መሆን ስለሌለበት፤
  • በአሁኑ ሰዓት ይሸጡ ቢባል እንኳን፤ ማን ሊገዛቸው እንደሚችል ግልጽ ስለሆነ – ከኢትዮጵያ ህዝብ ሰርቀው ለደለቡ ሌቦች፤ ተጨማሪ የአገር ንብረት በህጋዊ መንገድ መስጠት አግባብ ስለማይሆን፤
  • መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት፤ በሌላ መንገድ ማቃለል ስለሚችል – ሀ/ ሌብነትንና የውስጥ ንቅዘትን በማጽዳት፤ ለ/ ከውጭ ካሉ የኢትዮጵያ ዜጎች ጋር አስቸኳይ እርቅና የተለየ ጥሪ በማድረግ፤

ሸንጎ በተደጋጋሚ እንደጠየቀው ሁሉ አሁንም ደግመን የምንጠይቀው፤ አገሪቱን ወደ ዘላቂ መረጋጋትና ሰላም የሚወስዳት አንድ ሰፊ የአገራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ጉባኤ ጠርቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ማወያየት ሲቻል ነው። በዚህ ላይ ዶክተር አቢይና መንግስታቸው በአፋጣኝ ቢሰሩ ለችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄው እየተገኘ ይሄዳል። ህዝባችንም በአገሩ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ይሆናል።

የህዝብ ተሳትፎ የሌለበት ውሳኔ፤ መፍትሄ አያመጣም !!

የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ያሸንፋል !!

Filed in: Amharic