>

".... በቦንብና በመትረጊየስ ስደበደብ ባደርኩ ስለምን ተከሰስኩ???" ምላሽ ያላገኘ ጥያቄ (ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ)

” ሀምሌ 5/2008 ዓ•ም የተከፈተብኝን ጦርነት ሳስታውስ እከሳለሁ እንጅ እከሰስበታለሁ ብየ አስቤው አላውቅም”ነበር በማለት ተናገረ
“መንግስት አለ በሚባልበት ሀገር በቦንብና በመትረጊየስ ስደበደብ ባደርኩ፣ስለምን ተከሰስኩ”በማለት በሁኔታው መገረሙን ተናግሯል።
ኮሎኔል ደመቀ የመብት ጥያቄን የጠየቀ እና ህገ ወጦችን ከመታገል ባለፈ ንፁህ ሰው መሆኑን በሚከተለው መልኩ ገልጾታል።
“አማራ ነኝ ከማለት ውጭ ምንም ወንጀል የለኝም፣አማራ መሆን ደግሞ ተፈጥሮአዊ ሰጦታየ ነው።እግዚአብሔር የሰጠኝ ነው።አማራ አድርጎ ሰለፈጠረኝ አማራ ነኝ።ዛሬም፣ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ አማራ ነኝ።”ይላል።
ኮሎኔል ሲቀጥልም “ህገ መንግስቱ አማራ ነኝ እንዳልል አይከለክለኝም፣አማራ ነኝ ስላልኩ አሸባሪ የተባልኩ ይሁን እንጅ በፍርድ ቤት ሲታይ ግን የአሸባሪነት ተግባር አልተገኘበትም።
ይህ ትልቅ ስኬት ነው፣እንደኔ ከሆነ አሸባሪ እያሉ የሚያስሩት የነበረውን ሁሉ ህዝብ እውነትም አሸባሪ ማን እንደሆነ ከጉዳዩ እና ከፍርዱ ማየት ይቻላል።
ይህን ጉዳይ ዋጋ ብከፍልበትም በህጉ መሰረት መታየቱ እጅግ ደስተኛ ነኝ።
አሁንም “ለበጎ ነው!” የምለው ብዙ ነገር አስተምሮኛል።እንዴት አድርጎ ወንጀል የሌላቸውን ሰዎችን ታርጋ ለጥፈህ መክሰስ እንደሚቻል እኔ ብቻ ሳልሆን ማንም ህዝብ የተማረበት ነበር።
እና አሁንም ቢሆን ለህጋዊ ነገር ማንም ሰው ሊፈራ አይገባውም።
መታሰር ይኖራል ብለን እኛ መብታችንን ከመጠየቅ መተኛት አይገባም።ትናንት የተኛነባቸው ዓመታት እጅግ ይቆጨናል።
ስለዚህ አሁንም አማራዎች በድፍረት ልንታገል ይገባል፣በድፍረት ስንል ግን ህገ ወጥ የሆነ ነገር ልንደፍር አይገባም።ህጋዊ የሆነ ነገርን ግን ማንም ሊያስፈራራን አይገባም።
የአማራ ማንነት ጥያቄ የት ደረሰ ለሚለው ኮሎኔል ሲመልስ ትግሉ በ2007 ዓ•ም እንቅስቃሴ የነበረው ቢሆንም በዋናነት የጀመረው ግን በ2008 ዓ•ም በመስከረም ወር ነው።
ከዛ በኃላ ጥያቄው ለህዝብ ይፋ ሆኗል።በህገ መንግስቱ መሰረት ክልሉ እንዲያውቀው ሆኗል።የትግራይ ክልልም “የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ አያስፈልገውም ፣የትግራይ ማንነት ተሰጥቶት አድሯል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።በፁሁፍ አልሰጠንም፣በቃል ነበር የሰጠን።
ይህን ቅሬታ ይዘን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሄድን።ብዙ መሰናክል ደርሶብናል።የፖለቲካ ጥያቄ አልነበረም።የነበረው የማንነት የመብት ጥያቄ ነው።አማራዎች ተጎድተናል።ቋንቋችንና ባህላችን ሊከበር አልቻለም።
ህገ መንግስቱ ማንኛውም ህዝብ ባህሉን ፣ቋንቋውንና ባህሉን ማሳደግ ይገባዋል።የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ግን ቋንቋውን፣ ባህሉንና ታሪኩን እንዲጠብቅና እንዲያሳድግ አልተደረገም።ቢያንስ እንኳ ወደ ፈለገው እንዲካለል አልተደረገም።በግድ ነው የተካለለው።
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 46 በህዝብ ፍቃድ መካለል ይገባዋል ይላል።ነገር ግን የወልቃይት ህዝብ ሲካለል በግድ ነው።ትግርኛ ይናገራል በሚል ነው።
የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39(5) የሚለው”አንድ ብሄር የሚባለው ተመሳሳይ ቋንቋ፣ባህል፣ስነ ልቦና፣ጂኦግራፊያዊ የመሬት አቀማመጥና ታሪክ ያለው ህዝብ አንድ ብሔር ይባላል ይላል፣በዚያ መልክ ስንለካው የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ አማራ ነው እንጅ ትግሬ አይመስልም።
ስለዚህ ይህ ከሆነ እኛ ቋንቋችን፣ባህላችን፣ስነ_ልቦናችንና ታሪካችን አማራ ነው፣ከአማራ ጋር የተሳሰረ እንጅ ከትግሬ ጋር የተሳሰረ አይደለም።ወደ ነበርንበት ማህበረሰብ መልሱን ነው ያልነው እንጅ አዲስ ባህልና ማንነት አልጠየቅንም።
ትናንት አማራዎች ነበርን፣ዛሬም ወደ ነበርንበትአማራ መልሱን ነው ያልን።ለምን?ቋንቋችንና ባህላችን እንድናሳድግ።ህገመንግስቱም ስለሚደግፈን የሚል ህጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ ነው የጠየቅነው ።
ይህን ስንጠይቅ መጀመሪያ ብዙ ሰዎች ህወሐት ያጠፋቹሀል፣ይገላቹሀል፣ያፍናቹሀል ብለውን ነበር።
እኛ ያልነው ምንድን ነው?ህወሐት ለህዝቦች እኩልነት፣ለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት ነው የታገለው ፣እውነት ህወሐት ዲሞክራሲያዊ ከሆነ ይህን ህገ መንግስታዊ ጥያቄ ህጋዊ የሆነ መልስ ይሰጣል።
ለህገ መንግስቱ ቆሜያለሁ የሚለው ህወሐት  ግን ለይምሰል ከሆነ የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄን በጉልበት ወይም በአፈና ይመልሰዋል።ስለዚህ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጠያቂዎች ለህወሐት ፈተና ሰጥተነዋል።በሰላም ከመለሰው እውነትም ህወሐት ዲሞክራሲያዊ ነው፣እኛም ሁላችን ታግለንበታል እንኮራበታለን ብለን ተነሳን።
ህወሐትም ሆ የትግራይ መስተዳደር አላለፈም፣ ወድቋል።ወደ ማሰር፣ወደ ማፈን እና  ወደ ማስፈራራት ነው የተሄደው።
Filed in: Amharic