>

ኤፌርትም ሊሸጥ? (ደረጄ ደስታ)

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ቀፍድደው ከያዙት ውስጥ አንዱ የሆነውን ሙስናን በጽኑ ለመዋጋት የሚያስችለውን ስትራቴጂ ይፋ ለማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። ለዚህ ደግሞ እንደሚዲያው የመሳሰሉት ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ ነጻ ለማድረግ መነሳሳታቸውም ተወርቷል። ከሁሉ በላይ ግን ፍጹም ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ በማቋቋም ከሳቸውም ሆነ ከድርጅታቸው ሀሳብ ጋር ተፎካካሪ ሊሆኑ እሚችሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና ግለሰቦችን ለማፍራት ያላቸውን ቁርጠኝነት ደጋገመው ቢናገሩና ቢሰሩበት ለአገራቸው ክልባቸው እሚያስቡና የተሳካላቸው መሪ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል። ዴሞክራሲ ለኢኮኖሚው እድገት ከሚኖረው ፋይዳም ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ትሆናለች። ለዚህ የሳቸውና የደጋፊዎቻቸው ቁርጠኝነት ያስፈልጋል። ሙስናን በማያዳግም ሁኔታ መዋጋት ይኖርብናል ብለው ሲነሱም እነዚህን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል። መቸም በእዳ የተዘፈቀውን በኢንዶውመንት ስም በመንግስት እና በድርጅት ባለቤትነት ስም እሚዋዥቀውንና የሙስናና የባለ ብዙ ብድር እዳ ባለቤት የሆነውን ኤፈርትን አንድ መልክ ለማስያዝ መፈልገን የመሰለ ቁርጠኝነት የለም። እንደተባለው በዚህ መልክ ይዛችሁ መቀጠል አትችሉም ወይ ወዲያ ጆሮውን በሉት ወይም እምታደርጉትን አድርጉት እሚል አቋም ኖሯቸው ከሆነ ግን ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘታቸው አይቀርም። ከፌደራል እየተበደረ ለክልል እሠራለሁ እሚል ወይ ከሥራው ወይ ከብድሩ ያልሆነ አክሳሪ ድርጅት ነው። ያውም ምርጥ ምርጡን እየጎረሰ በሞግዚት የቆመ ግብሩም ስሙም ያላማረ ተቋም ነው። ታዲያ አትራፊዎቹን ድርጅት ልሽጥ ብሎ የተነሳ ድርጅት ይህንንም ነቀርሳ ተቋም አናቱን ብሎ ቢቀውረው ማን ይቃወመዋል? ተቃዋሚ ካለ እዳውን ከፍሎ ይግዛውና ይሞክረው። ላሚቷ እንደሁ በቃኝ አልታለብም ብላ እየነጠፈች ነው።
 
ከዚሁ ርእሰ ጉዳይ ሳንወጣ :-

 የህወሃትን የኢኮኖሚ አከርካሪ የሚሰብር ውሳኔ!!!

(ፋሲል የኔአለም)

የኢኮኖሚ ነጻነትን ከሚደግፉት ሰዎች መካከል ነኝ። በህግና በስርዓት የተመራ፣ ኢፈርት በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የሌለበት፣ የመንግስት ድርጅቶችን በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግለሰቦች የማዞር እንቅስቃሴንም እደግፋለሁ። የውጭ አገር ዜጎች የተገደበ ድርሻ እንዲኖራቸው የማደርግ አሰራር መከተል አዋጪ እንደሆነም አምናለሁ። አገራችን በሂደት ከአለማቀፍ ኢኮኖሚ ጋር የጠበቀ ትስስር እንድትፈጥር የፋይናንሱን ዘርፍ ላላ ማድረጉም ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን ነጻ ኢኮኖሚ በነጻ ፖለቲካ ካልተደገፈ ዋጋ የለውም። እንደ ቻይና ኢኮኖሚውን ከፊል ነጻ አድርጎ ፖለቲካውን አፍኖ መያዝ ዘላቂ እድገት አያመጣም። ፖለቲካውና ኢኮኖሚው እኩል ነጻ ከወጡ አገራችን ተዓምር ትሰራለች፤ አንደኛው ነጻ ወጥቶ ሌላው ተቀፍድዶ የሚያዝ ከሆነ ግን ያው  ከ“ እንዘጭ እንቦጭ” የሚያልፍ አይሆንም። የኢኮኖሚ “ሊበራላይዜሽኑ”ን  ብደግምፍ፣  በፖለቲካ “ሊበራላይዜሽን” ባለመደገፉ ድጋፌን በቅድመ ሁኔታ ላይ እንዳስቀመጥ ተገድጃለሁ። ውሳኔው የህወሃትን የኢኮኖሚ አከርካሪ እንደሚሰብር አምናለሁ፣ ነገር ግን ህወሃት ወይም በአጠቃላይ የኢህአዴግ የንግድ ድርጅቶች እነዚህን የመንግስት ተቋማት በእጅ አዙር እንዳይገዟቸው እሰጋለሁ። ሶቭዬትን ያዬ በእሳት አይጫወትም። ለዚህ ሁሉ መፍትሄው በፍጥነት ሚዲያውን፣ ሲቪል ሶሳይቲውን በአጠቀላይ ፖለቲካውን ነጻ ማድረግ ነው።

Filed in: Amharic