>
5:13 pm - Thursday April 19, 0891

የአገሪቱን የኢኮኖሚ መመሪያ አቅጣጫ ተቀየረ (ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ)

አብነት አጣነው
ባልተልመደ መልኩ ወያኔ/ኢህዴግ ዛሬ የስራ አስክያጅ ኮሚቴ ስብሰባውን ውሎ ይፋ አደረገ – በዚህ መሰረት፡-
– የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ባቡር እና ስኳር ፍብሪካዎች ወደ ግል እንዲዛወሩ
– ኢኮኖሚው ከመንግስት ወደ ግል ንብረትነት እንዲመራ ተወሰነ
ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አደረገአዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን፣ ይህም ዕድገት ከፍተኛ መነቃቃትንና ተነሳሽነትን በመቀስቀስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩን፣ በአንፃሩ ደግሞ በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ያሉ መሆኑን በጥልቀት ገምግሟል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የወጭ ንግድ አፈፃፀም ከታቀደው በታች በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለውን ውስንነት ለመፍታት የግብርናና ኢንዱስትሪ አምራች ዘርፍን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በተለይ የወጭ ምርቶች ላይ መረባረብ እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማስፋት፣ የገቢ መሰብሰብ አቅም ማሳደግ፣ የኑሮ ዉድነት ችግርን ማቃለልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ኮሚቴው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገምግሞ ቀጣይ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በዚህም መሰረት የስካሁኑን ፈጣን ዕድገት ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም በተሻለ የኤክስፖርት አፈፃፀም ለመድገም አሁን ከደረስንበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ አምኖበታል።
በዚህም መሰረት ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን አካታች (inclusive growth) በሆነ መልኩ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው ወስኗል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት በሀገራቸው ልማት ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት በማረጋገጥና የዕድገቱን ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል እንዲሁም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች በዕድገታችን ላይ ተገቢውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል
• በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ፣
• እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግስት ባህሪያት በሚያስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ፤ ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል፡፡
Filed in: Amharic