>

ተቃዋሚ የሚባል የትግሬ ድርጅት አለ ወይ? (ይኄይስ እውነቱ)

በዜግነቴ ስለ አገር ጉዳይ ያገባኛል፣ ያሳስበኛል፤ ደሀ ሲበደል፣ ፍርድ ሲጓደል ያመኛል፤ ስለሆነም ቢያንስ አገርና ወገኔን ለማጥፋት ከተሠማሩ እኩያን ማኅበር ጋር አልተባበረም፤ አቅሜ በፈቀደው ኹሉ ግፍና በደልን እቃወማለሁ፣ እጮኸለሁ፣ ወደ ኢትዮጵያ አምላክም አንጋጥጣለኹ፤ የሚል ዜጋ ኹሉ ፖለቲከኛ ካልተባለ በስተቀር እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ ዝንባሌውም የለኝም፡፡ በአንፃሩም አገር የደናቁርት ሽፍቶች መጫወቻ ስትሆን ዝም ብሎ ማየትም ካለመኖር ልዩነት ያለው አይመስለኝም፡፡ አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቄ (ነፍሳቸውን በመካነ ዕረፍት ያኑርልንና) በእምቅ ፍልስምናዊ ይዘቱ እንደሚያምኑትና እኔም እንደምጋራው ‹‹መኖሬን የማውቀው እምቢ ስል ነው፡፡›› ማለታቸው በአገርም ይሁን በዓለም አቀፉ ሥርዓት ደረጃ ግፍና በደልን ወይም ኢፍትሐዊነትን ከመጸየፍ የመነጨ ጽኑ አቋም ይመስለኛል፡፡

ፖለቲካ የጥበብም (የፍልስምና) የሳይንስም መሠረት ያለው ትልቅ የዕውቀት ዘርፍ (ዲስፕሊን) እንደሆነ ብረዳም፤ በተግባር የአገርን ዕጣ ፈንታ ከመወሰንና መንግሥታዊ ሥልጣን በመያዝ ዓውድ ስናየው በሠለጠኑትም ሆነ ኋላ ቀር በሆኑ አገራት፣ መንግሥታቱ የትኛውም ዓይነት ቅርፅና ስያሜ ይኑራቸው፣ የሚከተሉትም ርዕዮተ ዓለም የትኛውም ዓይነት ይሁን የመጠን/ደረጃ ልዩነት ካልሆነ በቀር ባጠቃላይ አነጋገር በፖለቲካ ‹‹ጨዋታ ደንብ›› መሠረት ከሸፍጥ፣ ከመጠላለፍ፣ ከውሸት የፀዳ የሚባል ፖለቲካ ያለ አይመስለኝም፡፡ የወያኔ ትግሬ የድንቁርና አገዛዝን በዚህ ውስጥ ባላካትተውም፡፡

እኔ እውነት ነው ብዬ የማምንበትን ጉዳይ ስጽፍ÷ ተሐዝቦቴን ሳካፍል አንድ ወገንን ለማስደሰት፣ በይሉኝታ፣ በማስታመም ወይም የፖለቲካ ትክክለኝነት ከሚባለው አስተሳሰብ ጋር አያይዤ አይደለም፡፡ ይህ የኋለኛውን ጉዳይ አስቤበትም አላውቅም፤ ላስብበትም አልፈልግም፡፡ የገባቸው ፖለቲከኞች ካሉ ይጨነቁበት፡፡

በኢትዮጵያ አገራችን ጉዳይ ላይ እንደሚያገባው አንድ ዜጋ – በተለያዩ አገራዊ ርእሰ ጉዳዮች ላይ እውቀቴና ልምዴ በፈቀደልኝ መጠን – ሀ ብዬ መጫጫር ስጀምር በደማቁ እንዳቀለምኩት የጎሣ አስተሳሰብን ሰውነቴም ነፍሴም እጅግ አድርገው ይጸየፉታል፡፡ ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) የምለው ግን እውነት ስለሆነ ነው፡፡ ሌላ ስምም የለውም፡፡ በሎሌነት ያደሩለት ጭፍራዎቹ (አሁን ያፈነገጡትን ጨምሮ) – ፈጣሪያቸው ዳቦ ቆርሶ ያወጣላቸው ስም አላቸው -ወያኔ ትግሬ በፈጸመውና እየፈጸመ ባለው ግዙፍ የሚለው ቃል በማይገልጸው ጥፋት ውስጥ ቀላል የማይባል ድርሻ፣ ኀላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡

በዛሬው ርእሴ ብዙ ማተት ዓለማዬ አይደለም፡፡ ወያኔ በበቀለበት የትግራይ ምድር ከወያኔ አብነት ነስተው ጎሣን መሠረት አድርገው (በዋናነት ትግራዮችን አሰባስበው) የተቋቋሙ ‹ተቃዋሚ› የሚባሉ ድርጅቶች በአገር ውስጥና በውጭም እንዳሉ ይሰማል፡፡ ‹ተቃዋሚ› የሚያሰኛቸው እንኳንስ ለእነዚህ ሌሎቹም በዚህ ስም የሚጠሩ አብዛኞቹ ለእኔ ትርጕም አይሰጡኝም፡፡ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ ላለፉት 27 ዓመታት በአንድ ጉዳይ ላይ እንኳን ኅብረት አጥተው፣ ቁም ነገር ሳይሠሩ (በወያኔ አገዛዝ በኩል ያለው አፈና እንደተጠበቀ ሆኖ) ከወያኔ ጉያ የዶ/ር ዓቢይ ‹አስተዳደር› መምጣቱ ብቻ ብዙ ይናገራል፡፡

የወያኔ ትግሬ አገዛዝን በእውነት የሚቃወም የትግሬ የፖለቲካ ድርጅቶች የሉም ስል ጎልቶ ለምስክር የሚበቃ ነገር ባይታይም በተራው የትግራይ ሕዝብ ውስጥ እና እንደ ግለሰብ ሕወሓትን የሚቃወሙ የሉም ማለቴ አለመሆኑን ግልጽ ማድረግ እፈልጋለኹ፡፡ በስም ደረጃ አረና፣ ዴምሕት ወዘተ. የሚባሉ ቢኖሩም እነዚህ ‹ተቃዋሚ ድርጅቶች› በተግባር ከወያኔ ጋር ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያስተሳስራቸው ጅማት የጠነከረ ይመስለኛል፡፡

1ኛ/ ሁለቱም በጎሣ ተደራጅተው ለትግራይ ሕዝብ ቆመናል የሚሉ ናቸው፡፡

2ኛ/ ወያኔ ላለፉት 27 የግፍ ዓመታት እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያንን ሲገል፣ ሲያስር፣ ሲያፈናቅል፣ ለስደት ሲዳርግ ይህ ነው የሚባል ተከታታይነት ያለው ተቃውሞ ሲያሰሙ አልሰማንም፡፡

3ኛ/ ወያኔ እንደ ባዕድ አገር (ለአስተዳደር ዓላማ ሳይሆን ለጥፋት ተልእኮው) በየቦታው (በጎጃም፣ በወለጋ) የመሬት ወረራ ሲያደርግ፤ በተለይም ለመስፋፋት ብሎም በመክሥተ ደደቢት ላይ ባሠፈረው ‹ታላቋን ትግራይ› የመመሥረት ዓላማ ከሕግና ታሪክ ውጭ የጎንደርንና የወሎን ግዛቶች ቆርሶ በትግራይ ግዛት ውስጥ ሲያጠቃልል አንድም ‹ ተቃዋሚ የትግሬ ድርጅት›  ነኝ የሚል እስካሁን ድምፅ አላሰማም፡፡ እንዲያውም እነዚህ በወረራ በጉልበት የተወሰዱ ግዛቶችን በሚመለከት ጥያቄ ታነሱና እልቂት ነው የሚፈጠረው እያሉ ነጋሪት እስከ መጐሰም ደርሰዋል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ይህ የመሬት ወረራ ጉዳይ ኹሉንም ትግራዮች ለማለት በሚያሰደፍር መልኩ ከወያኔ ጋር አንድ የሚያደርጋቸው አቋም ነው፡፡

    ወያኔ የማንነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ምድር ላይ አሠልጥኖ ‹ክልል› የተባለ አጥር ባያቆም ኖሮ ለዘመናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን (በተለይም የሚጎራበቱ ግዛቶች) ሲያደርጉት እንደኖሩት አንዱ ወደሌላው ሄዶ ኑሮውን መሥርቶ፣ ትዳር ሀብት ንብረት አፍርቶ መቀመጡ እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ይህንን መፋቀር፣ ይህንን መተሳሰብ፣ ይህንን መከባበር፣ ይህንን አብሮነት ነው ከሥሩ ለመንቀል የፈለገው፡፡ በሌላ አነጋገር ከሕዝብ ይልቅ ወያኔም ሆኑ በወረራ በተወሰደው መሬት ላይ የሠፈሩት የትግራይ ተወላጆች የመረጡት መሬቱን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም በየቦታው የተደረጉ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎች ደጋፊ የሆኑ ትግሬዎች ኹሉ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በአብሮነት ለመዝለቅ እንደማይፈልጉ ከሚያሳይ በቀር ሌላ ትርጕም ለመስጠት ቸግሮኛል፡፡

4ኛ/ ከራሳቸው አብራክ የወጣው ወያኔ ዓይን ባወጣ መልኩ በሁሉም መስኮች (በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊ፣ በደኅንነቱ፣ በብዙኃን መገናኛው፣ በመንግሥታዊ መዋቅሮች በሙሉ ወዘተ.) የትግራዮችን የበላይነት ማንገሥ የአደባባይ ምሥጢር ሆኖ እያለ፤ ትርጕም የሌለው ክርክር ውስጥ (ኹሉም ትግሬ ተጠቅሟል/አልተጠቀመም) ከመግባት ትክክል አይደለም ከቀሪው ወገናችን ጋር ያጣላናል/በጠላትነት ዓይን እንድንታይ ያደርገናል፣ በማለት ለትግራይ ሕዝብ በመደበኛና ተከታታይነት ባለው መልኩ መልእክት አስተላልፈዋል ወይ ለሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ማግኘት አይቻልም፡፡

ዝርዝሩን መቀጠል ቢቻልም፣ ለአሁኑ አስተያየት የጋበዘኝ ሁኔታ እነዚህ በስም የወያኔ ‹ተቃዋሚ የትግሬ ድርጅቶች› የኢትዮጵያን ሕዝብ ግፍና በደል ዝም ብሎ መመልከቱ ሳያንሳቸው መደንፋት መጀመራቸው ድንቁርናውን፣ በጉልበት ማምለኩንና ትእቢቱን ከሕወሓት ጋር እንደሚጋሩት ያሳብቅባቸዋል፡፡

Filed in: Amharic