>
5:13 pm - Tuesday April 19, 4416

ኦቦ በቀለ ገርባ ምን ተናገረ፤ ሳይሆን ለምን ተናገረ የሚለዉ ትኩረት ይሻል!! (ሃራ አብዲ)

ያንዱ እለት፤ አንዱ ባልቴት።

ኦቦ በቀለ ገርባ ምን ተናገረ፤ ሳይሆን ለምን ተናገረ የሚለዉ ትኩረት ይሻል !!

ሃራ አብዲ

ይህችን ሁለት ቀናት ደግሞ ሌላ አተካሮ የሚጋብዝ ነገር አግኝተናል። ታዋቂዉ ፖለቲከኛ ኦቦ በቀለ ገርባ ተናገረ በተባለዉ ንግግር ሳቢያ አንዳንዱ በግላጭ «ምቀኝነት ይመስላልl» (ስዩም ተሾመ) ብሎ ሲኮንን  ሌላዉ ደግሞ፤ «ጥፋታቸዉ ምንድን ነዉ? አቶ በቀለ ከቆሙለት አመለካከት አንፃር የተሳሳቱ አይመስለኝም» (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት) ሲል በዉስጠ-ወይራ ይሸረድዳል።

ከላይ ለአብነት ያህል የጠቀስኩዋቸዉ የማከብራቸዉ ወገኖቼ ከእኔና ከአብዛኛዉ ordinary ዜጋ በተሻለ ሁኔታ የፖለቲካችንን ትኩሳት እንደሚያዉቁት ጥርጥር የለኝም። ይሁን እንጂ፤ ኦቦ በቀለ ለምን ይሆን እንዲህ ለማለት የበቃዉ? ብሎ ማሰብ ተቻችሎ ትግሉን ወደፊት ለመግፋት ይበጅ ይመስለኛል በማለት ነዉ ሃሳቤን ጣል ለማድረግ የዳዳሁት።

ወዲሁም፤ የፖለቲካ ትክክለኝነት(political correcetness) እንደካባ መደረብ ብቻዉን የነጠረ ፖለቲከኛ አያደርግም።

እንዲያ ቢሆን ኖሮ ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት መሆን ቀርቶ አያልመዉም ነበር።

ሶስተኛዉ ወገን እንዲሁ፤ በህወሃት የተቀነባበረ ሴራ ነዉ ሲል ተደምጦአል። እዚህ ላይ፤ ይህ ትክክል ነዉ ፤አይደለም ወደሚለዉ አልገባም። የሚሰማኝ ግን እንደዚህ ነዉ።

ኦቦ በቀለ ገርባ በሀገራችን እና በህዝባችን ላይ ተጣብቆ አልላቀቅ ያለዉን መዥገር፤ (ህወሃት)  ለማስወገድ በሚደረገዉ ትንቅንቅ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለና በመክፈል ላይ የሚገኝ ጀግናችን ነዉ። አሁን ያንን ተናገረ ተብሎ ያደረገዉን መስዋእትነት ለማጣጣል መሞከር ክቦ እንደ ማፍረስ ይሆናል። በኔ ግምት ያቅሙን የወረወረ ሁሉ ፈሪ አይባልም ። ከዚያም ላቅ ሲል እዚያቹ መከረኛ ሀገራችን ዉስጥ እየኖሩ፤ ለማናቸዉም የህወሃት ወከባ፤እስራት ፤ግርፋት እና ሞት ተጋልጠዉ የመጣዉን እንቀበላለን ብለዉ ሲታገሉና ህዝባቸዉን ሲያታግሉ ያሉ  እንደ በቀለ ገርባ አይነት ብርቅዬ የሀገራችን ልጆች በእጅጉ ክብር ይገባቸዋል። ኦቦ በቀለ ገርባ ለተምሳሌት ስማቸዉ በታሪክ ማህደር ከሚቀመጡት መካከል አንዱ ነዉ።

በሌላዉ በኩል ደግሞ፤ ህወሀት፤ በሰላም በሚደረግ ትግል አንድ ኢንች ፈቀቅ እንደማይል አይተዉ፤ መዝነዉ፤ ቤት ንብረታቸዉን ትተዉ፤ ልጆቻቸዉን ሳያሳድጉ፤ ሞቴም ሽረቴም ከሀገሬ ነጻነት ጋር ይሁን ብለዉ በረሀ የገቡ እንደ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ያሉ፤ የስስት ዜጎች አሉን። በእነዚህ ሁለት የትግል ስልት ታጋዮች መካከል ያለዉ የትግል ልዩነትና የመስዋእትነት ልኬታ፤ የአይነት እንጂ የጥራት አይደለም። ስለዚህ የማን መስዋእትነት ይበልጣል ወደሚለዉ አንግባ።

ይህን መሰረት አድርጌ በቀለ ገርባ ምን ያህል ቢገፋ ነዉ? እንዲያ ለማለት የበቃዉ ብዬ ሳስብ ልቤ ይራራለታል።

( do not get me wrong, አንዳርጋቸዉም እኩል የምራራለት ጀግና በመሆኑ «

አንዳርጋቸዉን ፍቺዉ!!  ጦቢያ ተለመኚኝ» የሚለዉን ስነግጥም ስጽፍ እንባ እየተናነቀኝ ነበር)።

እርግጥ ነዉ የቁቤ ትዉልድ ባለመሆኔ የኦሮምኛዉ ትርጉም በትክክል ወረቀት መንከሱን ማጣራት ባልችልም፤ አልፎ አልፎ እንደገባኝ ከሆነ ጋሽ በቀለ በመከፋት ስሜት ትንሽ መረር አድርጎ እንደተናገረ ተረድቻለሁ። አንድ ነገር ከልቤ የማምነዉ ነገር ቢኖር ግን፤ በአንዳርጋቸዉ መፈታት ጋሽ በቀለ ሀሴት ማድረጉን ነዉ። ይህን የምልበት ምክንያትም፤ በቀለ ገርባና አንዳርጋቸዉ ጽጌ፤ የኢትዮጵያን ቀንደኛ ጠላት ህወሃትን ከስልጣን ተወግዶ እኩልነትና ዲማክራሲ የሰፈነባትን ዉድ ኢትዮጵያ ለመገንባት በአመኑበት መስክ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉና ወደፊትም የሚያደርጉ በመሆናቸዉ፣ ይህ የጋራ አላማ ብቻዉንና፤ ብቻዉን የአንዱ ነጻነት የሌላዉ ነጻነት እንዲያስፈነድቀዉ ስለሚያደርግ ነዉ።

ይሁን እዉነተ-ሃሳብ ከመሰረትን ዘንዳ፤ ስለምን ጋሽ በቀለ ከፋዉ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።

አንዱ ምክንያቱም ሰዉ መሆኑ ነዉ።

ኦቦ በቀለ አሜሪካን ሀገር ደማቅ አቀባበል ሊደረግለት ሲታሰብ ምናልባትም ህወሃት የማይቀበለዉን ባንዲራ ይዘዉ በሚመጡ ተቀባዮች መሀል መገኘቱ መንግስትን  (ወያኔን) ያስከፋ ይሆናል፤ብሎ ሰግቶ ያንን የመሰለ አቀባበል እንዳልፈለገ በሚዲያ የተንሸራሸረ ጉዳይ ነዉ። ሀገሩ ተመልሶ ሰላማዊ ትግሉን ከመቀጠል ምንም ነገር እንዲያናጥበዉ እንዳልፈለገ በዚህ እንረዳለን። ይህ ብቻም ሳይሆን፤ ኦቦ በቀለ ዘመዱቹን ለማየት ከአዲስ አበባ መዉጣትን የተከለከለ ነጻ እስረኛ ነዉ!!

ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ምሳሌዎች የሚያሳዩት፤ ምን ያህል ከሀገሪቱ ህግ ዉጭ መንቀሳቀስ እንደማይፈልግና ለህጉ (ምንም እንኳን የወያኔን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ህግ መሆኑን ቢያዉቅም) በመገዛት ትግሉን መቀጠል እንደሚፈልግና ለራሱ ክብርና አጀብ ማብዛት እንዳልፈለገ ያሳያል። ይህ የግል ህይወቱን የሚመለከት ሲሆን የግሌን እይታ ማካፈሌ እንጂ ኦቦ በቀለ፤ ለንግግሩ መሰረት ያደረገዉ የግል ብሶቱን ነዉ ለማለት አይደለም። ሰፋ ያለዉን ሁነት ስንመለከት ደግሞ፤ አሁንም በሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች በፖለቲካ ምክንያት በእስር መሰቃየታቸዉና በሰላማዊ መንገድ መታገል ገና መራራ መስዋእትነት እያስከፈለን እንደሚገኝ እናያለን። በግልባጩ፤ በጸረ-ሽብር ወያኔ የከሰሳቸዉ አክቲቪስቶች ይሁኑ፤ የሚዲያ ተቁዋማት ፤ክሳቸዉ እየተሰረዘ ወደ ሀገር እንዲገቡ ሲደረግ፤ ለገቡትም ጉንጉን አበባ ሲበረከት፤ ማስተዋል የት ሄደ? ያስብላል። በዚህ ግርምቢጡ በወጣዉ አድሎአዊ አያያዝ ተበሳጭቼ አልናገርም የሚል ቢኖር፤ ያንዱ እለት ሌላዉ ባልቴት የሚባለዉ እሱ ነዉ። (ሚዛናዊነቱን ለማሳየት እንጂ፤ እኔ ብሆን ደግሞ አበባ ብቻ ሳይሆን ፍሪዳም እጥልላቸዉ እንደነበረ ይታወቅልኝ)

እናም፤ የኦቦ በቀለ ንግግር ዉስጡን ገልጠዉ ሲያዩት ንግግሩ ጣት የሚጠቁመዉ ወደ አንዳርጋቸዉ ሳይሆን ወደ ህወሃት ሆኖ እናገኘዋለን። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት ፤በእስር የሚማቅቁ ፤ ነጻ የወጡትም ነጻ የማይወጡ ከሆነና፣ በትጥቅ ትግል የሚፋለሙት የተሻለ ቅቡልነት አግኝተዉ ፤ቤተ- መንግስት ለዉይይት ተጋብዘዉ፤ ከ ጠ/ሚ/ር ጋርም ፎቶ የሚነሱ ከሆነ ፤ እቅፍ አበባም የሚጠልቅላቸዉ ከሆነ፤  የወደፊቱ የትግል አቅጣጫም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን የማያካትት ከሆነ፤ሰላማዊ ትግል ባፍንጫዬ ይዉጣ፤ የሚል መልእክት ያለዉ እንደሆነ ዉስጤ ይጠረጥራል።

ለዚህም ይመስለኛል ኦቦ በቀለ ገርባ ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳለን ሀቁን እንደእንቁላል እምቦጭ ያደረገዉ።

«ራሷን ለነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማዘጋጀት ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ለመበተን እና ለመጥፋት ራሷን ታዘጋጅ» ሲሉ አስጠንቅቀዋል። –(ethioreference ላይ እንደቀረበዉ)።

በማጠቃለያዉ፤ ኦቦ በቀለ ለምን ያንን እንደተናገረ እስከምንሰማ ድረስ በማስተዋል እንጠብቅ። ንግግሩ የቅናት ይመስላል የሚሉ ቢኖሩም መንፈሳዊ ቅናት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።በ political correcetness ጥፋተኛነቱ ከተረጋገጠም በግሌ ይቅር ብየዋለሁ። ይህ ከጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ የተማርኩት ነዉ። «እኔ እያለሁ ምንም አትሆኑም ብያቸዋለሁ» ብሎ የለም?

ይህ እንኳን አዮ ሌላ ወየዉ ሌላ ነዉ አይደል? እንዲያዉ ለማጣፈጫነት የቀረበ።

Filed in: Amharic