>

ከዚህ ደርሰናል፣ ቀጥሎስ? (ሸንጎ)

 ግንቦት 28 ቀን 

የአገራችንን ሕዝብ ከሚያስከብሩት ባህሪያት አንዱ የሚያስደንቅ፣ አንዳንዴም እልህ የሚያጨርስ እርጋታው ነው። ይህንንም ገፀ-ባህሪ በዘፈኖቹ፣ ውብና ድንቅ በሆኑ ተረቶቹና አባባሎቹ እየቋጠረ ለትውልድ ሲያስተላልፍ ቆይቷል። ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ ባደረጓቸው ንግግሮችና በወሰዷችው እርምጃዎች የተማረከ፣ በርካታ የአገራችን ሕዝብ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት እርጋታ በተላበሰ መልኩ እስቲ እንያቸው የሚል ወደ ድጋፍ ያዘመመ አቋም ይዞ ሰንብቷል። በሌላ በኩል ደግሞ አናሳ ድምፆች አሁን የተያዘውን የለውጥ ሂደት በጥርጣሬ ዓይን የሚመለከቱ ክርክሮች ሲያሰሙ ተደምጧል።

ካለፈው ሣምንት ጀምሮ ከዶክተር አብይ መንግሥት በኩል የሚወርዱ ዜናዎች፣ እስካሁን በቃላት ብቻ ሲገለጽ የሰነበተውን የለውጥ አቅጣጫ በተግባር የሚተረጉሙ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን ያበስራሉ። ከነዚህ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት የተላለፈው ውሳኔ፣ እነ አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞችን መልቀቅ፣ ታዋቂ ፖለቲከኞችን ከሽብርተኞች ስም ዝርዝር መሰረዝ፣ የሽብርተኛ አዋጅ የተባለውን ድንጋጌ ለማሻሻል የተወሰደው እርምጃ ወዘተ.. ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የጦር ኃይል መሪዎችን ሰብስበው፣ ጦሩ ብሄራዊና ሙያተኛ ጦር መሆን እንደሚገባው ያስተላለፉት መመሪያ የሚደገፍ ነው።   ሸንጎ እስካሁን የተወሰዱትን እርምጃዎች በአዎንታዊ መልክ እንደሚመለከታቸው እየገለጽን ወደፊትም አገሪቱንና ሕዝቡን ወጥረው የያዙ አፋኝ ህጎች በሙሉ እንዲሰረዙ ለሚደረገው ጥረትና ሌሎችም በሀገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚረዱ፣ የሕዝባችንን ጥቅም የሚያስጠብቁና መብቱን የሚያስከብሩ እርምጃዎች በተወሰዱ ቁጥር በአወንታዊና መልክ እንደምንቀበላቸውና ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያሸጋግሩ የሚረዱ እርምጃዎች በመሆናቸው የምንደግፋቸው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

እነዚህ በቅርብ ጊዜ የተወሰዱ እርምጃዎች፤ ተስፋ ሰንቆ ለቆየው ሕዝብ ተጨማሪ መተማመኛና ጉልበት ከመሆናቸውም ባሻገር የተጠራጣሪዎችንም ልብ የሚያረጋጉ ክስተቶች እንደሚሆኑ አያከራክርም። ይህ ሁኔታ በለውጥ ፈላጊው ጎራ ውስጥ ውህደት፣ ስምምነት ብሎም ኃይልና ጥንካሬ የሚፈጥረውን ያህል፣ በለውጥ አጋች ቡድን ውስጥ ደግሞ ፍርሃትና ሽብር እንደሚፈጥርም ሰሞኑን በገሃድ መታየት ጀምሯል። አሁን ባለው መንግሥት ውስጥ በለውጥ ፈላጊዎችና በለውጥ አጋቾች መካከል ትግልና መተናነቅ በግልጽ እየተጋጋመ ነው። ከዚህ ቀደም እንደነበረው ለማስመሰል የሚደረግ ሽኩቻ ነው በሎ መገመት ትልቅ ስህተት ነው። በዚህ ትግል ውስጥ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሕዝቡ ሚናቸውን መለየት ይኖርባቸዋል። ሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ከለውጥ ፈላጊዎች ጋር ተሰልፎ እስካሁን የተገኙትን ድሎች በመጠቀም የሥርዓት ለውጥ  ለማምጣት ሕዝባዊ ትግሉን ማስቀጠል የግድ ነው።፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ በአገዛዙና ከአገዛዙ ውጪ ያለው የለውጥ ፈላጊ ኃይል ተባብሮ የሚገፋ ካልሆነ የለውጡ ሂደት እንዳይናገፍ እንሰጋለን።

ከላይ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የዶክተር አብይ መንግሥት ብሄራዊ መግባባትንና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ደረጃ እስካሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎችን እንዲመልስ አበክረን እንጠይቃለን። ከነዚህም ውስጥ እጅግ አጣዳፊ ናቸው ብለን የምናምንባቸው፦

  • ብሄራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ፤ በመንግሥትና በተፎካካሪ ኃይሎች መከከል ጉባዔ አድርጎ ዋና ዋና የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት እርምጃ መውሰድ፣
  • በውጭ አገር ለሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራቸው ውስጥ ገብተው ለመንቀሳቀእንዲችሉ የደህንነት ዋስትና የሚሰጥ ህግ ማወጅ፣  
  • ፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በሙሉ በአንድ አዋጅ መልቀቅ፣ መዳረሻቸው የጠፋ እስረኞችን መኖር/መሞት ማሳወቅ፣
  • በሲቪክ ድርጅቶችና በነፃ ፕሬስ ላይ የተጫኑ አፋኝ ህጎችን ማንሳት የሚሉት ናቸው።

ዜጎች ሁሉ የተገኙትን ድሎች እየተንከባከቡ፤ ለበለጠ ለውጥ ተግተው ይሠራሉ!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ይቀጥላል!

Filed in: Amharic