>

"ቂም እና ጥላቻ የበቀል ስሜትን ይወልዳሉ፤ ለበቀል የተዘጋጀ አዕምሮ ደግሞ ለይቅርታ ቦታ የለውም!!!" (አንዱአለም አራጌ)

 
ያሬድ ይልማ
ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ አቶ አንዱአለም አራጌ ድልድይ የኢትዮጵያዊያን የውይይት መድረክ በአውሮፓ ባደረገለት ጥሪ ወደ ብራስልስ ብቅ ብሎ ነበር። በአካባቤው ከሚገጉ ኢትዮጵያዊያን ጋርም የግማሽ ቀን ውይይት አድጓል። የአንዱአለምን ስብዕና፣ በሳልነት እና አዋቂነቱን እንዲህ ባለ አጭር ማስታወሻ ማስፈር አይቻልም። ለሁለት ቀናት በግልም ሆነ በአደባባይ በነበረው ውይይታችን እያንዳንዱ ከአፉ የሚወጣው ቃል፣ በውስጡ የሚታይበት የመንፈስ መረጋጋት፣ የሞራል ልዕልና እና ስክነት እራሴን እንድታዘብ አድርጎኛል። አንዱአለም በአገዛዝ ሥርዓቱ እጅ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ያሳለፈውን ሰቆቃ እና መከራ እሱ በአንደበቱ ባይናገረውም ተክለ ሰውነቱ ያሳብቅበታል። ኢትዮጵያ በምን አይነት ግፈኞች እጅ እንደወደቀች ማሳያ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዱአለም በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው። ይሁንና በግፈኞቹ የተፈጸሙበትን አሰቃቂ ድርጊቶች በየትኛውም መድረክ አውጥቶ ላለመናገር እራሱን አሳምኗል። ይህን የሚያደርገው ግን በፍርሃት ተውጦ ወይም ግፍ ፈጻሚዎቹ ከተጠያቂነት ነጻ እንዲሆኑ በማሰብ አይደለም። ከራሱ አንደበት እንደሰማሁት የተፈጸሙበትን በደሎች እያነሳ ለሕዝብ የማይናገረው ቂምን እና ጥላቻን ላለማውረስ በማሰብ ነው።
ቂም እና ጥላቻ የበቀል ስሜትን ይወልዳሉ። ለበቀል የተዘጋጀ አዕምሮ ደግሞ ለይቅርታ ቦታ የለውም። እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን በተለይም የአገዛዙን በትር ሸሽትን በብዙ ሺ ማይልስ እርቀት ላይ የምንገኝ ሰዎች አንዱአለም አራጌ ያሳለፈውን መከራ የሩቡን እሩብ እንኳን ያላየን ነገር ግን ጭንቅላታችን በጥላቻ እና በበቀል ስሜት ተወጥሮ እርስ በእርስ ስንገፋፋ የምንውል ነን። ይህን ሁሉ መከራ ያሳለፈው አንዱአለም ግን ወደ ኋላው ተመልሶ ላለማየት ወስኗል። ገራፊዎቹ የፈጸሙበትን በደል እያሰላሰለ ዛሬንም በመንፈስ ስቃይ ውስጥ ሆኖ እየማቀቀ ላለማሳለፍ ወስኗል። ገራፊዎቹን እንደ ጠላት ወይም ጭራቅ ሳይሆን የአስተሳሰብ ችግር እንደገጠማቸውና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ሰዎች አድሮጎ ነው የሚቆጥራቸው። እራሱን በመንፈሳዊ ሕይወት አንጾ እና ተመሳሳይ መከራ ያሳለፉትን እንደ እነ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ማህተመ ጋንዲን ምሳሌ እያደረገ ፍቅርን እና ይቅር ባይነትን ይሰብካል። በዳዮቻችንን ይቅር እንድንል አበክሮ ይማጸናል። የበዳይና ተበዳይ፤ የግፈኞችና ግፉዋን ግንኙነት በይቅርታ ሽሮ ግፍ ታሪክ ሆኖ እንዲቀርም ዛሬም ይታገላል።
እንግዲህ ስለ እርቅ፣ ስለ ይቅር ባይነት፣ ስለ ፍቅር፣ ሰለ ሰላማዊ ትግል እና ጽናት ለመማር እና በጥላቻ የተሞላ ልቡን ለማጽዳት የሚፈልግ ሁሉ አቶ አበራ የማነአብን፣ እስክንድርን ነጋን እና አንዷለም አራጌን ማድመጥ ግድ ይለዋል። በደልን በይቅርታ ማሸነፍ እንደሚቻል የቁም ምስክሮቻችን ናቸው።
Filed in: Amharic