>

በ‹‹ምርኮኛ›› እና ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› ውስጥ... !!! (አስፋ ሀይሉ)

‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› በቅርብ ቀን ያገኘሁት መጽሐፍ ርዕስ ነው፡፡ ነገር ግን ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› በሚያዝያ ወር 2010 ዓመተ ምህረት በፋር ኢስት ትሬዲንግ እንደታተመ ይናገራል፡፡ መፅሐፉ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ የአንዲት ሴት የህይወት ታሪክ ነው፡፡ ‹‹ንፁህ›› የተባለች አስደማሚ ሴት ህይወት ታሪክ ነው — ‹‹ያላረፉ ነፍሶች››፡፡ ደራሲዋን ከዚህ ቀደምም ‹‹ምርኮኛ›› በሚል እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመረኮዘ — እና ተመሣሣይ መቼትና ባለታሪኮች ባሉት — እና ስምንት ጊዜ ተደጋግሞ እንደታተመ በሰማሁት — እጅግ ድንቅ ድርሰቷ አውቃታለሁ፡፡  ቆንጂት ብርሃን ትባላለች ደራሲዋ፡፡ ወይዘሮ ቆንጂት ብርሃን፡፡ ለዚህኛው ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› መጽሐፏ —የደራሲ እናቱን መጽሐፍ ታሪክ በሚገባ ይገልጽልኛል ያለውን ምስል — በትክክል ከድርሰቱ ታሪክ ጋር እንዲሰናሰል አድርጎ የመፅሐፉን የሽፋን ዲዛይን የሠራላት — የዚህችው ደራሲ የቆንጂት ብርሃን ወንድ ልጅ — ‹‹ዮሐንስ ሠረቀ›› እንደሆነ በመጽሐፉ የውስጥ ገጽ ሰፍሮ ሳገኝ እጅግ ተደመምኩ፡፡
የደራሲዋ ዋና ባለታሪክ በቀደመው መጽሐፏ በ‹‹ምርኮኛ›› ፍሬህይወት የተሰኘች — በ60ዎቹ ዘመን አፍላ ወጣት የኖረች — እና ታላቅን አስገራሚ የፅናት ሕይወት የኖረች — እጅግ አስደማሚ አይበገሬ ባህርየ-ሰብዕ ነበረች፡፡ በምርኮኛ ላይ ያለችው ፍሬህይወትም ምኑንም ሳታውቀው ከት/ቤት ግርግርና የወጣቶች የፖለቲካ ዲስኩር ጀምራ — ቀስ በቀስ ወደ ዘመኑ የኢህአፓ ፖለቲካ የተሳበች — ብሎም በወቅቱ የኢህአፓ ወጣቶች ታላቅ ተጋድሎ ላይ — በሚያስገርም ፍቅር፣ የሀገር ፍቅርና በሚያስገርም መስዋዕትነት — ያለመቻትን መልካሚቱን ኢትዮጵያ ለማምጣት የተሟሟተች ምስኪን፣ ቆንጆ፣ እና አሳዛኝ ገጸ ባህርይ ነበረች — ፍሬህይወት፡፡ የምርኮኛዋ ፍሬህይወት የኢህአፓ ወጣቶች በአደባባይና በማዕከላዊ ሲጨፈጨፉና ሲገረፉ አብራ የግፍ መከራን የተቀበለች፣ ብዙዎቹን ውዶቿን ያጣች፣ በፍፁምና በምንም ሊተካ የማይችልን ባዶ የሰቀቀን ህይወት ከነሃዘኑና ተስፋው ተሸክማ የምትኖር — እና እስከመጨረሻው ታግላ ከናሳደገቻቸው — ሁለት ልጆቿ የምናገኛት — እጅግ አሳዛኝም፣ እጅግ ፅኑም፣ እጅግ እንደ እህት ቀርበህ ስታያት የምትሳሳላት ጠንካራ ሴት ነበረች — የ‹‹ምርኮኛ›› መፅሐፏ ገጸ ባህርይ — ፍሬህይወት፡፡
በአሁኑ ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› ደግሞ — በአሁኑ ደግሞ ደራሲዋ ይዛ የመጣቻትም ዋና ባለታሪክ ሴት — ንፁህ — ይህች ንፁህ ደግሞ — ከዚያችኛዋ በምርኮኛ መጽሐፏ አሳምሬ ከማውቃት ከፍሬህይወት ጋር — አንድ ሆነችብኝ፡፡ አንድ ሲባል ግን — ለየት ያለውን — ቀድሞ በምርኮኛ ውስጥ ያላየነውን — በደንብ ገልጣ ያላሳየችውን — ሌላ እሷን ሆና ነው ብቅ ያለችው ንፁህ፡፡ ንፁህም እንደ ፍሬህይወት ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከአራት ኪሎ እስከ ግቢ-ገብርዔል — ከባህታ እስከ ቅዱስ ጊዮርጊስ — ከጉለሌ እስከ ሰንጋተራ — ከቅዱስ እስጢፋኖስ እስከ ሩፋኤል — ከቄራ እስከ ላንቻ — ከዝዋይ እስከ ሻሸመኔ (ፍሬ ግን አዋሣን ነበር የረገጠችው – በዝዋይና ሻሸመኔ አልፋ) — ሁሉንም ስፍራ እያዞረች  — የንፁኋን ኢትዮጵያዊት ቆንጆ — የንፁህን — እና የእልፍ አዕላፍ የ60ዎቹን ኢትዮጵያውያን ጉዞ — ቀስ አድርጋ አብራን ‹‹ዎክ›› እያደረገች — ታሳየናለች፣ ታወጋናለች፣ ታንሾካሹክልናለች — ከፍስሃ ስብሃቱም፣ ከባህል ትውፊቱም፣ ከሰቆቃውም፣ ከመከራውም፣ ከሁሉም ስብሃት ስብሃቱን ፉት እንድንል እየጋበዘችን — በንፅሂቷ ኢትዮጵያዊት ወጣት ንፁህ አዕምሮና ስሜት ውስጥ ጨምራን፡፡
እና ልክ ይህን ባለ 398 ገጽ መጽሐፍ — ‹‹ያላረፉ ነፍሶች››ን — አፍታም የቆየህ ሳይመስልህ ከጨረስከው በኋላ — በቃ — ራሷኑ ንፁህን — ከነእናቷ፣ ከነልጆቿ፣ ከነፍቅሯ፣ ከናጣቻቸውና ከነተረፏት ውዶቿ፣ ከነትውልዶቿ፣ ከነ ሙሉ ውበቷ — በቃ — ልክ አብረሃት የኖርክ ያህል ሆና — በውስጥህ በአካል በአምሳል በግዙፉ ተተክላ ትቀርብሃለች፡፡ እና እሷን ንጼን ከማወቅ አልፈህ — ከሌላ ከምታውቀው ሰው ጋር ሁሉ ታመሳስላታለህ፡፡ በበኩሌ ገና እንዳየኋ ያመሳሰልኳት — እና በደንብ ካወቅኳትም በኋላ ሁለነገሯ ቁርጥ አንድ የሆነብኝ አንዲት ሌላ ሴት ብቻ አለች፡፡ ይህችን ንፁህን የመሠሉ እልፍ ጀግኖችን ያፈራች፣ እልፍ ውቦችን፣ እልፍ ፅኑዎችን ያፈራች ሃገር አለችን፡፡ ያ ያኮራል፡፡ ግን ደግሞ አንዱ ሰው ከሌላው ሰው በመልኩም፣ በባህርዩም፣ በቅጽበቱና በፍፃሜውም ይለያያል አይደል? — አዎ፡፡ እና ለእኔ — ይህችን ንፁህን ቁርጥ በአካል-በአምሳል የምትመስላት ሴት — በዓለም ላይ ተፈልጋ — ምናልባት የምናገኛት አንድ ሌላ ሥፍራ ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህች ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› ውስጥ ደግማ ነፍስ የዘራችው ‹‹ንፁህ›› የምትሰኘው ውብ የዘመነ-ኢህአፓ አይበገሬ ገጸባህርያዊ ሴትን የምትመስል — ቁርጥ ሌላ የማውቃት ሴት ያለችበት አንድ ሠፈር አለ፡— የዚህችው ደራሲ የቆንጂት ብርሃን ሌላኛው መጽሐፍ — ‹‹ምርኮኛ›› መጽሐፍ ውስጥ!! ፍሬህይወትን ሆና፡፡ ፍሬህይወት እና ንፁህ — የኢትዮጵያ አምላክ ያላረፈች ስጋችሁን፣ ያልጨለመች ብርሃናችሁን፣ ያላረፈች ነፍሳችሁን፣ ያልወደቀች ኮከባችሁን… አብዝቶ አብዝቶ ከትውልድ እስከ ትውልድ ይባርክ ዘንድ ምኞቴ ከልብ ነው፡፡
እና ደግሞ . . . ምን የሚል ሃሳብ ደግሞ መጣብኝ? . . . የሁለቱ መጻሕፍት ደራሲ — የ60ዎቹ ወጣቶች ብርሃነ-አምሳል — የአሁኗ ወይዘሮ ቆንጂት ብርሃን — በእርግጥ ግን — የእነዚህ በ‹‹ምርኮኛ›› ላይ ያለችዋ — የፍሬህይወት — እና — በ‹‹ያላረፉት ነፍሶች›› ላይ ያለችዋ የሃሳብ መንትያዋ — የንፁህ — እውነተኛ ታሪክ ባለቤት ራሷ ትሆን?? የሚል ድንገታም ሃሳብ — ድንገት — ጭራው እንደማይያዝ (ግን ጅራታም) ኮከብ ወደኔ ብርሃኑን ፈንጥቆ — ልይዝ ልጨብጠው ስል — በህልሜ ሰማይ ጥሎኝ ተሰወረ፡፡ በእውነት — ለማንም ኢትዮጵያዊት ሴት — ለማንም ኢትዮጵያዊ ወጣት — ለማንም ያን አሰቃቂ ዘመን ከነባህሉ በጽናት ለተወጣ ሰው ጭምር — እነዚህን የደራሲዋን ገጸባህርያት ‹‹ፍሬህይወት››ን ማወቅ ልክ የህይወትን ፍሬ እንደማግኘት ነው፤ እና ደግሞ ‹‹ንፁህ››ን ማወቅ —ልክ የራስን ህሊና፣ የራስን ልቦና እንደማንፃት ያህል ነው — ባይ ነኝ፡፡ ‹‹ፍፁም ኢትዮጵያዊት!›› ከሚለው የእነ ግርማ በየነ ዘፈን ውጭ — በእውን ፍፁም ኢትዮጵያዊት የሚባሉ ኢትዮጵያውያት ሰብዕናዎች እንደኮከብ በራቁን በዚህ ዘመን — ስለእውነት — እነዚህን አርአያ ሰቦች የምርኮኛዋን ፍሬህይወት እና ያላለፉ ነፍሶችን ንፁህን የመሠሉ አብረቅራቂ ከዋክብት — ታሪካቸው በመጽሐፍ ተከሽኖልን ማግኘት — የእውነት — በተለይ ማነፃፀሪያው ለጠፋብን ለእንደኔ አይነቱ እልፍ ኢትዮጵያውያን — ታላቅ መታደል ነው!!! በበኩሌ ደራሲዋን ዝቅ ብዬ አመሠግናለሁ፡፡ ግን ግን… የዚህች ደራሲ የወ/ሮ ቆንጂት ብርሃን ታሪክ — የራሷ የህይወት ታሪክ ይሆን?? የሚል ሀሳቤንም ሳልተወው ነው ታዲያ — በምስጋና የምለጥቀውው፡፡
‹‹እናመሠግናለን›› ማለትም እኮ ትልቅ ስጦታ አይደል?? — ነው እንጂ!! እና ለዚህች — የሁልጊዜም ውብ ኢትዮጵያዊት፡፡ እ ና መ ሰ ግ ና ለ ን ! ! ! ብለናል፡፡ ተባረኪ አንቺ ሁሌም ወጣትነትን የተላበስሽ የተዳፈነን ብርሃን ለትውልድ የምትፈነጥቂ እውነተኛ ደራሲ፡፡ ይህችን ደራሲ በአካል አላውቃትም፡፡ በመጽሐፍ ምረቃዋ ላይ ከተነሳችው ፎቶግራፍም ውጭ ምን ዓይነት ሰው ትመስል እንደሆነም አይቼም አላውቅ፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን — የግድ ማወቅ ሳያስፈልግ — ወይዘሮ ቆንጂት ብርሃን — ከእነዚህ ሁለት መጽሐፎቿ በኋላ — እውነትም እንደስሟ የቆነጀች ብርሃን መሆኗን መገንዘብ አያዳግትም! እውነትም እንደ ስሟ — ውብ፣ ቆንጆ፣ አዲስ ኮከብ የሆነች፣ ብርሃን፣ ፀዳል፣ ጨረሯን በጭለማችን ላይ የምትፈነጥቅ ድንቅ ወይዘሮ ነች — ደራሲ ቆንጂት ብርሃን፡፡
በበኩሌ — ለእኔ — ንፁህም ሆነች ፍሬህይወት ወይም ደራሲዋም ራሷ ብትሆን — ልናዳፍነው በደረስነው በሰብዓዊው ተፈጥሯችን ላይ ፈንጥቀውልን የሚያልፉት ድንቅ ነገር — በአንድ ወቅት በዚህች ምድር ኖረው ያለፉ ወይም የሚያልፉ እውነተኛ የኢትዮጵያውያት ሴቶችን አብርሆትና ማንነትን ብቻ ሳይሆን — ከዚህም በላይ የሚወክሉትን ድንቅ የእውነተኛ የኢትዮጵያውያን እውነተኛ ሰብዕናና እውነተኛ ታሪክ፣ እውነተኛ ቅርስ ነው፡፡ እነዚህ ቆነጃጀት የሚወክሉት — በአንድ ወቅት እንደዘበት ወድቆ ቢቀርም — አንድ ቀን ደግሞ ከአመዱ ውበትን ተላብሶ እንደሚነሳው በራሪ ወፍ — እንደ ፊንክስ — አንድ ቀን ከወደቀበት አለምልሞ የሚነሳውን — እና የብዙዎች ሕልምና ረሃብ የሆነውን — ለምንጊዜም በልባችን ማህተሙ የሚቀርልንን — ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የሃገር ፍቅር ነው፡፡ ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የብልፅግና መቅረዝ ነው፡፡ ያን እንደ ኦርየን ከዋክብት ከያቅጣጫው ከተሰባሰቡ እልፍ አዕላፍ ኢትዮጵያውያን ነፍሳት እየተነሣ የሚበራውን — ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነፃነት፣ ኢትዮጵያዊ ስብዕና ነው የሚወክሉልኝ!!!
እነዚያን ድንቅ ነገሮች አልመው — በሁለ-ነገራቸው አንግበው የተነሱት — እነዚያ ውብ የሆኑ — በተሸነፈ ማንነት ውስጥ እንደለመለሙ ያሉ — ግና ያልተሸነፉ አይበገሬ፣ ውብ፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት የዘመን ጽጌረዳዎች — ውብ አይበገሬ እውነተኛ ወንድሞችና እህቶች — እነዚያን ያላረፉ ነፍሶች — አንድዬ አምላክ ነፍሳቸውን ያሳርፍላቸው — ህልማቸውን ያብራላቸው — በገነተ-አፀዱ ያኑራቸው አልን — ከልብ፡፡
ደራሲዋ — በዚህ አዲሱ መጽሐፏ — ንፁህን — ውሃ-ተራጭታ ካደገችበት ሠፈሯ ጀምራ — እስከ ትምህርት ቤቷና መምህሮቿ — እስከ እናት፣ ወንድም፣ እህቷ — እስከ ቀደማዊ ምኒልክና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያጓጓዘች — በአሰቃቂው የ60ዎቹ የፖለቲካ እሣት ተቃጥሎ ጠባሳው ያልለቀቀውን — ያን የንፁኅ፣ የንፁሀን ህይወት — በሚገርም ቅለትና ቅርበት — ልብን በሚነካ ሰብዓዊ ቋንቋ — ልክ ራሳችን በሥፍራው ላይ ታዳሚ ሆነን ነበልባሉን የቀመስነው እስኪመስለን ድረስ — ስላየችን፣ ስላናደደችን፣ ስላሳዝነችን፣ ስላስቆጨችን፣ እና ሳንወድ በግድ — በእናት አንጀት ከሚያለቅሱት እናቶች ጋር — አብረን — እንድናለቅስ — የእናት አንጀትን እንዲህ በቃላት ኃይል ግልጽልጽ አድርጋ ላቋደሰችን — ለዚህች ደራሲ — ቆንጂት ብርሃን — በድጋሚ ጤናውን፣ ሠላሙን፣ ዕድሜውን ይስጥሽ፣ ልጆችሽን የኢትዮጵያ አምላክ ይባርክልሽ ብዬ አመስግኜ አበቃሁ፡፡
አምላክ  ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያችንን ሁላችን ራዕያችንን እውን የምናደርግባት፣ እፎይ ብለን በሠላም፣ በፍቅር፣ በብልፅግና በፍፁም ነፃነት የምንኖርባት — የለመለመች የብርሃን መስክ ያድርግልን፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ትኑር፡፡
ፎቶግራፍ ምስል (ለእናትና ልጅ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
ከ ‹‹ያላረፉ ነፍሶች›› መጽሐፍ ሽፋን የተወሰደ፡፡
Filed in: Amharic