>
5:13 pm - Sunday April 19, 4443

ከዲያስፖራው ጋር የሚደረገው ውይይት ትርጉም እና ፋይዳ ይኖረው ዘንድ በእውነተኛ የለውጥ እርምጃዎች የታጀበ ይሁን!! (ትብብር)

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጭው ነሀሴ ወር 2018 ዓም ወደ አሜሪካ እና ሌሎች የምእራብ አገሮች መጥተው ከዲያስፖራው ጋር ውይይት ማድረግ እንዳቀዱ በስፋት ይነገራል። ይሄንን ጉዳይ አስመልክቶ የአለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል እና የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ያላቸውን አቋም የሚያንጸባርቅ መግለጫ  አውጥተዋል ያንብቡት።

ከዲያስፖራው ጋር የሚደረገው ውይይት ትርጉም እና ፋይዳ ይኖረው ዘንድ በእውነተኛ የለውጥ እርምጃዎች የታጀበ ይሁን!!

አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በመጭው ነሀሴ ወር 2010 ዓ.ም. ወደ አሜሪካን አገር እንደሚመጡ እና ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር የመወያዬት እቅድ እንዳላቸው በስፋት እየተነገረ ይገኛል። በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ማወያዬት የሚደገፍ ሀሳብ ቢሆንም፣ የሚደረጉት ውይይቶች የአገራችንን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መሰረታዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት እገዛ የሚያደርጉ መድረኮች ሊሆኑ ይገባል። አገራችን ኢትዮጵያ ስር የሰደዱ፣ ዘመን የጠገቡ እና ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ያሉባት አገር ነች። እነዚህ ችግሮች ደረጃ በደረጃ መፍትሄ ያገኙ ዘንድ አገራችን በትክክለኛው የለውጥ ጎዳና ላይ መጓዝ ይኖርባታል። በመሆኑም፣ ከዲያስፖራው ጋር የሚደረግ ውይይት ከዘላቂ መፍትሄ አኳያ የሚቃኝ እንጂ የአጭር ጊዜ ግብ ለማሳካት የሚደረግ የህዝብ ግንኙነት ሥራ ሊሆኑ አይገባም።

ዲያስፖራው ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት በአገሩ ጉዳይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ሲያሰማ የኖረ ማህበረሰብ ነው። አገሩ የነጻነት ምድር እንድትሆን፣ የህዝቧ አንድነት እንዲጠበቅ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ፍትህ እንዲሰፍን እና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ዲያስፖራው ያለመታከት የሚቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል፤ ወደፊትም እነዚህ እሴቶች በአገራችን እውን ይሆኑ ዘንድ የድርሻውን ሀላፊነት መወጣቱን ይቀጥላል። በጥቅሉ፣ የዲያስፖራው ጥረት በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ የስርአት ለውጥ እንዲመጣ እና አገራችን በተሻለ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጎዳና ላይ እንድትጓዝ ማገዝ ነው። ስለሆነም፣ የዶ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር ከዲያስፖራው ጋር ለማድረግ ያሰበው ውይይት አገራችንን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት አካል መሆን ይኖርበታል።

ዶ/ር አብይ አህመድ የህዝባዊ እምቢተኝነት ግፊት ወደ መሪነት ያመጣቸው እና የለውጥ አቀንቃኝነት ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑ በህዝቡ ዘንድ ከፍ ያለ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የጠቅላይ ሚኒስተር ሃላፊነትን ከተረከቡም በኋላ በጎ የሚባሉ በርካታ ሀሳቦችን ሰንዝረዋል። በተለይም፣ ኢትዮጵያዊነትን አስመልክተው ያራመዱት አቋም እና ያደረጉት ንግግር የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ይሁን እና፣ አገራችንን ወደተሻለ የለውጥ ጎዳና ከመውሰድ አኳያ ዶ/ር አብይ ምን ሀሳብ እንዳላቸው እና ምን ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ እንደሚፈልጉ ግልፅ አይደለም። ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለማሸጋገር ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንዳላቸው በግልፅ አይታወቅም። ይህ መሰረታዊ ቁምነገር ግልፅ ባልሆነበት ሁኔታ ከዲያስፖራው ጋር የሚደረገው ውይይት የረባ ትርጉም እና ዘላቂ ፋይዳ ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ከዲያስፖራው ጋር ሊደረግ የታቀደው ውይይት ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እንዲኖረው ከተፈለገ፣ አገራችን ወደተሻለ የስርአት ለውጥ ጉዞ መጀመሯን የሚያመለክቱ ተጨባጭ እርምጃዎች በዶ/ር አብይ ሊወሰዱ ይገባል። ዶ/ር አብይ ከታች የተዘረዘሩትን ተጨባጭ እርምጃዎች አጠር ባለ ጊዜ ውስጥ በመውሰድ ለስርአት ለውጥ ያላቸውን ፍላጉት እና ቁርጠኝነት በግልጽ ማሳዬት ይጠበቅባቸዋል።

  1. ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ማድረግ፣
  2. ህዝቡን ለማሸበር ከህግ አግባብ ውጭ የጸደቀውን እና አገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ ስር ያደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ ነገ ሳይባል እንዲነሳ ማድረግ፣
  3. ዜጎችን ከቀያቸው የማፈናቀል ኢሰብአዊ ወንጀል በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ፣
  4. የህዝቡን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለመገደብ፣ የመጻፍ እና የመናገር መብትን ለማፈን እና በሰብአዊ መብት ማስከበር ዙሪያ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማሽመድመድ የወጡ አፋኝ የፀረ-ሽብር ህግ፣ የሚዲያ አዋጅ እና  እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድንጋጌዎች እንዲሻሩ ማድረግ፣
  5. በፖለቲካ ድርጅቶች፣ በሚዲያ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ የተጣለውን የአሸባሪነት ፍረጃ ማንሳት፣
  6. ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአገራቸው የለውጥ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑበትን መደላድል መፍጠር።

እነዚህ የለውጥ ፍላጎትን እና ቁርጠኝነትን የሚያንጸባርቁ ተጨባጭ እርምጃዎች እየተወሰዱ ከዲያስፖራው ጋር የሚደረግ ውይይት ጤናማ እና ትርጉም ያለው ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የሚከተሉትን ሁኔታዎች በማመቻቸት ከዲያስፖራው ጋር የሚደረገው ውይይት የበለጠ ፍሬያማ ማድረግ ይቻላል ብለን እናምናለን።

  1. ከህዝብ ጋር ከሚደረገው ውይይት በተጨማሪ መሰረታቸውን በውጭ ካደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና አክቲቪስቶች ጋር ውይይት ማድረግ፣
  2. ውይይቶቹ በውጭ ላሉ ሁሉም ሚዲያዎች ክፍት እንዲሆኑ ማድረግ እና ዶ/ር አብይ እራሳቸው ከሚዲያዎቹ ጋር በመገናኘት ከጋዜጠኞች የሚነሱላቸውን ጥያቄዎች እንዲመልሱ ሁኔታውን ማመቻቸት።

ከላይ የተዘረዘሩት እርምጃዎች እየተወሰዱ እና መድረኩ ሁሉንም አሳታፊ እና ለሚዲያዎች ክፍት እንዲሆን ከተደረገ፣ ከዲያስፖራው ጋር የሚደረገው ውይይት የአገራችንን የለውጥ ሂደት ከማገዝ አኳያ ፋይዳ ይኖረዋል ብለን እናምናለን። እነዚህ የቅድሚያ ስራዎች ከተከናወኑ ለአገራችን እና ለህዝባችን የሚጠቅሙ በጎ ጅማሬዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ እየገለጽን፣ ሁላችንም በሂደቱ ውስጥ በመሳተፍ የዳበረ ውይይት እንዲደረግ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንደምናደርግ በዚህ አጋጣሚ እናሳውቃለን።

አገራችን ኢትዮጵያ በነጻነት፣ በእኩልነት እና በፍትህ ለዘላለም ትኑር!!

አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል1 እና

የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር2

ግልባጭ፦ ለኢሳት፣ ለኦኤምኤን፣ ለቮይስ ኦፍ አሜሪካ፣ ለዶቸቬሌ እና ሌሎች የሚዲያ ተቋማት

መግለጫ፦

  1. አለምአቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግብረሀይል በተለያዩ ክፍለ-ዓለማት የሚገኙ እና በከተማ ደረጃ የተዋቀሩ ግብረሀይሎችን በአለምአቀፍ ደረጃ የሚያስተባብር የጋራ ስብስብ ነው።
  2. የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር ከታች የተዘረዘሩትን ድርጅቶች በጋራ የሚያስተባብር አካል ነው።
  • የአፋር ሰብአዊ መብት ድርጅት
  • የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ማእከል
  • የሰብአዊ መብት ማህበር በኢትዮጵያ
  • የባለራእይ ወጣቶች ማህበር
  • የድንበር ጉዳዮች ኮሚቴ
  • የኢትዮጵያ የውይይት መድረክ
  • የኢትዮጵያዊያን አሜሪካዊያን ምክርቤት
  • የኢትዮጵያ ውርስ እና ቅርስ ማህበር በሰሜን አሜሪካ
  • የኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባኤ
  • የመጀመሪያው ሂጅራ ፋውንዴሽን
  • የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ እና ፖሊስ አባላት ማህበር
  • ጋሻ ለኢትዮጵያ
  • ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት
  • የኢትዮጵያ ህብረት (የክፍለሀገራት ህብረት)
  • ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ወጣቶች አንድነት
  • አንድ ኢትዮጵያ ንቅናቄ
  • የተባበሩት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ንቅናቄ
  • ሕጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
  • የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
  • የወላይታ እና ተባባሪዎቹ ማህበር በሰሜን አሜሪካ
  • የተባበሩት የቀድሞ  አየር ሃይል አባላት ኢንተርናሽናል ማህበር
  • የኢትዮጵያ ራእይ (ቪዥን ኢትዮጵያ)
  • ያ ትውልድ ተቋም
  • የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሀይል አባላት በዋሽንግተን ዲሲ
  • የተጠቂዎች ድምጽ ድርጅት
  • Zemecha18@gmail.com 2026270130info@tibibir.org           www.tibibir.org 773-341-8511
Filed in: Amharic