>

እባካችሁ ቀስቅሱኝ? ስሞትላችሁ "እውነት ነው" በሉኝ? "የቂም-በቀል ፖለቲካ አልፏል!" በሉኝ?  (ስዩም ተሾመ)

ወዳጆቼ ከኢትዮጲያ ፖለቲካ የተማርኩት ነገር ቢኖር ቂም-በቀል እና ጥላቻ ነው፡፡ አፄ ሃይለስላሴ በላይ ዘለቀ፥ ጄ/ል መንግስቱ ነዋይ፥ ጄ/ል ታደሰ ብሩ፥…ወዘተ ያሉ ጀግኖችን መስቀላቸውን ዘወትር አስባለሁ፡፡ መንግስቱ ሃይለማሪያም 60ዎቹን ባለስልጠናት፣ በቀይ ሽብር ዘመቻ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን፣ እንደ ጄ/ል ደምሴ ቡልቶ ያሉትን ተቀናቃኞቹን ገድሏል፥ አስገድሏል፡፡ ህወሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት እንደ ፕ/ር አስራት ወልደየስ ያሉ ጀግኖችን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞትና መከራ ዳርጏል፥ የብርቱካን ሚደቅሳ ሰብዓዊ ክብር ገፍፏል፣ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ፅጌ ያሉ መሪዎችን ለስደትና እስራት ዳርጏል፡፡ በአጠቃላይ ከህፃንነት እድሜዬ ጀምሮ ቂምና በቀል ስሰማ፥ ስማርና ሳስብ ኖሬያለሁ፡፡
አሁን የማየው ነገር ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ በቂም-በቀል አስተምህሮት የዛገው አዕምሮዬ በዶ/ር አብይ ይቅር-ባይነት እና አክብሮት ግራ ተጋብቷል፡፡ በእርግጥ መሆን ያለበት እንደሆነ፣ ሊደረግ የሚገባው ነገር እንደተደረገ አውቃለሁ! እንደው የለመድኩት ቂምና ጥላቻ፥ እልህና በቀል መቅረቱን ማመን አቃተኝ፡፡ የማየው ነገር ብርቅ ሆነብኝ፡፡ ይሄ ነገር በህልሜ እንዳይሆን እባካችሁ ቀስቅሱኝ? ስሞትላችሁ “እውነት ነው” በሉኝ? “የቂም-በቀል ፖለቲካ አልፏል!” በሉኝ? “የይቅርታና አብሮነት ዘመን ተጀምሯል”፣ “የዱክማኖች ፖለቲካ ላይመለስ ሄዷል በሉኝ?”… እባካችሁ አትፍረዱብኝ፣ ቂም-በቀል ስማር ነው ያደኩት፡፡ ልቦናዬ በጥላቻ ቆስሎ ፍቅርን መሸከም አቅቶታል! ልቤ በቂም-በቀል ደንዝዞ ይቅርታን መገንዘብ ተስኖታል!! ዘር-ማንዘሬን ቆጥሮ የሚጠላኝ፥ የሚበቀለኝ በቀለኛ መንግስት አልፏል በሉኝ፡፡ አደራ…አደራ… ነገ ጠዋት ይሄ ሁሉ “ህልም ነው” እንዳትሉኝ፡፡ ተስፋዬን አንዳታጨልሙብኝ፣ ምኞቴን አታጣጥሉብኝ…  ያ… ዘረኛ፥ ቂመኛ፥ በቀለኛ፥… ስርዓት ላይመለስ ሄዷል በሉኝ፡፡
Filed in: Amharic