>
5:13 pm - Friday April 20, 5523

እስረኞችን ማስፈታት “መሠረታዊ” የህዝብ ጥያቄ አይደለም፣ የፖለቲካ ግብ ሊሆን አይችልም! (ስዩም ተሾመ)

ባለፉት ሁለት ወራት የታዩትን ለውጦች መለስ ብሎ ላስተዋለ የሀገራችን ፖለቲካ የኋሊት ጉዞ መገታቱን ይገነዘባል። ለምሳሌ የዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገረባ፣ እስክንድር ነጋ፣… ወዘተ የመሳሰሉ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ለእኔ በጣም አስገራሚ ነው። በእርግጥ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች እንደሚፈቱ ፅኑ እምነት ነበረኝ። ነገር ግን፣ በዚህ ፍጥነት እውን ይሆናል ብዬ ፈፅሞ አልጠበቅኩም ነበር። ለመሆኑ ከሁለት ወራት በፊት “በግንቦት20 ዕለት የግንቦት7 መስራችና መሪ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ቤት ይወጣል” ብሎ የጠበቀ ሰው ነበርን? ይህንን ሌላው ቀርቶ ጠ/ሚኒስትር አብይ ራሱ የጠበቀ አይመስለኝም። በአጠቃላይ ከሁለት ወራት በፊት የሩቅ ሀገር ሀሜት ይመስሉ የነበሩ ነገሮች ዛሬ ላይ እውን ሆነዋል። ነገር ግን፣ የእስካሁኑ እንዳለ ሆኖ በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ከወዲሁ ሊታሰብ ይገባል።

የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በአግ7 (PG7)፥ ኦነግ (OLF)፥ ኦብነግ (ONLF)፥ ጋህነን (GPLM)፣ ቤህነን (BPLM)፣ ትህዴን (TPDM)፣… ወዘተ አመራር፥ አባል፥ ደጋፊ፥ ተላላኪ፥… እያለ ለእስራትና ስደት የዳረጋቸው የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የፖለቲካ መሪዎች፥ … ከሞላ-ጎደል ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር “የዜጎች መብት እና የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ!” የሚለው የጋራ አቋማቸው ነው። እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ያሉ መሪዎች የትጥቅ ትግል የጀመሩበት ዋና ምክንያት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የዜጎችን መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደማይችሉ በማመናቸው ነው። ለዚህ ደግሞ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ለሕዝብ ድምፅ ሆነ ለሕግ ተገዢ እንደማይሆን በ1997ቱ ምርጫ ወቅት በተግባር አረጋግጠዋል።

እንደ ዶ/ር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገረባ በሰላማዊ መንገድ፣ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አንዳርጋቸው ፅጌ በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ መሪዎች በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በአሸባሪነት ተከስሰው ለእስራትና ስደት ተዳርገዋል። ይህም ሆኖ ግን እነዚህ መሪዎች በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ድጋፍና ተቀባይነት ከዕለት-ወደ-ዕለት እየጨመረ ሄደ እንጂ አልቀነሰም። በመጨረሻም በሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ አማካኝነት አብዛኞቹ ከእስር ተፈትተዋል፣ በስደት ከሚኖሩበት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። ይህ የሚሆነው በሌላ ምክንያት ሳይሆን ሲጀመር ለእስርና ስደት መዳረጋቸው ስህተት ስለነበር ነው።
የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ትክክል የሚሆነው በመጀመሪያ መታሰራቸው ስህተት ስለሆነ ነው። በተመሳሳይ በስደት የሚገኙ ፖለቲከኞች ወደ ሀገራቸው መምጣት ያለባቸው መሰደዳቸው ስህተት ስለሆነ ነው። በአጠቃላይ የፖለቲካ እስረኞችና ስደተኞችን መፍታትና ለሀገራቸው ማብቃት ግዴታ እንጂ ውለታ አይደለም። ስለዚህ መታሰር ያልነበረባቸውን ሰዎች አስሮ መፍታት፣ እንዲሁም መሰደድ ያልነበረባቸው ሰዎች ለስደት ከተዳረጉ በኋላ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መፍቀድ የሚፈለገው ለውጥ መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ሊሆን አይችልም። የሕዝቡ ጥያቄ ሆነ የፖለቲከኞቹ ዓላማ የዜጎች መብትና ነፃነት ማስከበር ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት ሲቻል ነው።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት በቅድሚያ የዜጎች ድምፅ እና የሕግ የበላይነት ሊረጋገጥ ይገባል። ይህ እስካልሆነ ድረስ የዜጎች ጥያቄ ምላሽ አያገኝም፣ የፖለቲካ መሪዎች እስራትና ስደት አይቆምም። ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ፣ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት ጨርሶ ሊጠፋ አይችልም። ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው፣ የዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትህ የሚከበረው በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ለዜጎች ድምፅ እና ለሕግ ተገዢ ሲሆን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ አንደኛ፡- ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ያስፈልጋል፣ ሁለተኛ፡- ሀገሪቱ የምትመራባቸውን ሕጎች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥… ወዘተ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች በማስከበር፣ እንዲሁም የብዙሃኑን ጥቅምና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ ይገባል።

ብዙዎች ለእስራት፥ ስደት፥ እንግልትና ሞት የተዳረጉት የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር፣ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ጥረት በማድረጋቸው ነው። በመሆኑም የሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው፣ በዚህም የሀገሪቱ ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው፣ መንግስት ነፃና ገለልተኛ ምርጫ በማካሄድ ለሕዝብ ፍቃድና ምርጫ ተገዢ ሲሆን፣ እንዲሁም አፋኝ የሆኑ ሕጎች፥ ደንቦችና መመሪያዎችን በማስተካከል የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ማክበርና ማስከበር ሲችል ነው።

በዚህ መሰረት፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ሆነ ከስደት እንዲመለሱ ማድረግ ከዚህ በፊት በመንግስት የተፈፀሙ ስህተቶችን ማረም እንጂ የሕዝቡን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ አይደለም። የሕዝቡ ጥያቄ በአፋኝ ሕጎች፥ ደንቦችና መመሪያዎች አማካኝነት ለእስርና ስደት የተዳረጉትን የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የፖለቲካ መሪዎች ማስፈታትና ማስመለስ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እነዚህን አፋኝ ሕጎች፥ ደንቦችና መመሪያዎች ከፍትህ ስርዓቱና የአሰራር ሂደት ውስጥ ማስወገድ ነው። መንግስት የሰራቸውን ስህተቶች እንዲያስተካክል ዕድል መስጠት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በነፃና ገለልተኛ ምርጫ አማካኝነት በመንግስት ላይ ያለውን የስልጣን የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ በቀጣይ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በፍትህና አስተዳደራዊ ስርዓቱ ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ ለማምጣትና ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

Filed in: Amharic