>

አንዲ ሊይዙት ምጥ - ሊለቁት ጭንቅ አስቸጋሪ የነብር ጭራ!  (መስከረም አበራ)

አንዲ በሰው ዘንድ ምን እንደሆነ የማያውቁት አሳሪዎቹ ገና ዛሬ ነው የአንዳርጋቸውን እና የኢትዮጵያን ህዝብ ስብት ሃይል  ጉልበቱን የተረዱት፨ ቢለቁት ክብሩን ያያሉ ፤ቢያስሩት አንገታቸው ታንቋል፨ ስለዚህ ወደ እንግሊዝ መላኩ አማራጭ ሊደረግ ይችላል፨ እኛ (የአቀባበል ኮሚቴው አባላት) እስከዚች ደቂቃ በአባቱ ቤት ተገኝተን መጠበቅን ወደናል፨ ጥበቃችን የአንዲ እስረኝነቱ አብቅቶ ራሱ ቁርጡን እስኪነግረን ይቀጥላል፨
አሁን በወያኔ የጡት ልጆች እየተወተወተ ያለው ‘እንግሊዛዊ ስለሆነ ኢትዮጵያ መቆየት አይችልም ፣የሚቆየው የጉዞ ዶክመንቱ እስኪዘጋጅለት ነው’ እያሉ ነው፨ ይህ ጉዳዩን ወደ ጌታቸው አሰፋ ቢሮ ይወስደዋል፨ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን ጉዳይ የሚከወነው እዛ ነው ፤ህገ-ወጡም ህገኛውም የሚቦካው በእሱ እጅ ነው፨ እዛ ደግሞ ብዙ ንዴት፣ ብዙ መቃጠል ፣እልፍ ጥርስ ማፋጨት አለ! ነገሮች በቅንነት እንደማይሆኑ ግልፅ ነው፨ ነገሩ ሁሉ እንደ ጠ/ሚ አብይ ሃሳብ እንደማይደረግ በዚህ ማወቅ ይቻላል፨
አብይ በግሉ አንዳርጋቸውን እንደጠላት የሚያይበት ምክንያት የለውም፨ እንደውም ስለ አንዲ  ከእኛ የሚርቅ መረዳት ላይኖረው ይችላል፨ አብይ አባቱ ቤት ድረስ አጅቦት መጥቶ ይቅርታ ጠይቆ ሊያስረክብ እንኳን ችግር እንደ ሌለበት እገምታለሁ፨ ችግሩ ያለበትን ቦታ አሳምረን እናውቃለን፨
 አንዳርጋቸውን ሲያዩ አለማወቃቸው ጠልቆ የሚሰማቸው፣የዝቅተኝነት ምርኮኞች ድኩማን ይህን ግዙፍ ሰው ፈተው አዲስ አበባ ላይ ሲከበር ማየት ሞታቸው ነው፨ አንዳርጋቸው ዛሬ ቀርቶ ሲይዙት የፈለጉትን የሚያናግሩት ፣የፕሮፖጋንዳ ብርንዶ የሚቆርጡበት ግልብ ፖለቲከኛ አይደለም፨ ስለፈታችሁኝ እነሆ ውዳሴ ያላቸው አልመሰለኝም፨ አዋርደው መፍታት የለመዱት እባቦች የሁልጊዜ አሸናፊያቸውን ለቀው በአደባባይ መዋረድ አልፈለጉምና አይናችን እስኪሟሟ መንገድ መንገድ ብናይ አንዲ አልመጣም፨
ለልጆቹ በሰላም ከደረሰም ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፨ እኛ ትናንት የዓለምን ደስታ ተደስተናል ፣ ቤተሰቦቻቸው እንባ እሰስኪተናነቃቸው የእኛ በቤታቸው መገኘት ትርጉም ያለው ነገር እንደሆነ ነግረውናል፣ እምብዛም ድምፅ የማይወዱት አዛውንት አባቱ በዳንኪራችን መሃል ገብተው በጭብጨባ አጅበውናል ፣ዝናብ እየመታን ስንጨፍር አምላካቸውን አመስግነዋል ! እኛ እንዲህ አንጀታችንን አርሰናል ፤ይብላኝ ማሰር ብቻ ለሚያስደስተው መፅናኛ ቢስ!!!!!!!
Filed in: Amharic