>

ፌዴሬሽኑን የዶ/ር አብይን የእንግዳችሁ ልሁን ጥያቄ "ይቀበል" ወይስ "አይቀበል" 

ፌዴሬሽኑን የዶ/ር አብይን የእንግዳችሁ ልሁን ጥያቄ “ይቀበል” ወይስ “አይቀበል” የሚለው ርእሰ ጉዳይ ትልቅና ወቅታዊ አጀንዳ ሆኗል፤ የአገራችን እውቅ ፖለቲከኞች፣ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን የግል ምልከታ አንጸባርቀዋል እኛም ለአብነት ያህል የተወሰኑትን ሀሳቦች አስተናግደናል:-
                    ***

ፌዴሬሽኑን ወ/ሪት ብርቱካንን በመጋበዙ ለመሰንጠቅ የዳረገውን ስህተቱን እንዳይደግመው እሰጋለሁ!??!

መሳይ መኮንን
ዶ/ር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት በዓል ላይ ለመገኘት ጥያቄ ማቅረባቸውን ሰማሁ። በተመሳሳይም የአውሮፓውን የኢትዮጵያውያን ፌደሬሽንንም በደብዳቤ እንደጠየቁ ይነገራል። አስገራሚ ነገር ነው። መጠየቃቸው ባልከፋ። ወገናቸውን ለማነጋጋር በዚህ ደረጃ መፈለጋቸው የሚወገዝ አይደለም። ነገር ግን ምን አስበው ነው? ውጭ ላለው ኢትዮጵያዊ እስከአሁን በሀገር ቤት ከተናገሩት የተለየ ምን ሊነግሩት ነው? ቢያንስ የተወሰኑ በህዝብ ዘንድ የሚጠየቁ እርምጃዎችን ከወሰዱና መንገዱን ካለሳለሱ በኋላ ቢሆን አይሻልም? መድረክ እንዲህ የጠማቸው ለምን ይሆን?
የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌደሬሽን የራሱን መተዳደሪያ ደንብ ጥሶ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ ይቀበላል የሚል ግምት የለኝም። ፌዴሬሽኑን ለሁለት ከፍሎት ላለፉት 12 ዓመታት የዘለቀው ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በክብር እንግድነት በጋበዘ ወቅት ከህወሀት ደጋፊ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በኩል ተቃውሞ በመቅረቡ ነው። እንደመፍትሄም የፖለቲካ ሰው ከየትኛውም ወገን መጋበዝ አይቻልም የሚል መመሪያ ደንቡ ውስጥ አስቀምጦ ነው ላለፉት 10 ዓመታት የቆየው። በዚህ ዓመትም አቶ በቀለ ገርባን ለመጋበዝ ታስቦ ይህ መመሪያቸው እንደከለከለቸው ሰምቼአለሁ። እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛ በመሆኑ ሊጋበዝ እንድታሰብ ታውቋል።
 ታዲያ ዶ/ር አብይ ያቀረቡትን ”በእንግድነት ጋብዙኝ” ጥያቄን ፌዴሬሽኑ ምን መልስ ሊሰጥ ይሆን? መመሪያውን ጥሶ ጥያቄአቸውን ሊቀበል? ወይስ ለደንቡ ተገዝቶ በአቋሙ መጽናት? ይህ ፌዴሬሽን በዚህ ውሳኔ ከሁለት ዳግም እንዳይከፈል ስጋት እንዳለ ይሰማል። ዶ/ር አብይ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት የኢትዮጵያውያን መሰባሰቢያ የሆነውን መድረክ ከአደጋ ጋር አፋጠውታል። ዲያስፖራውን ለማዳከም ህወሀት ብዙ ሙከራ አድርጓል። አልተሳካለትም። ዶ/ር አብይ ይህን ያደርጉታል ብዬ አልጠብቅም። ካደረጉት ግን አካሄዳቸውን ብቻ ሳይሆን ያደነቅነውንና ያጨበጭብልነትን አመጣጣቸውንም በጥያቄ እንድንመረምረው የሚያደርገን ይሆናል።
ዶ/ር አብይ መድረክ አብዝተዋል። በእምነት ህይወታቸው የቀሰሙትን የማነቃቂያ ንግግር ክህሎታቸውን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ጉዟቸው አጥበቅው እየተጠቀሙበት ነው። ሆኖም እንዲህ መድረክ የሚያስጠና ውጤት አስመዝግበዋል ብዬ አላምንም። ስራው መቅደም ነበረበት። ቢያንስ ደጋፊዎቻቸው አደረጉ ብለው ነጥብ ከሚሰጧቸው አንዳንድ እርምጃዎች ተሻግረው መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ እርምጃዎችን በሂደት ደረጃ ሳያሳዩ በየመድረኩ መከሰትና፡ ጋብዙኝ ማለት የሚደገፍ ውሳኔ አይደለም።
ትላንት በኤምባሲ በተጠራ ስብሰባ ላይ ኢሳትና አባይ ሚዲያ እንዳይገቡ ተደርገዋል። ለኢትዮጵያውያን በሙሉ በተጠራው መድረክ ላይ ለምን እንዲህ ዓይነት ክልከላ እንዳስፈለገ ግራ ያጋባል። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስተዳደር የለውጥ ምልክት ማሳየት ካለበት ከዚህ መጀምር ይኖርበታል። ኤምባሲው ባልተለመደ መልኩ ደጋፊና አባል ብሎ ልዩነት ሳያደርግ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ያቀረበው ጥሪ የሚበረታታ ነበር። ሆኖም ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ ነገር ሆኖ የህወሀት ሰዎች ከተጣበቀባቸው አባዜ ባለመላቀቃቸው ታጥቦ ጭቃ ሆነው አርፈዋል። ኤምባሲው በር ላይ የሚገባና የሚወጣ የሚለዩ መሆናቸውን ዳግም አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነሃሴ ወደ አሜሪካ ይመጣሉ በሚል በዋሽንግተን ዲሲ ሽር ጉድ እያሉ ያሉ ግለሰቦችንም ካየን የተለመደው የካድሬ ግርግር ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም። ከስርዓቱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች ኮሚቴ አቋቁመው ለአቀባበል ወገባቸውን አጥብቀው እየሰሩ ነው። እንደምንሰማው ጠቅላይ ሚኒስትሩም እየመረጡ አንዳንድ አክቲቪስቶች ጋር ስልክ ደውለው እያነጋገሩ ነው። መለየቱ ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። ለመፍትሄና ለዘላቂ ለውጥ ከልብ የተነሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ እንዲህ ዓይነት ከፋፋይ መንገድ ተመራጭ አይደለም።
መሪነታቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩል መሆኑን ማሳየት የእሳቸው ግዴታ ነው። እዚህ ያለውን አንድነት በማንኮታኮት ላይ የተመሰረተውን የህወሀት ታክቲክ ዶ/ር አብይ እንዳይከተሉት የቅርብ ወዳጆጃቸው ቢመክሯቸው ጥሩ ነው። ኢህአዴግ ከሚባለው የግዑዛን ስብስብ እሳቸውና ቲም ለማ እንደሚለዩ በዚያም የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ እንደሸመቱ አይጠፋቸውም ብዬ አስባለሁ። አሁንም በኢህ አዴግ ዜማና ቅኝት እንድንደንስ እየፈለጉ ከሆነ ብዙም ርቀት የሚወስዳቸው አይሆንም። እሳቸው እንዳሉትም ይህ ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ እንጂ ባረጀው ሊመራ አይፈቅድም።
በአጭሩ መድረክ የመጠማታቸውን ያህል ለተግባራዊ መሰረታዊ ለውጦች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲተጉ ያስፈልጋል። ዙሪያቸው ተኮልኩለው አላሰራ ያሉ የህወሀት እንቅፋቶችን በሂደት እየጠራረጉ በቃላቸው የዘመሩትን ኢትዮጵያዊ ለውጥ በተግባር እንዲያሳዩ ይጠበቃሉ። ያን ጊዜ በአንደበታቸው ብቻ ሳይሆን በውጤታቸው የሚማረክ ከጥግ እስከ ጥግ ያገኛሉ።
#ግንቦት20የጨለማቀን
             ***

በስታዲየም ጫጫታ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም፤ ስንት ጊዜ በቀቢፀ ተስፋ እንነዳለን ?

 (ከሀብታሙ አያሌው)
የከበረ ሰላምታ አስቀድማለሁ ! ወደ ፍሬ ነገሩ በማለፍም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሃሳብና ስሜቴን ለቦርዳችሁ በደብዳቤ ለማቅረብ ወዳነሳሳኝ ሃሳብ አልፋለሁ። ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ዘንድሮ በአሜሪካ እና በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌድሬሽን በዓል ላይ ለመገኘት እና ንግግር ለማድረግ እንደጠየቁ መገናኛ ብዙሃኖች በመዘገብ ላይም ናቸው። ተያይዞም ሰኞ ፌድሬሽኖቹ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ይገኛል።
የአውሮፓው ፌዴሬሽንም የሰሜን አሜሪካውን ፌዴሬሽን መልስ ከሰማሁ በኋላ ምላሽ እሰጣለሁ ማለቱም በዘገባዎች ተካትቷል። የተከበራችሁ ፌድሬሽኑ የቦርድ አመራሮች ነገሩን በጥንቃቄ እንድታጤኑት እጠይቃለሁ! እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ መርህ መጣስ የፌዴራሽኑን ህልውና ለአደጋ ያጋልጣል ብዬም እሰጋለሁ። የዲያስፖራውን ፖለቲካ በእስፖርት መካከል መፈለግም ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆን ጠቃሚ አይመስለኝም።
በሆይ ሆይታ በእስታዲዬም ጫጫታ የኢትዮጵያ ችግር አይፈታም። ስንት ጊዜ በቀቢፀ ተስፋ እንነዳለን ? ስንት ዘመን አስረው ያሰቃዩን ሲፈቱን ዩኒቨርስቲ አስገብተው ያስመረቁን ይመስል ለማጨብጨብ እንቆማለን የሚል ጥያቄም በህሊናዬ ይመላለሳል። እርቅና ስምምነት በሰከነ መንገድ ከሚመለከታቸው የፖለቲካ አካላት ጋር በመነጋገር እንጂ እስታዲዬም ለስፖርት ፌስቲቫል የሚመጣው ህዝብ መካከለል ተገኝቶ በመከፋፈል በመረበሽ ሊመጣ አይችልም።
አፋኝ ህጎችን ይሰርዙ፣ አስቸኳይ አዋጁን ያንሱ፣ የቀሩትን እስረኞች በሙሉ ይፍቱ፣ የገደሉና ያፈናቀሉትን የሚያጣራ ገለልተኛ ቦርድ ይቋቋም፣ ብሄራዊ እርቅ ይደረግ። ያኔ 100% አስተማማኝ ለውጥ ይሆናል። ያኔ ዶክተር አብይ በክብር ይጋበዛል !! ያኔ ሁላችንም በጋራ ቆመን በጭብጨባና በእልልታ እንደ ኢያሪኮ ቅጥር የፀብ ግድግዳን እናፈርሳለን። ይህ ዶክተር አብይ ከበረቱ ለሚቀጥለው አመት ይደርሳል። ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ህዝቧ የመስዋዕት በግ ሆኖ ዛሬ ዶክተር አብይ በሚመሩት ድርጅት ስቃይ የተቀበለውን አንዷለም አራጌን ፖለቲከኛ ስለሆነ በሚል ከግብዣው ተርታ አስቀርተን ለጠቅላዩ መፍቀድ ብርቱ ሃጢያት ይሆናል። ስለ ኢትዮጵያ እራሱን የበረሃ ሲሳይ ያደረገውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን አልፈን ጠቅላዩን ቤት ለእንግዳ ብንል የበደል ሁሉ በደል ይሆናል። እናም ፌዴሬሽኑ ያስብበት።
ጠቅላያችንን ለእስካሁኑ ስራው ከጨካኝ ድርጅታቸው ነጥለን እናመሰግናለን!!! ፍፃሜያቸው እንዲያምርም የበኩላችንን እናደርጋለን!!
               ***
ከአብይ ወደ አብይ ሁለቱ አብዮች 
            ከታምራት ነገራ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ
                   እና
 የ ESFNA ፕሬዝዳንት   አብይ ኑርልኝ

ሕዝቤን ላናግር ጠቅላይ ሚኒስቴር !!!

ዶ/ር አብይ አህመድ 
      
    ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጲያኖች የስፖርት ፌደሪሽን በሚያዘጋጀው በዓል ላይ በመገኘትና በጁላይ 6 አርብ በኢትዮጲያ ቀን ላይ ንግግር ለማድረግ ጠይቀዋል፡፡ ጉዳዩ በቅድሚያ በፌዴሬሽኑ ያልታሰበበት በመሆኑ የጠ/ሚ አብይ አህመድን ጥያቄ ለመወያየት የፌዴሬሽኑ ቦርድ በነገው እለት በአስቸኳይ ተሰብስቦ ድምጽ ይሰጥበታል፡፡  ይህን የጠ/ሚ አብይ አህመድን በኢስፋና ጥያቄ የሰሙ የዳያስፖራ አክቲቪስቶች ቦርዱ የጠ/ሚ አብይ አህመድን ግብዣ ውድቅ እንዲያደርገው የቦርዱ አባላትን ስልክ በመበተን የቦርዱ አባላት ላይ ጫና እንዲደረግ ዘመቻ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፌ ኢስፋና ለምን የጠ/ሚ አብይ አህመድን ጥያቄ መቀበል እንዳለበት ያሉኝን ምክንያቶች እና እይታዎች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ይህ ለኢስፋና ትልቅ ድል ነው!!
   ኢስፋና ኢትዮጵያውያን በዳያስፖራ ካፈሯቸው  ተቋማት ውስጥ ግንባር ቀደም እና ምናልባትም እጅግ ጠንካራው ነው ማለት ይቻለል፡፡ ለረጅም ጊዜ ያለማቋረጥ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የመገናኛ ፤ የመቀራረቢያ፤ ሞቷል ተብሎ የነበረ የአገር ልጅ ተገናኝቶ የሚላቀስበት፤ የልጅነት ፍቅር እንደገና የሚታደስበት እጅግ ኢትዮጵያዊ መድረክ ነው፡፡ ይህ መድረክ ለረጅም አመታት እራሱን ከፖለቲካው ገለል አድርጎ በመኖሩም ምክንያት በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመወደዱ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡
    ይህም ሆኖ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በዚህ የአገር ልጆች የአንድነት መገለጫ መድረክ ላይ በነበራቸው ከፍተኛ ጥላቻ የተነሳ ኢስፋናን ለማፍረስ ትልቅ እቅድ አውጥተው ነበር፡፡ እቅዱንም  በሼክ አላሙዲን የፋይናስ ተደርጎለት ዘመቻው ተጧጧፈ፡፡ ሆኖም የህዝብን ልብ ብር አይለውጠውም ሆነ እና በአንድ  ከተማ ውስጥ የኢስፋና ዝግጅት ስቴዲየም ሞልቶ  መቆሚያ ቦታ ሲታጣ መለስ ዜናዊ እና ሼክ አላሙዲን የደገሱበት እስቴዲየም አንድ ሰው እንኳን ዝር ሳይልበት መቅረቱን ምስክር ሆነናል፡፡
   ኢስፋና ሊያፈርሰው ከነበረው መንግስት እና ድርጅት ውስጥ  በቃ በእናንተ መድረክ ተገኝቼ ልናገር የሚል መሪ ማግኘቱ  ኢስፋና በግልጽ ማሻነፉን ያስመሰክራል፡፡ ኢስፋናም  ከመንግስት/ ከገዢው ፓርቲ ገለልተኛ የሆነ ብቻ ሳይሆን ተናንቆም ያሸነፈ መድረክ መሆኑን የሚያስመሰክር  የድል አጋጣሚ ነው፡፡ ስለዚህ ኢስፋና የጠ/ሚ አቢይ አህመድን በእናንተ መድረክ ተገኝቼ ልናገር ጥያቄ ባይቀበል ያሸነፈውን ድል እንደመጣል ይሆንበታል እላለሁ፡፡
የኢስፋና ግብ ይሄን አይነት መድረክ መፍጠር ነው
    በመንግስት እና ሕዝብ መካከል በተፈጠረ እጅግ አላስፈለጊ መቃቃር እና መራራቅ ሆኖ ነው እንጂ የአገራችው መሪ በዝግጅታቸው ላይ እነዲገኝላቸው ጥያቄ ማቅረብ የነበረባቸው የፕሮግራሙ አዘጋጆች የሆኑት ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሰት ከፈጠረው ቁርሾ አንፃር ኢስፋና ግብዣ ሊያቀርብ አይችልም ነበር፡፡ ጠ/ሚ አብይም ይሕን ተገንዝበው  በትህትና በመድረካችሁ ልገኝ ማለታቸው የተፈጠረውን የቁርሾ፤ቂም ጥላቻ እና መናናቅ ድባብ በእጅጉ ይሽራል፡፡
   በአመለካከት ፤በፖለቲካ ፤የተለያዩ የአገር ልጆች እንደገና እንዲተያዩ እንዲወያዩ አዲስ እድል ከፍታል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢስፋና እስከአሁን ሲያደርገው ከነበረው  ስራ ጋር የሚሄድ ፤የሚስማማ ፤የሚደጋገፍ እርምጃ ነው፡፡  ጠ/ሚ አቢይ አህመድ ሕዝቤን ላናግር  ከሕዝቤ ጋር ልነጋገር ፍቀዱልኝ ሲሉ ኢስፋና ካለው ኢትዮጵያውያንን የማቀራረብ ግብ አንጻር ጉዳዩን አፋጥኖ ለጠ/ሚ አብይ ጥያቄ በመልካም ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ በተጨማሪም በዚሁ ዝግጅት ላይ የክብር እንግዳ ሆኖ ቀድሞ የተጋበዘው ጀግናው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ እና ጠ/ሚ አብይ አህምድ በአንድ መድረክ ላይ ኢትዮጵያውያንን አነጋግረው እነሱም ቁጭ ብለው የተለያየ ሀሳብ ይዘው ስለአገራቸው እንዲያወሩ እንዲነጋገሩ ከማስቻል የበለጠ ኢትዮጵያውያን እንዲቀራረቡ የማስቻል ድል አለን? የኢስፋና ግብስ የህ አይነት ሁሉን አቀፍ መድረክ መሆን አይደለምን?
 ይሄ ለኢስፋና ትልቅ ክብር ነው  
   በአንድ ዝግጅት ላይ የሀገር መሪ ሲገኝ ከሀገር መሪው ጋር አብሮ የሚንቀሰቀሰው የሚዲያ ፤የፖለቲካ፤ የዲፕሎማሲ፤ የፕሮቶኮል  ኃይል እና ግርማ አብሮ ይመጣል፡፡ እስከአሁን ኢስፋና ዝግጅቶቹን በሚያዘጋጅባቸው ከተማዎች ሁሉ የከተሞቹ ከንቲባዎች፤ የግዛቶቹ ሴናተሮች እና ገቨርነሮች ዘንድ ከፍተኛ ተወዳሽነት እና ተደናቂነት ተደማጭነት አግኝቷል፡፡
      ኢስፋና የጠ/ሚ አቢይ አህመድን ጥያቄ በመልካም ቢያስተናግድ ግን ከዚህ በፊትም አይቶትም ሰምቶትም የማያውቀውን እና ለረጅም ተከታታይ አመታት የሚከተለውን የሚያተርፍበትንም ፖለቲካዊ ማሕበራዊ ኢኮኖሚያዊ ሞገስ በአሜሪካውያን እና በአሜሪካዊ ተቋማት ፊት ያገኛል፡፡ ሁል ጊዜም እንደተለመደው  መንግስታቸው ያሳደዳቸው፤ ከመንግስታቸው የተጣሉ ከሚል አሰልቺ ተረክ አዙሪት አውጥቶ እነዚህ እኮ  በመንግስተቻው እውቅና የተሰጣቸው መንግስታቸው ያከበራቸው ናቸው መባል በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ይሄ የተረክ ለውጥ እና አብሮት የሚመጣው የኢኮኖሚ ለውጥም ለኢስፋና ብቻ ሳይሆን ለመላው ዳያስፖራ የመዳረስ አቅምም አለው፡፡
ታሪካዊ አጋጣሚ አያምልጠን 
   የቀድሞው ነገስታቶቻችን ተወደዱም ተጠሉም ገበሬው የተናገረውን  አዝማሪው የዘፈነውን፤ ወታደራቸው ተናገረውን፤  ጭሰኛቸው ያንሾካሸከውን፤ ካሕናቶቻቸው የተቀኙትን የሚያደምጡ ከእነሱም ጋር የሚከራከሩ የራሳቸው ከሕዝባቸው ጋር የመነጋገሪያ መድረክ  ዘይቤ  የነበራቸው ጠቢቦች ነበሩ፡፡ ከአብዮት በኋላ ያየናቸው የሀገራችን መሪዎች ግን ሕዝበ ሊያገኛቸው፤ ሊያናግራቸው ቢፈልግ እንኳን ከሕዝብ የሚሸሹ ፤እነሱ እራሳቸው መቶ በመቶ በተቆጣጠሩት መድረክ ካልሆነ በነፃ መድረክ ላይ ቀርቶ ተራ የእድር መድረክ የሚሸሹ ድንቡር  መሪዎች ናቸው፡፡
   ጠ/ሚ አብይ አህምድ ሌላው ሁሉ ቢቀር ይህን የአብዮት አመጣሽ ባሕል ሰብረው በእናንተ መድረክ ልገኝ የማለታቸው  ብቻውን ምን ያህል የለውጥ ታሪካዊ አጋጣሚ እጃችን ላይ እንዳለን ያስመሰክራል፡፡ ይህ ሕዝብ እና መንግስት ስደተኛ እና በባለ አገር  መካከል የማቀራረብ የታሪክ  አጋጣሚ ፈጸሞ ላይመለስ ይችላል፡፡ ይሄ ልዩ ድልድይ መገንባት ታሪካዊ አጋጣሚ እውን እንዲሂሆን ግን ጠ/ሚ አብይ ብቻቸውን ምንም ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ኢስፋና የጠ/ሚ አብይ አሕመድን ጥያቄ በበጎ በመመለስ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ላይ አሻራውን ያስፍር፡፡
    በጠ/ሚ አብይም ሆነ ገዢው ፓርቲ  ላይ ተቃውሞ ያላቸው ኢትዮጵያውያን  ታዳሚዎች በዝግጅቱ ወቅት ስርአት ባለው መልኩ ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙበት የሚያንጸባርቁበት ስፍራ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ግን ለተወሰኑ አክቲቪስቶች ዘመቻ ፤ዛቻ እና ጫጫታ ሲባል ብቻ ከሀገራችን መሪ ጋር በክብር የመነጋገር አጋጣሚ ማጣት ፈጽሞ ተገቢ አይደለም ኢስፋናንም የሚመጥን እርምጃ አይደለም፡፡
   አዎ እኔን ጨምሮ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ከመንግስታችንም ሆነ ከገዢው ፓርቲ ጋር ብዙ ብዙ አጀንዳዎች አሉን፡፡ ሁልም አጀንዳዎች መልሱ ግን ዘመቻ አላናግርም አንነጋገርም የሚል ጫጫታ አይደለም፡፡ ለመጮህም ስፍራ እና ጊዜ አለው ለመነጋገር አና ለመደማመጥም ስፍራ እና ጊዜ አለው፡፡ የዳያፖራ ማሕበረሰብ ከዚህ በኋላ ከመንግሰት እና ገዢው ፓርቲ ጋር ላለው በርካታ ውይይት፤ ክርክር እና ድርድር ይህ እነደውም በጎ ታሪካዊ አጋጣሚሚም ነው፡፡ ኢስፋናንም ወደ ታላቅ ማሕበራዊ መድረክ ከፍ የሚያደርገው አጋጣሚ ነው እላለሁ፡፡
 ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
        ***

ቀልደኛው ዐቢይና የ”ጋብዙኝ?” ሸፍጠኛ ጥያቄው!

አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ጠቅላይ ሚንስትር (ጠቅላይ ዋና ሹም) ዶ/ር (ሊ.ማ.) ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ በየዓመቱ በደመቀ ሁኔታ በሚያኪያሒዱት የስፖርት (የፍን፤ ፍን ሲነበብ ን ትጠብቃለች) በዓል ላይ በእንግድነት ለመገኘት እንዲፈቀድላቸው የ”እባካቹህ ጋብዙኝ?” ጥያቄ በደብዳቤ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎም የስፖርት ፌዴሬሽኑ (የፍን ነጻ አሥተዳደሩ) ቦርድ (ባለአደራ) በጉዳዩ ላይ ለመምከርና ምላሽ ለመስጠት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያደርግ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የአሜሪካውም ሆነ የአውሮፓው ቦርድ (ባለአደራ) “የተሳሳተ ውሳኔ ያስተላልፉ ይሆናል!” የሚለው ሥጋቴ በማየሉ ነው ይህችን ጽሑፍ ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ ሥጋቴ የመነጨው ከወያኔ ነውረኛ ማንነትና ወራዳ ተግባር ነው፡፡ እንዴት? ቢባል ወያኔ በጀርባ በኩል ሔዶ ዐቢይ ሊጋበዝ እንደሚችል ሳያረጋግጥ ጥያቄውን ያቀርባል ብየ ላምን አልቻልኩም፡፡
በተለይ ደግሞ ወያኔ ከዚህ ቀደም የሰሜን አሜሪካውን የስፖርት ፌዴሬሽን (የፍን ነጻ አሥተዳደር) ለመቆጣጠር ወይም በእጁ ለማስገባት ብዙ የደከመና ቀላል የማይባል ችግርም የፈጠረ መሆኑ ሲታሰብ ወያኔ ከዚህ የስፖርት ፌዴሬሽን (የፍን ነጻ አሥተዳደር) ጋር ግንኙነት መፍጠር ሲያስብ ውጤቱ ወይም ምላሹ ያማረ እንዲሆንለት ምን ያህል ዝግጅትና ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚችል እንዲሁ መገመት ይቻላል፡፡
በመሆኑም ወያኔ አስቀድሞ የቤት ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ ነው ጥያቄውን በአንባሳደሩ (በእንደራሴው) ካሳ ተክለብርሃን በኩል በደብዳቤ እንዲቀርብ ያደረገው የሚል ግምት አለኝ፡፡ እናም አብላጫውን የቦርድ (የባለአደራ) አባላትን ድምፅ ዶላር ረጭቶ፣ ወይም በሌሎች ጥቅሞች ደልሎ ገዝቷል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ይሄ ግምቴ ትክክል የሚሆነው ባለአደራው ተሰብስቦ ዐቢይ በዓሉ ላይ እንዲገኝ በድምፅ ብልጫ ከፈቀደ ወይም ከወሰነ ነው፡፡
ዐቢይ እንዲገኝ ካልፈቀደ ግን ወያኔ የባለአደራ አባላትን በዶላር ወይም በጥቅም ለመደለል ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቶ የባለአደራ አባላቱ ለሕሊናቸው ለሀገርና ለሕዝብ ታማኝ በመሆን መወሰናቸውን ያረጋግጣል፡፡ አንድ ነገር ግን እርግጠኛ ልትሆኑ ትችላላቹህ፡፡ ወያኔ በጎን የባለአደራ አባላትን ለመደለልና ለማግባባት ጥረት ሳያደርግ ጥያቄውን ሊያቀርብ እንደማይችል፡፡
ወያኔ ጥያቄውን ከማቅረቡ በፊት የባለአደራ አባላትን በጎን ለማነጋገር የሚገደድበት ሌላኛው ምክንያት ፌዴሬሽኑ (ነጻ አሥተዳደሩ) በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ፌዴሬሽኑን (ነጻ አሥተዳደሩን) ከማንም ያልወገነ ለማድረግ በማሰብ ፖለቲከኛን በክብር እንግድነት መጋበዝ እንደሌለበት የሚከለክል አንቀጽ ያለ በመሆኑ ነው፡፡
ይሄንን አንቀጽ ወያኔ ስለማያውቀው ነው ጥያቄውን ያቀረበው እንዳይባል ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በክብር እንግድነት ሊጋበዙ ከታሰቡ በኋላ በዚህ አንቀጽ ምክንያት ሳይጋበዙ የቀሩ እንግዶች መኖራቸውን ወያኔ አሳምሮ ያውቃል፡፡ ይሄን እያወቀ ጥያቄውን ማቅረቡ መተዳደሪያ ደንባቸው ቢከለክልም ጥያቄውን በልዩ ሁኔታ (in exceptional case) ለማስተናገድ መታሰቡን ያመለክታል፡፡
“ዐቢይ ይሄንን መድረክ ለምን ፈለገው?” ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሁለት ዐበይት ምክንያቶች አሉ፦
1ኛ. ዋነኛው ምክንያት በዳያስፖራ (በሀገረ ግዩራን) ያሉ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ እየወጡና በሌሎችም መንገዶች በየጊዜው በወያኔ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ እንደመሆናቸው መጠን ይሄም ጉዳይ ግዩራን ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው ሀገራት መንግሥታት ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ጉዳይ እንደመሆኑና በዚህም ምክንያት በወያኔ እና በእነኝህ መንግሥታት መሀከል የግንኙነት መሻከር ስለተፈጠረ ዐቢይ በዚህ በዓል ላይ በክብር እንግድነት እንዲገኝ መደረጉ ለእነኝህ ሀገራት መንግሥታትና ባጠቃላይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው ትርጉም ለወያኔ እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆነ ነው ወያኔ ዐቢይ እዚያ እንዲገኝ የፈለገበት አንደኛው ምክንያት፡፡
2ኛ. ሁለተኛው ፋይዳ ደግሞ ዳያስፖራውን (ግዩራኑን) አግባብቶ ደልሎ ከወያኔ ጎን እንዲሰለፍ ለማድረግ፣ አንድነቱን ለመከፋፈል፣ በዳያስፖራው ያለውን ተቃውሞ ማምከን እንኳ ባይቻል ለመፈረካከስ በማሰብ ነው፡፡
ዐቢይ በእነዚህ በዓላት መድረኮች መገኘት ቢችል ያለምንም ጥርጥር እነኝህን ድሎች ያገኛል፡፡ በመሆኑም ወያኔ ዐቢይ እዚያ እንዲገኝ የፈለገበት ምክንያትና ዓላማ እንዲህ ቀላል አይደለም፡፡ ከወቅታዊ ችግሩ አኳያ ከባድ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ፋይዳና እንድምታ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ለቀላል የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ አይደለም ወያኔ ዓይኑን በጨው አጥቦ ዐቢይ እዚያ መድረክ ላይ እንዲገኝ ጥያቄውን ያቀረበው፡፡
የፌዴሬሽኑ (የነጻ አሥተዳደሩ) የባለአደራ አባላት በአንዳች ነገር ካልተያዙ ወይም ካልተገዙ በስተቀር መተዳደሪያ ደንባቸውን ጥሰው ዐቢይን በመቀበል ቁማርተኛው ሸፍጠኛው ወያኔ በሜዳችን ላይ ነጥብ አስጥሎን ወይም አስቆጥሮብን እንዲወጣ ያመቻቻሉ ይፈቅዳሉ የሚል እምነት አይኖረኝም፡፡ ጉዳዩ ለወያኔ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፡፡ ይሄ ምን ማለት እንደሆነ ይገባቸዋል ብየ እገምታለሁ፡፡ ከመሰብሰባቸው በፊት ይሄንን ጽሑፍ የጻፍኩትም ለዚሁ ነው፡፡ ከግንዛቤ ጉድለት አኳያ ከተሳሳተ ውሳኔ ላይ እንዳይወድቁ ለመታደግ፡፡ የባለአደራ አባላትን የምታውቋቸው ወገኖች ተሰብስበው ከመወሰናቸው በፊት ይሄንን ጽሑፍ እንድታደርሷቸው እጠይቃለሁ፡፡
እናም የዐቢይ እነዚያ ቦታላይ መገኘት የሚጠቅመው ወያኔን ብቻ ነው፡፡ ለሕዝብ ግን ዐቢይ እዚያ ተገኝቶ መለፈፉ ምንም የሚፈይድለት ነገር ስለሌለ የባለአደራ አባላቱ “ለሕዝብ ጥቅም ብለን ነው!” ብለው ሊጠቅሱት የሚችሉት አንድም ጥቅም ስለሌለ በሕዝብ ጥቅም በማመሃኘት ሊፈቅዱ አይችሉም አይኖርባቸውምም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚበቃውን ያህል ከዚያም በላይ የዐቢይን ልፈፋ ጠጥቶ ጠግቧል፡፡ ሌላ ተጨማሪ ልፈፋ መስማት አይደለም አሁን የሚፈልገው፡፡ ተግባር ነው አሁን ማየት የሚፈልገው፡፡
ፌዴሬሽኑ (ነጻ አሥተዳደሩ) የዶ/ር (የሊ.ማ.) ዐቢይን ጥያቄ የማይቀበለው ከሆነ በሚሰጠው ምላሽ ይሄንን የሚከተለውን ቢል ደስ ይለኛል፦
“ጠቅላይ ዋና ሹም ዶ/ር (ሊ.ማ.) ዐቢይ አሕመድ ሆይ! በቅድሚያ ለፌዴሬሽኑ (ለነጻ አሥተዳደሩ) ክብር ሰጥተው ጥያቄውን በማቅረብዎ ላቅ ያለ ክብርና ኩራት ይሰማናል፡፡ ሕዝቡን ፊትለፊት አግኝተው ንግግር ለማድረግና ከሕዝቡ ጋር ለመግባባት ያለዎትን ከፍተኛ ፍላጎት እንረዳለን፡፡ ይሁንና ግን 1ኛ. የመተዳደሪያ ደንባችን የሚከለክል በመሆኑ፡፡ 2ኛ. ዳያስፖራው (ግዩራኑ) የሀገሩን ጉዳይ በንቃት የሚከታተል እንደመሆኑ እርስዎ በየ ክፍለሀገሩ (ክልሉ) እየዞሩ ያደረጉትን ንግግርና ውይይት በጥሞና ተከታትሏል፡፡ ዳያስፖራው (ግዩራኑ) በነዚያ ንግግርና ውይይት ባደረጉባቸው መድረኮች ከተነሡት ቁምነገሮችና የሕዝብ ጥያቄዎች የተለየ ጥያቄና ፍላጎት የሌለው ስለሆነ እዚህ እንዲገኙ ፈቅደን ውድ ጊዜዎትንና የሀገርን ውድ የውጭ ምንዛሬ ማባከን አልፈለግንም፡፡ በእርግጠኝነት ልናሳውቅዎ የምንፈልገው ጉዳይ ግን ለቃልዎ ታምነው ለሕዝብ የገቡትን ቃል ተግብረው የተናገሩትን ለውጥ ማምጣት ከቻሉ ያኔ በሕዝባችን መሀል ያለው የጥልና የልዩነቱ ግንብ ስለሚፈርስና እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ አንድ ብሔራዊ መግባባት ላይ ስለምንደርስ “ደንባችን ይከለክለናል!” ሳንል በሚቀጥሉት የውድድር ዘመናት ወይም በዓላት እርስዎ ሳይሆኑ እኛ ራሳችን በክብር ጋብዘን በታላቅ ድምቀት የምንቀበልዎ መሆኑን በአክብሮት ልንገልጽልዎ እንፈልጋለን፡፡ እኛና እርስዎ በዚህ መድረክ መገናኘት ካለብን ትክክለኛ ሰዓቱ ለሕዝብ የገቡትን ቃል መፈጸምዎ ከታወቀ በኋላ እንጅ አሁን አይደለምና በጠቀስናቸው ምክንያት ጥያቄዎትን ባለመቀበላችን ይቅርታ እየጠየቅን ትኩረትዎን ወደ ተግባራዊ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንጠይቃለት!” ብሎ ባለአደራው መመለስ ይኖርበታል፡፡
ነገር ግን ይሄ ሳይሆን ቀርቶ የባለአደራ የአሥተዳደር አባላቱ ክህደት ፈጽመው ዐቢይ እንዲገኝ ከፈቀዱ ግን ዳያስፖራው (ግዩራኑ) በበዓሉ ወይም በዝግጅቱ ቦታ ባለመገኘት ተቃውሞውን እንዲገልጽና ብዙ የደከመበትንና ፍሬም እያፈራ ያለውን የተቃውሞ ትግሉን ከኪሳራ እንዲታደግ ከወዲሁ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ከበዓሉ በኋላም እነኝህን ክህደት የፈጸሙ የባለአደራ አባላትን የማስወገዱንና በታማኝ የሕዝብ ልጆች የመተካትን እንቅስቃሴ ወዲያውኑ መቀጠል ይኖርበታል እላለሁ፡፡ ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ነኝ ካለ መቸም ቢሆን ከሕዝብ ጎን ሊቆም ይገባል! ከሕዝብ ጎን ካልቆመ ግን የሕዝብ አይደለም! የሕዝብ እንዲሆን ሕዝቡ ይንቀሳቀሳል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
Filed in: Amharic