>

የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ (አንዷለም ቡከቶ ገዳ)

አንዱ ብስል አንድ ጥሬ ..ግንቦት 18 …2010….ወያኔ ሸገርን ልትይዝ 2 ቀን ቀራት ፡፡(አባባሉ ርእስ ነው …ያው አብይን ለመንካት ነው…ጸሃፊው እኔው ነኝ)

በሰላም ናችሁ ጋይስ!? ዌል እንግድክ በዚህ” ሶሻል ክራይስስ” በሆነ የሶሻል ሚዲያ ላይ ዛሬ ምን አዲስ ነገር አለ ?!(ሃይሌ ስታይል…በነገራችን ላይ ፈረንጆቹ ሃይሌን “ከሌላ ፕላኔት የመጣው ሰው!” ይሉት የነበረው በሩጫው ይመስለኝ ነበር ለካ በንግግሩ ነው!ሎል ….አሁንማ አፉን በከፈተ ቁጥር ያቃጥለኝ ይዟል….!)

እናም አቶ አያልቅበት (ጋሽ አብይ) ሰሞኑን ደግሞ ምን አዲስ ነገር አምጥተው ይሆን ብዬ በየታይም ላይኑ ስልከሰከስ በቀደም በቤተመንግስታቸው ግብር ባበሉበት ወቅት “ሰው እብድ ቢለኝም ግብጽ ድረስ ሄጄ በዳኢሽ የታረዱ ወገኖቻችንን ሬሳ ይዠ እመለሳለሁ!” ብለዋል አሉ …..የሚል ነገር አይቼ ስደመም ከረምኩ፡፡በእውነቱ የሚገርም ሀሳብ ነው! ካደረጉትና ከተሳካላቸው( እንደጉዳዩ አፈጸጸም ከሆነ የሰማእታቱን ሬሳ ማግኘቱና መለየቱ በራሱ ትልቅ እንቆቅልሽ ይመስለኛል…… መቼም ዳኢሽ አንገታቸውን ቆርጦ ሲጥል ለተቀረው አካላቸው ስማቸውን እየጻፈ መቃብር ይሰራላቸዋል ብዬ አላስብም ! ግን በሆነ መላ ብቻ ጠሚው ከቻሉና ድሮውንም በገቡት ቃል መሰረት “እኛ ኢትዮጲያውያን ስንኖር ኢትዮጲያዊ ስንሞት ኢትዪጶያ እንሆናለን” በሚለው ታዋቂ ብሂላቸው መሰረት ውድ ወገኖቻችንን ላገራቸው አፈር ካበቋቸው ያለማንም ተ.ካ. አስገዳጅነት ቆሜ ነው የማጨበጭብላቸው….ስለ ዜጎቹ በተለይ ውጭ ስላሉት ዜጎች (ከሚልኩት ዶላር ውጪ) ቅንጣት ታህል የማይጨነቅ የነበረ ሬሳ መንግስት ከምኔው በሰው አገር የወደቀን የወገን ሬሳ ወደ ማምጣት አብየታዊ የለውጥ ሽግግር እንዳደረገ ማየት ራሱ እኮ አስገራሚ ነው፡፡

እናም በአጭሩ ምንም እንኳን ቋ ተ. (ቋሚ ተቃዋሚ) ብንሆንም ዶ/ር አብይ ሃሳቡን በማሰባቸው ብቻ (በነገራችን ላይ “ሃሳቡ ግን እንዴት መጣለት!?” የሚለው በራሱም እኮ አስገራሚ ነው….ለማብራራት ያህል .. ቤተክህነት ሟቾቹን ሰማእት ብላ ሰይማቸዋለች …(ለነገሩ ስያሜው የመጣው ሟቾቹ በቫቲካን እውቅና ከተሰጣቸው በኋላ መሆኑን ስናይ ጉዳዩ “ውስጡን ለቄስ “እንደሆነ ግልጽ ነው…..”ውይ አንዲ ደግሞ ድሮስ የቤተክህነት ጉዳይ ውስጡን ለቄስ ካልሆነ ውስጡን ለማን ይሁንልህ?!” የሚል አይጠፋም….ሎል) እናም ቤተክህነት እንኳን ውል ያላለባትን ሃሳብ እኚህ የልጅ አዋቂ መሪ ከየት ሃሳቡን እንዳመጡት ሳስብ ..አንዳንዴ ሰውየው የምር ለየት ይሉብኛል!…….

ግን ደግሞ በጉሊት ለመተዳደር የመጠረችን ምስኪኗን እና ምንዱባኗን አዜብ መስፍንን የጮምዬው የሜቴክ የቦርድ አባል አድርገው ያለመደችውን በምቾት ሲያንገላቷት ሳይ፡ ጥቂት ሚሊዮን ዶላሮች እና አንድ ሃያ የመሬት ካርታ ቤቱ ውስጥ የተገኘበትን አቶ ገብረዋህድን አብይ በብሄራዊ እርቅ ስም ማንም ፍታልኝ ሳይለው ልፍታው ሲል (ይሄ ብሄራዊ አረቄ እንጂ ብሄራዊ እርቅ ያመነጨው ሃሳብ አይመስለኝም!ሎል) ፡……አንዳርጋቸውን ፍታልን ብሎ ለጠየቀ ህዝብ ገብረዋህድን መፍታት ማለት ጌታን ለመፍታት በተሰየመ ሸንጎ በርባንን መፍታት አይነት ጲላጦሳዊ ፍርደገምድልነት መሆኑን ያልተረዱ መሆናቸውን ሳይ፡…አዲስ ካቢኔ አቋቁማለሁ ብለው በህይወት እንዳለ እንኳን የረሳነውን የድሮውን ተሾመ ቶጋን ሲጎትቱ ሳይ ….. በእውነቱ “አይ የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” ያስብሉኛል……በእርግጥ አንዳንድ ስለ አንዲ ማኛ ነብስ የማያውቅ ፍልጥ “አንተ በእነ ገብረዋህድ የከፋህ ችግርህ ከትግሬ ነው እንዴ!?” ብሎ ፍልጣዊ ጥያቄ ሊያነሳም ይችላል…እኔ ..ከትግሬነታቸው ችግር የለብኝም ……ትግሬነት ወይም “ትግሬ ተለይቶ ተጠቃ” የሚለውም የመሃይም ትርክት የሙሰኛ ሌባ ባለስልጣናት መሸሸጊያ ዋሻ መሆን የለበትም………በቃ! ….አቶ ገብረ ዋህድ 20 የቤት ካርታ ተገኘባቸው ተብሎም ነበር ….”ሰውየው እኮ ዝም ቢባሉ እንደነበራቸው የመሬት ስብስብ አንቀጽ 39ን ጠቅሰው ሊገነጠሉ ጫፍ ደርሰው ነበር!” ሲባል አልነበረም እንዴ?! …ሎል…..እኮ አብይ ማን ፍታልኝ ብሎት ነው እሳቸውን የፈታው..!?….በመፈታታቸው እሳቸውስ ህዝቡስ ምን ተማረ!? ዛሬ ኤፊ እንዳለው ….ሰውየው ኑ ውጡ ሲባሉ እንኳንስ ሊጸጸቱ “.ድሮም ብዬ ነበር “እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል!” እያሉ አይደል እንዴ ካርታዎቻቸውን በባጃጅ አስጭነው ከቃሊቲ የወጡት?! ..ሃሃሃ ቀልድ ነው ደግሞ…..ይመቾት ጋሽ ገብሬ ! እድሜ ለቄሮ..አሁን ስብሰባ የለ መሳቀቅ የለ ፈታ ብለው ኑሮን ማጣም ነው…ውስኪ የሚያጣጣ ካጡ ደውሉልኝ…..

እሺ ቆይ ከትግራይ ክልል የፖሊት ቢሮም ሆነ ከስራ አስፈጻሚነት ወዘተ እንደ ችግኝ ተመንግለው የተጣሉትንና አሁንስ አለቀላቸው ተብለው የነበሩትን የሟች ሚስት በምን ሂሳብ ነው አብይ አንጓሎ አንጓሎ የቱጃሩ የሜቴክ ቦርድ አባል ያደረጋቸው?! ..ነው ወይስ የቦርድ አባልነት በሜሪት ሳይሆን በድጎማ መልክ የሚታደል የግርማዊነታቸው ችሮታ ነው!? …..እሺ ስራ ከሆነም ስጦታም ከሆነም ለኛም ይድረሰና…!መቸም አንዲ ማኛ አብይ የሆነ ድርጅት የቦርድ አባል ቢያደርግህ በአመት አንድ ግዜ ተሰብሰብህ በየወሩ እየሄድክ ዳጎስ ያለ አበልህን መሰብሰብ ካቃተህ ሞተሃላ!…በቃ አብይ ሙት የሆነ የቦርድ አባልነት ግጨኝና እስቲ በኮሌስትሮል ልሰቃይ!? ለዚች ምስኪን ሀገር ለምን ከፈለክ የአስር ድርጅት የቦርድ አባል አታደርገኝም!! …ያውም ለእምዬ…!?

ግን ደግሞ በዚህ በዚህ እርር ስል ግርማዊነታቸው..”ሞአ ሌንጫ ዘምነገደ ቄሮ ስዩመ ጃዋር ወ ለማ” ባላቸው ሰፊ ቸርነት የነጻነት አርበኛውን ፡ጀግናውን፡ ዘ ዋን ኤንድ ኦንሊ አንዳርጋቸው ጽጌን ፈተው ያስቦርቁኛል…..ምን እላለሁ?!…ከወገቤ ለጥ ብዬ ንጉስ ሆይ ቸርነቶ ወደር የሌለው ምህረቶም እስከአለም ዳርቻ ነውና እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ሺ አመት ይንገሱ ብየ ለጥ እላለሁ፡፡ ግርማዊነታቸው አስከአሁን ድረስ ሼባዎቹን ኦነጎችን ማምስመጣትን ጨምሮ(ይሄን በነገ ፖስት እመለስበታለሁ) ያደረጉትን እጅግ አስገራሚ እና ፈጣን የለውጥ ጉዞ ዞር ብየ አይና ልገረም ስል ሌላኛው ንሜሮዬ(ፈ/ሪ ተክለዋሃዋርያት ስታይል) …”አሄሄ ይቺ እቺ እንኳን ኤች አር 128 በሴነቱ ዘልቆ እንዳይጸድቅ ከአንገት በላይ የምትደረግ የጥድፍያ ለውጥ ነች ….አይ አንቺ አሜሪካን ስንቱን አስደገደግሽው !” ብዬ የሸር ፈገግታ ፈገግ እላለሁ……ወዲያው ደግሞ ” በስመአብ በወልድ …. እስቲ አንዳንዴ እንኳን ቀና ቀናውን አስብ ..ሰውዬው የለውጥ ሰው ናቸው …ብዬ” እራሴን በራሴ ገስጸዋለሁ፡፡

ለማናቸውም ዛሬ የመጣሁት በዋናነት ለነቆራ ሳይሆን ለምስጋና ነው

ስለሆነም ግርማዊነቶ በእርሶ ያገዛዝ ዘመን (60 ቀናት) ያቺ ወንድም ከወንድሙ የተጫረሰባት የግንቦት ሃያ “ድል” በአል እንደ አንድ ድሃ ልደት ደብዝዛ ስትከበር ስላሳዩን (ሰሞኑን በኢቲቪ አልፎ አልፎ በምትመላለስ ማስታወቂያ ነገር ላይ እንኳን “ግንቦት ሃያ” በደቃቃ ፎንት ከጀርባ በለሆሳስ ተጽፋ ያውም በአይተ መለስ ንግግር ሳይሆን ከግንቦት ሃያ ድል መገኘት ጋር ምንም አይነት ግኑኝት በሌላቸው የደ/ር አብይ “የአንድነት ና አንድ አይነትነት ልዩነት ” ንግግር ታጅባ ሳይ)…

በአሁኑ ሰአት በአገሬ እስር ቤቶች ውስጥ በእኔ አቅም አስቤ አስቤ የማውቀው የህሊና እስረኛ ያሌለ መሆን ሳይ

በሰው አገር እንደ ውሻ ይቆጠር የነበረው አበሽ… ዛሬ እንኳንስ እራሱ ሬሳውም ተከበሮ በአገሩ ያርፋል የሚባልበት ዘመን ሲመጣ ሳይ

….ከወገቤ ለጥ ብዬ እጅ ነስቻለሁ፡፡
ይመቾት!
፡….አንዲ እንኳንም ለቤትህ አበቃህ ይመችህ !..አንዲ የሚለውን ስምም ከዛሬ ጀምሮ በክብር መልሻለሁ፡፡

ሌሎቻችሁም
ይመቻችሁ

Filed in: Amharic