>
5:13 pm - Sunday April 19, 3254

የግንቦት 20 ድሎች! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

1. በዐፄ ሠርፀ ድንግል ዘመን ቱርኮች ሀገራችንን ቅኝ ለማድረግ በማሰብ ባሕረ ነጋሽ ይስሐቅን (አሁን ላይ ጥሊያኖች ኤርትራ ያሏት የባሕረ ምድርን ገዥ) በመደለል በገዛ ሀገሩና ሕዝቡ ላይ ክህደት በመፈጸም የሚገዛውን የሀገራችንን ክፍል ይዞ እንዲከዳ በማድረግ ተጀምሮ የነበረው ነገር ግን ወዲያውኑ 1571ዓ.ም. ዐፄ ሠርፀ ድንግል ወደቦታው ዘምተው የከሐዲውን የባሕረ ነጋሽ የይስሐቅንና የወራሪውን የቱርክን ጦር በመደምሰስ ከሽፎ የነበረው፤ በኋላ እንደገና ከአራት ምዕት ዓመታት በኋላ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ለ50 ዓመታት ተነጥሎ የነበረውና ፋሽስት ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በተደረገው ዲፕሎማሲያዊ (የአቅንኦተ ግንኙነት) ጥረት እንደገና ወደ እናት ሀገሯ እንድትቀላቀል በማድረግ እንደገና ከሽፎ የነበረው ለበርካታ ምዕት ዓመታት የተደረገው ሀገራችንን ገንጥሎ የመውሰድ የጠላት ሀገራት ጥረትና እንቅስቃሴ በዚያ ምድር ላይ የእነኝህን ጠላት ሀገራት ዓላማ ግብና አቅድ የሚደግፉ የሚያስፈጽሙ የባሪያ ሥነልቡናና ሰብእና ያላቸው የእፉኝት ልጆችን በማፍራቱ እነኝሁ ዜጎች የሚባሉት የገዛ ሀገራቸውን የማፈራረስ ዓላማ አንግበው በመነሣት አሁን ለጊዜው ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግባት የነበረችውን ባሕረምድር (በባርነት ስሟ ኤርትራን) የገነጠሉና ያስገነጠሉ ገንጣይና አስገንጣይ የጥፋት ኃይሎችን ያገኘንበት፡፡
2. ዜጎች በዘር በሃይማኖት እንዲከፋፈሉ በመደረጉ የነበረ ፍቅራቸው፣ ትስስራቸው፣ መተማመናቸው፣ ሰላማቸው፣ አንድነታቸው እንዲጠፋ ተደርጎ በጠላትነት እንዲፈላለጉ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሲደረግ ያየንበት፡፡
3. ግንቦት 20 ያነገሣቸው የጥፋት ኃይሎች መጥተው ከማየታችን በፊት ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ በፍጹም በማይገመት መልኩ “ሰው እንዲህ ሆኖ ይፈጠራል?” በሚያስብል ደረጃ ጠባብ፣ ግፈኛ፣ አርቆና አስፍቶ ማየት ማሰብ የተሳናቸው፣ የማሳስተውሉ፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ባይ፣ ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማቸውን የነውረኛ የጉድ ፍጥረቶች መንጋ ሀገረ እግዚአብሔር በምትባል ኢትዮጵያ መኖራቸውን ዓይተን ያረጋገጥንበት፡፡
4. በ20/21ኛው መ/ክ/ዘ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ዜጎች የአንድ ብሔር ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ለተለያየ ዓይነት ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ሲዳረጉ ያየንበት፡፡
5. ለሽዎች ዓመታት የኖረች ሀገር ያካበተችው ያቆየችው የኖረችው ያለፈችበት ታሪክ፣ ቅርስ፣ እሴት፣ ማንነት ተቀብሮና እንዲጠፋ ተደርጎ በቦታው ለጥፋት ኃይሎቹ የጥፋት ሥራዎች የሚረዱ ሐሰተኛና የፈጠራ የጥፋት ታሪኮች ሀገር ስትሞላ ያየንበት፡፡
6. “ከምን ጋር የዋለች ጊደር ምን ተምራ ትመጣለች” እንደተባለው በአብዛኛው ቅን፣ ቅዱስ፣ ጨዋ፣ ታማኝ፣ ደግ፣ አዛኝ፣ ተሳሳቢ ከነበረው ሕዝባችን ቀላል የማይባለው ቁጥር ሳይወድ በግዱ ከእነኝህ ጉዶች ክህደትን፣ እብለትን፣ ሐሰትን፣ ሆድ አምላኪነትን፣ ሸፍጥን፣ ማስመሰልን፣ ቀማኛነትን፣ ስግብግብነትን፣ ኅሊናቢስነትን፣ ነውረኛነትን ወዘተረፈ. ተምሮ ሲረክስ ሲባልግ ያየንበት፡፡
7. ቀደም ሲል ከነበረው በተናጠል ይፈጸም የነበረው ከዝምድናና ከትውውቅ የሥራ ቅጥር፣ ከሙክትና በእጅ የመጨባበጥ ሰላምታ ከምትሰጥ ጥቂት ብር ጉቦና የሙስና አሠራር ወደ መቶ ሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች (አእላፋትና ብልፎች) በግልና በቡድን ከሚዘረፍ የሀገር ገንዘብ ዘርን መሠረት ያደረገ የሥራ ቅጥርና የሙስና አሠራ ከመንኮራኩር በፈጠነ ፍጥነት ተወንጭፎ ሲያድግ ያየንበት፡፡
8. ለመሠረተ ልማት ግንባታ ስም የሚመጣው ብድርና እርዳታ በጥቂቱ እጅ የወረደ የጥራት ደረጃ ያለው ብላሽ ሥራ ተሠርቶ አብዛኛው በብድርና እርዳታ የመጣ የሕዝብ ገንዘብ እየተዘረፈ እየተበላ ግለሰቦችና ቡድን ሲበለጽጉበት ሰማይ ሲተኮሱበት ሀገርና ሕዝብ ለድርብርብ ጉዳትና ኪሳራ ተዳርገው በትውልደ ትውልድ ተከፍሎ ከማያልቅ የዕዳ ማጥ ውስጥ ሲጠልቁ ሲሰምጡ ያየንበት፡፡
9. የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገሪቱ የጥቂቶች በመደረጓና እሱ መተፋቱን ዓይቶ በሀገሩ ተስፋ ከማጣቱና ከመቁረጡ የተነሣ ሀገሪቱን ጥሎ የትም ቢሆን ለመሰደድ የሌት ከቀን ሕልሙ የሆነበትና እየተሰደደም ለበረሀ አውሬ፣ ለባሕር ዓሣና ለአሕዛብ ካራ እንደተዳረገ ዕያየ ያላንዳች መደናገጥና ማቅማማት አሁንም ለመሰደድ ሲገደድ ያየንበት፡፡
10. ዜጎች ኢትዮጵያዊያን በመሆናቸው ብቻ ስደት በየሔዱበት ሀገራት የሚዋረዱበት፣ የሚታሰሩበት፣ የሚገደሉበት፣ ኩራትና ክብር የነበረው ኢትዮጵያዊነት እርግማን ሆኖ በዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ብሔራዊ ውርደት ተከናንበን ተሸክመን ስንቀመጥ ያየንበት፡፡
11. እንደ ሰባዎቹ (1961-1970ዓ.ም.) ዘመናት ወጣቶች ትውልዱ ጠያቂ ሞጋች ተቆርቋሪ አፋጣጭ፣ ሞትንም እንኳ ሳይፈራ የዜግነት ኃላፊነቱንና ግዴታውን ለመወጣት የሚተጋ ሆኖ ሥልጣናቸውና ደኅንነታቸው ችግር ላይ እንዳይወድቅ በማሰብ ትውልዱን ለማፍዘዝ ለማደነዝ በተሠራው ሥራ ትውልዱ በደረሰበት የቅስም (የሞራል) ልሽቀት ስብራት ድቀት ውድቀት የተነሣ ነፍዞና ደንዝዞ ድሮ ድሮ የድሩየነት የወሮበላነት የከንቱነት መለያ የነበረው ጫት ቃሚነትና ሱሰኝነት የዱርየነት መለያ ከመሆን ወጥቶ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችና መምህራን መለያ ሲሆን ያየንበት፤ አሁን አሁን ደግሞ በየቢሮው (በየመሥሪያ ቤቱ) በግላጭ ሲያመነዥኩትና ሲጠቀሙት ያየንበት፡፡
12. የትምህርት ጥራት ድራሹ ጠፍቶ እንኳን ሌላ ስማቸውን እንኳ አስተካክለው የማይጽፉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎችን ያየንበት፡፡
13. በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኃላፊነቱንና ግዴታውን የማያውቅ፣ የሀገር ፍቅር ስሜቱ የሞተ፣ ለማንነቱ ለክብሩ ለኩራቱ ክብርና ዋጋ የማይሰጥ፣ ከሆዱ በቀር ምንም የሚያሳስበው የሌለው፣ ለሆዱ ሲል ሀገሩን እናቱን ሌላው ቀርቶ “እኔ ከሌለሁ መቸ ልበላው ነው?” ብሎ እንኳ ሳያስብ ራሱንም የሚሸት ትውልድ ፈርቶ ያያንበት፡፡
14. የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቶ ሀብታም፣ መሀከለኛ፣ ድሀ የሚባል የነበረው የዜጎች የኑሮ ደረጃ ፈርሶ ማዕከላዊውን አጥፍቶ በጣም ጥቂት የናጠጡ ሀብታሞችን ጥቂት ድሆችንና እጅግ በጣም ብዙ የድሀ ድሀዎችን በመፍጠር የኑሮ ደረጃዎች ሲዛቡ ያየንበት፡፡
15. የሀገሪቱ ቅርስና ባለውለታ የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ፣ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋ፣ ክብሯ፣ መታፈሯ፣ መፈራቷ ተጥሶ ተድሶና ተገርስሶ የምናምንቴዎች መጫወቻና መቀለጃ ስትሆን ያየንበት፣ ምናምንቴዎቹም “እንዳታንሰራራ አድርገን አከርካሪዋን ሰብረናል!” ብለው ሲፎክሩ የሰማንበት፡፡
16. ኧረ የግንቦት 20 ፍሬ ስንቱ ተወርቶ ይዘለቃል? እናንተን ሥራ ማስፈታት ይሆናል እንጅ ዓመት ቢወራ ያልቃል እንዴ! ባጠቃላይ ግንቦት 20 ኢትዮጵያ የጨለማ ዘመኗን ሀ ብላ የጀመረችበት፣ ሕዝብ ሀገሩን የተቀማበትና በገዛ ሀገሩ በቀየው በመንደሩ ግፍ ሰቆቃ የሚቆጥርበት የሚጋትበትን፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የወደቀችበት ሕዝቧ እንደ ሕዝብ የተዋረደበትን የአጋንንት መንጋና ዘመን ያገኘንበት ዕለት ነው ግንቦት 20፡፡
መድኃኔዓለም ክርስቶስ ፈጥኖ ከእንቅልፋችን ቀስቅሶ ማቃችንን አውልቀን እንድንጥል ያስችለና!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው amsalugkidan@gmail.com
Filed in: Amharic