>

በፈውስ ሥም መሸቀል… (በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

ስለዚህ ጉዳይ ምንም ሳልናገር፣ አድፍጬ ለማለፍ ሞክሬ ሞክሬ መታገስ አልቻልኩም። ሰሞኑን “መምህር” ግርማ የተባሉ “ፈዋሽ ነኝ” ባይ የአእምሮ መታወክ የገጠማትን ታላቋን አትሌት ጌጤ ዋሚን የገበያ ምንጭ ለማድረግ (በእርሳቸው አስተሳሰብ) ሰይጣኑን እያስለፈለፉ ቪዲዮ አስቀርፀው በይነመረብ ላይ ለቀውታል። ሰውየው ማይክራፎን ደቅነውባት እሷን ሲያጮዃት ልብ የሚሰብር ትእይንት ነበር። አሠራሩ በየጠበሉ የተለመደ ቢሆንም የእርሳቸው የሚለየው ካሜራ ተደቅኖ፣ ሰይጣኑ ወይም የሰይጣኑ መንፈስ ቃለ መጠይቅ የሚደረግለት መሆኑ ነው። ከሁሉም በላይ ያሳዘነኝ ግን “የመምህሩን” ድርጊት ወገባቸውን አስረው የሚከራከሩላቸው ሰዎች አበዛዝ ነው። በጣም አሳፍሮኛል። እሺ “ሰይጣኑ በዚህ ስርዓት ወጥቶ ሔደ? አሁን ጌጤ ዋሚ ዳነች?” ለመሆኑ ሰዎቹ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካለፉ በኋላ የሚሆነውን ተከታትለን አይተን እናውቃለን?
እውነቱን ለመናገር ይህ የእርሳቸው ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሰፈሬ ማርያም ፀበል የሚባል አለ። በዚያ በኩል በየቀኑ ሳልፍ፣ በድሮ ዘመን የቀረ እግር ከወርች የታሰሩ የአእምሮ ሕመምተኞችን በየመንገዱ ዳር ተኮልኩለው አያለሁ። አያያዛቸው በራሱ ለሌላ በሽታ የሚዳርግ ነው። እንጦጦን ትንሽ አለፍ እንዳላችሁ ሽንቁሩ ሚካኤል የሚባል ብዙ በሽተኞች የሚሰበሰቡበት ጠበል አለ። እዚያ መሔድ ሕይወታችሁን እንድትጠሉ ነው የሚያደርጋችሁ። በሥመ ሰይጣን የአእምሮ ሕሙማን እግር ከወርች ታስረው የሚሰቃዩበት መንገድ ‘ተቋማዊ የሰብኣዊ መብት’ ጥሰት ሊባል ይችላል። ነገር ግን በሃይማኖት ሥም ስለሚደረግ ማንም “ኧረ ይሄ ጭካኔ ይቁም” ብሎ መተንፈስ አይችልም። በጣም የሚያሳዝነው የድርጊቱ (የበደሉ ፈፃሚዎች) የሚያስሩት፣ የሚደበድቡት እና የሚያሰቃዩት ሰይጣኑን ነው ብለው ስለሚያስቡ የሰዎቹ አካል ስቃይ ቅንጣትም አይሰማቸውም። ታማሚዎቹም ሰይጣን ያለባቸውን መሆኑን አምነው ራሳቸውን እንዲጠራጠሩ ነው የሚያደርጋቸው።
ብዙ ሰዎች በአፍንጫቸው ሥር ይሔ ሲደረግ ዝም ብለው በፕሮቴስታንቶች ቤት “የፈውስ” ግፎች ላይ ያላግጣሉ፤ በየጠንቋይ ቤቱ የሚደረገውን ብዝበዛ እና ግፍ ያወግዛሉ። እውነቱን ለመናገር በምስኪን በሽተኞች እና ችግረኞች ጉጉት ላይ ታዕምራዊ ኃይል ያለ እያስመሰሉ በሚሸቅሉት የተለያዩ ሰዎች እና ተቋማት መካከል ያለው ልዩነት የኃይል እና የተከታይ ብዛት ልዩነት ነው። የኃይለኞቹ ቡድን የፈለገ ቢያጠፋ፣ የፈለገ ቢበድል አይወቀስም። አነስተኛ ኃይል ያለው ግን ይብጠለጠላል፣ ሕጋዊ እርምጃም ይወሰድበታል።
የችግሩ ዋነኛ መንስዔ አለማወቅ (ignorance) እና ድህነት ናቸው። አለማወቁ በሥማ በለው አንድ እንኳ ተጨባጭ መረጃ ሳይዙ በመንጋ መንጎድን ያስከትላል። የአእምሮ መታወክን ከሰይጣን እና መንፈስ ጋር ማያያዝ አንዱ የአለማወቅ መዘዝ እና ጦስ ነው። በሌላ በኩል ደሞ ድህነት አለ። በርግጥ አለማወቅ እና ድህነት ተያያዥ ናቸው። የአእምሮ ሕመምተኞች ሔደው የሚታከሙበት በቂ የሕክምና ማዕከል በኢትዮጵያ የለም። ያሉትም ጋር ለመሔድ ቤተሰቦች አቅም የላቸውም። ስለዚህ ነገሩን ለፈጣሪ መተዉ ይቀላል። ነገር ግን እነዚህ “የፈውስ” ቦታዎች የመከራ ቦታዎች ሆነዋል። ቢያንስ አንዴ እንኳን ቆም ብሎ ማሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
ከዚህ በፊት የኤችአይቪ ወረርሽኝ ሲስፋፋ አጥማቂዎች ራሳቸውን “ተአምረኛ አዳኝ” አድርገው ወጥተዋል። እንዲያውም የሕክምና መድኃኒት እየወሰዱ ሲጠመቁ መድኃኒቱ አይሠራም በሚል ሰበካ ትልቅ እልቂት ተከስቶ ነበር። ይህ እንዲቆም ፓትርያርኩ በአደባባይ መድኃኒት እየወሰዱ ጠበሉን መጠመቅ ችግር እንደሌለው እስከመናገር ደርሰዋል። አሁንም “ተአምረኛ አጥማቂዎች”፣ “ፈዋሽ” እና “ነብይ” ነኝ የሚሉት ሰዎች በንፁኃኖች ላይ የሚያደርሱትን ማሰቃየት እንዲያቆሙ አንድ ነገር መደረግ አለበት።
Filed in: Amharic