>

ሌሎቹ አንዳርጋቸው ፅጌዎችም ይፈቱ! (ጌታቸው ሽፈራው)

አንዳርጋቸውን “እንኳን ተፈታህ” አልለውም። አንዳርጋቸውን ሳይሆን ራሳቸውን አስረው ነው የከረሙት፣ አንዳርጋቸውም የከረመው ትግል ላይ ነው። ኤርትራ በርሃ ሌጦ ላይ ሲተኛ የኖረ ሰው እስር ምኑ ነው?  አንዳርጋቸው ከታሰረ በኋላ ብዙ ተጩኋል፣ ብዙ! ይህ ጩኸት ትግሉን ምን ያህል እንዳሞቀው ለማወቅ የግድ ከታሰረበት ጊዜ ጀምሮ የጩኸቱን ውጤት መደመር አለብን።  እንጅማ አንዳርጋቸው ለትግሉ ነዳጅ ከሆኑት መካከል አንዱ ነው።  የታጋይ ሚና ተሰቃይቶም ቢሆን ለትግሉ ጠብ ማድረግ ነው። አንዳርጋቸውን ይህን ሚናውን  ከሚገባው በላይ ተወጥቷል።
አንዳርጋቸው በአርበኞች ግንቦት 7 ከታሰሩት መካከል ቁንጮው ነው። በፖለቲካ እስር ከታሰሩት መካከል ቁንጮው ነው። አንዳርጋቸው ፅጌ ታዋቂ ነው። ታዋቂ በመሆኑ ብዙ ተጩሆለታል። ይህ ጩኸትም አሳሪዎችን አክስሯቸዋል።
በአርበኞች ግንቦት 7 የታሰረው ዋነኛው ሰው ሰፈታ፣ በፖለቲካ እስር ቁንጮው አንዳርጋቸው ፅጌ ሲፈታ ግን ሕዝብ በስም ስላላላወቃቸው ብቻ፣ ስላልጮኸላቸው ብቻ ብዙ አንዳርጋቸው ፅጌዎች በእስር ላይ ናቸው።
ለምሳሌ!
በፎቶው ላይ ከአንዳርጋቸው ጎን ሆኖ፣ አንገቱም ወጣ አድርጎ በትኩረት እያየ የሚገኘው አወቀ መኮንን  ይባላል። እነ አንዳርጋቸው “በቃ” የሚል ልብስ ለብሰው ሲሰለጥኑት ከተነሱት ፎቶ ላይም ከአንዳርጋቸው ቀጥሎ ይታያል።
እስር ቤት ካገኘኋቸው ታጋዮች መካከል እንደ አወቀ አንዳርጋቸውን የሚያውቀው የለም። ውሏቸው አንድ ላይ ነበር። አሁን አወቀ በእስር ላይ ነው። በርካታ የአወቀ ጓደኞች፣ ኤርትራ ውስጥ ከአንዳርጋቸው ጋር አብረው ይውሉ ያድሩ የነበሩ ወጣቶች  በእስር ላይ ናቸው።
አንዳርጋቸው አሸንፎ ተፈትቷል። ሲከስሩ ለቀውታል። ያልተጮኸላቸው ግን አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ። በአርበኞች ግንቦት 7፣ በፖለቲካ ክስ ቁንጮው፣ ማንም እንዳያየው ተፈርቶ ታስሮ የቆየው አንዳርጋቸው ሲፈታ፣ ስማቸው የማይጠቀሰው፣ የማይጮህላቸው አንዳርጋቸው ፅጌዎች ሁሉ በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል! እነ አወቀ መኮንን!
Filed in: Amharic