>

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች "በልዩ ሁኔታ" በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ ተወሰነ

ፋና ብሮድ ካስቲንግ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 18 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በልዩ ሁኔታ በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ መወሰኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው የነበሩ 576 ግለሰቦች በልዩ ሁኔታ ይቅርታ ተደርጎላቸው እንዲፈቱ መወሰኑን አስታውቋል።
በልዩ ሁኔታ በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው መካከል 18ቱ ሴቶች መሆናቸውም ተገልጿል።
እንዲፈቱ ከተወሰነላቸው መካከል ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኝና ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረገ፥ እንዲሁም ጉዳያቸው በይቅርታ ቦርድ ለኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ቀርቦ በልዩ ሁኔታ በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ናቸው።
ግለሰቦቹ ስነ ምግባራቸውና መፀፀታቸው ታይቶና ከእስር ቢፈቱ ለህብረተሰቡ ስጋት የማይሆኑና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በማሰብ መሆኑንም የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ገልጿል።
በአጠቃላይ ለ745 ታራሚዎች እና ተከሳሾች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑንም ነው ጠቅላይ አቃቢ ህግ ያስታወቀው።
ከእነዚህ ውስጥ 576ቱ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰውና ተፈርዶባቸው የነበሩና በልዩ ሁኔታ ይቅርታ የተደረገላቸው ናቸው።
137ቱ ደግሞ በሽብር ወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የበነበረና ክሳቸው የተቋረጠ ነው።
31 ግለሰቦችና ተቋማት ደግሞ በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩና ክሳቸው የተቋረጠላቸው ናቸው።
Filed in: Amharic