>

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አሁንስ  አበዙት¡¡¡ (ሸዋዬ ገላው)

 
ዶ/ር  አብይ የውስጥ ሽኩቻውን በድል ተወጠው ወደ ቤተ መንግስት እንዲገቡ ከሚፈልጉት አንዱ  ነበርሁ።ጠቅላይነቱንም ከተረከቡበት ቀን ጀምሮ እንቅስቃሴዎንም በትኩረት ተከታትያለሁ፡፡ ነገር ግን ከቀን ወደ ቀን በክቡርነታቸው መከፋቴ እየጨመረ ሄደ፡፡
ክቡርነትዎ!! ቅር መሰኘቴ ከበዓለ ሲመትዎ ቀን ይጀምራል፡፡ የተከበሩ ጠ/ሚ የበዓለ ሲመትዎ ቀን እኛን አይደለም “ተዎካዮቻችችንም” በእንባ “ ባልተለመደ ሁኔታ” ሲያራጩ ግዴለም በመጀመሪያዎ የስልጣን ቀንዎ ነው ብየ ችየ አልፍሁዎት::  በመጀመሪያ ንግግርዎ በመዝለፍ እና በማሸማቀቅ ፋንታ እንዴት የደስታ እንባ ያስለቅሱናል። ስለ ዕውነት ቅር ተሰኝቸብዎታለሁ፡፡ ጠ/ሚ  እኛ እኮ የሰቆቃ እንባ  ማለቅስ የለመድን ህዝብ  ነን፡፡ እንዴት   ያልመድነውን የደስታ እንባ  ያስለቅሱናል ? ብየ  በመጠኑ ቅር ብሎኛል፡፡ ደግሞ ደግሞ ንግግርዎ ውስጥ “ ኪራይ ሰብሳቢ፣ ወዮልሽ፣ ልክ እናስገባቸዋለን” ወዘተ ማለቱን  ቢተውት እንዴት “ፀረ ሰላም ሃይሎች፣ የጥበት እና የትምክህት ሃይሎች ሳይሉ ንግግርዎን ይቋጫሉ።አዝኘበዎታለሁ፡፡
ክቡርነታዎ እሺ ለእኛ ባያዝኑ ፊት ለፊትዎ ለቆመው ካሜራ አያዝኑም። የ40 ቀን ዕድሉ ኢ/ያ ያመጣው ይህ ካሜራ ለ20 ምናምን ዓመታት እኮ  ሲጋት የኖረው እነዚህን ቃላት ነው። የቀረው ቢቀር ያለፈውን ስርዓት እንዴት ወረፍ አድርገውት አያልፋም። ያሳዝናል፡፡
እኛን  ሰፊ ህዝብ ስለሆንን “ሰፊው ህዝብ  ሆደ ሰፊ ነው”  ብለው አስበው ይሆናል:: እንዴት  ለጋዜጠኞች ትንሽ አያዝኑም ሌላው ቢቀር እንዴት “ያለበት ሁኔታ ያለው” የሚለውን ቃል ከመዝገብ ይፍቁባቸዋል።
ሌላው የገረመኝ ነገር እንዴት ህዝብ እየዞሩ ያወያያሉ። ህዝብ ጋር ውይይት ማድረግ ከነበረበትዎም የምርጫ ወቅት ሲደርስ ጠብቀው ነበር። እየሄዱ ሲያወያዩም በኮንደሚኒየም ቤት ለመደለል አለመሞከርዎ ሌላው ጥፋትዎ ነው፡፡ “ህዝብ ምን ይለኛል?” ይባላል እኮ ጠ/ሚ  !! እንደ ጠ/ሚነትዎ ርሰዎ ፅቤት ቅሬታ ይዘው ከየክልሉ የሚመጡ ህዝቦችን አፍኖ እንደማሳሰር ርስዎ ጭራሽ በየክልሉ እየሄዱ “ቅር  ያላችሁ ምንድነው እያሉ?” ማወያየትዎ ቅር አሰኝቶኛል።
ሌላው ደግሞ ከትንሹ ከትልቁ ጋር  በሆነው አልሆነው እንደመጣላት እንዴት ጠላት አልባ ይሆናሉ ?።  ከውስጥ ካሉ” ፀረ ሰላም ሃይሎች “ ጋ እሺ ይታረቁ እንዴት ከውጭ “ ፀረ -ሰላም ሃይሎች”  ጋ እንዴት ይታረቃሉ ? እንዴ?”!!! መንበርዎ ትንሽ  አያሳስበዎም።በስደት ላይ ያሉትን እኮ  ሀገር አለኝ ብለው እንዳያስቡ መሰለኝ የዘር ማንዘሮቻቸውን ሀብት የተወረሰው። ርስዎ እኮ ተዓምረኛ ሰው ነዎት እስክንድር ነጋ ከቤተሰቦቹ በውርስ ያገኘውን መኖሪያ ቤት ውርሱ ለእኔ ይገባኛል ካለው አካል ነጥቀው እንዳይመልሱለትና እንዳያስገርሙኝ።
ሌላው የተከፋሁብዎ ነገር እና ግራ የገባኝ “እንዴት ከሚያስተዳድሩት  ህዝብ ጋር  ሆድና ጀርባ መሆን ሲገባዎ እንዴት ከህዝብዎ ጋር ለመስማማት ደፋ ቀና ይላሉ ?”፡፡ ኧረ አይደረግም፡፡ከሀገርም ሆነ ከውጭ ከራስዎ  ህዝብ ጋር በጠላትነት ካልተያዩ ምን ሊሰሩ ነው ?”። አስከፍተውኛል፡፡
 ተጨማሪ አስረኞችና ተጨማሪ ስደተኞችን እንደማፍራት ርስዎ ግን ጭራሽ የታሰረውን ይፈታሉ፣ ርቀው ተሰደዱትንም “ ተመለሱ “ይላሉ።ጠ/ሚ እኛ የለመድነው እኮ ወደ ውጭ ሀገር ሲሄዱ በኢንቨስትመንት ስም  ለሀብታሞቻቸው…ከሰፋፊ ርሻዎቻችን የእጅ መንሻ …..ይዘው ሄደው …እዚህ ያሉ ዜጎቼ..” በሬዲዮ እንዳይናገሩ፣ በመንግስቴ ላይ እንዳያሴሩ፣ “ እኔን ሆነው ይስሩ  ብለው ስውር ስምምነት እንደመፈጸም  እንዴት… …በእስረኛ ታጅበው ወደ ሀገርዎ ይመለሳሉ፡፡ ጠ/ሚ እኛ እኮ እዚያም እዚህም ስንታሰር የኖርን የተናቅን ህዝቦች ነን እንዴት  “ያስታውሱናል”፣ እንዴት “ያከብሩናል “ ፡፡ አዝኘብዎታለሁ፡፡
ክቡርነትዎ !! ዝምብዬ ሳስበዎ  ሙሉ ጊዜዎን “የህዝቦች እኩል በጠቃሚነት የተረጋገጠባት ኢኮኖሚያዋ የዳበረች ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር ለመፍጠር ሊሰሩ ያሰቡ ይመስለኛል። በጣም አበዙት፡፡ ደግሞ ንግግርዎን ሲቋጩ  “ኢትዮጵያ በልጆቿ  ጥረት ታፍርና ተከብራ ለዘላለም ትኑር፡፡” ማለቱ አልበቃዎ ብሎ “ ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ልጆቿን ይባርክ “ የሚሉት ነገር አስከፍቶኛል፡፡ ክቡርነትዎ እኛ እኮ..በመሪዎች “የሚጸለይብን” እንጂ “የሚጸለይልን”ህዝብ አልነበርንም እንዴት ይሄን ያደርጋሉ፡፡ ከፍቶኛል፡፡
ሌላው የከነከነኝ  ነገር ጋዜጠኛን በአደባባይ “ ከውጭ ሀይሎች ጋር ግንነኙት  ያላቸው አሸባሪዎች”  እንደማለት፣ “የድሮው ስርዓት ሞግዚት” እንደ ማለት ማዕዛ ብሩን እንዴት “የሀገር ጀግና” ብለው በአደባባይ ያሞግሳሉ። እሺ ይሄም ይሁን እንዴት  ሚንስትሮችዎ ጋዜጠኛ እንዲያስሩ  እንጂ እንዴት  ከ ጋዜጠኛ  እንዲማሩ ያሳስቧቸዋል፡፡  አሳዛኝ ነገር ነው።
ደግሞስ ከሳውዲ እንደተመለሱ ቤተመንግስትዎ በደህና ማደሩን ሳያረጋግጡ “እንዴት ህዝቤ ይበልጥብኛል “  ብለው በቀጥታ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ ይመጣሉ። መምጣቱ ይምጡ ግዴለም ርስዎ ከመግባትዎ ፊት ጋርዶችዎ ቀድመው ገብተው እንዴት መድረኩን ከበው ህዝቡን በጥቁር መነፅር ቁልቁል አያይቱም ነበር። ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡
 እኛ አይደለም ጠ/ሚ የቀበሌ አስተዳዳሪ እንኳ በሙሉ አይኑ  የማያየን፣ ደንብ አስከባሪዎች የሚገርፉን ህዝቦችን ነን፡፡ እንዴት የለምድነውን ሁሉ በአንዴ ያስቀረቡናል፡፡ የምር ከፍቶኛል፡፡
ይሄም ይሁን እሺ እንዴት መድረኩ ጋር መጥተው መድረክ መሪው ካወራበት ቦታ ላይ  እንዴት ይቆማሉ። ከርስዎ ፊት ያሉ መሪዎች ያሰሩት ፎቁ ላይ ጥይት ማይበሳው በመስታውት የተሰራ ሳጥን ውስጥ ንግግር ማድረግ ነበረብዎት። ጠ/ሚ እኛ እኮ ህዝብ ነን እንዴት ይቀርቡናል። የዕውነት ተበሳጭብዎታለሁ።
“ያምራል ሀገሬን” ሲዘፈን  ያጨበቡትን “መራርጣችሁ እሰሯቸው” ብለው ቀጭን ትዕዛዝ እንደመስጠት  እንዴት ቆመው ከህዝብ ጋር በ”ያምራል ሀገሬ”  ያጨበጫባሉ።
ሲሄዱ ሲመጡማ መንገድ ማዘጋቱን ረስተውታል። እሺ መንገድ ማዘጋቱ ይቅር እንዴት ርስዎ እስኪያልፋ ድረስ እንዴት እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ፌደራል ፖሊስ  አፍንጫችንን እያሉ  ጀርባችንን ሰጥተን እንድንቆም ማድረጋቸውን  ስለምን  ተውብን፡፡ ‘’ጠ/ሚ ስለምን ይወድኑናል….?’ ስለምን አክብረዎ
 ያስከብሩናል….…?’ እኛ እኮ ህዝብ ነን…
Filed in: Amharic