>
5:13 pm - Friday April 19, 6447

ምንም ኬላ ባይሰብሩ፣ ወንዝ ባይሻገሩ ለታጋዩ ፕሮፌሰር  አድናቆቴና አክብሮቴ አይቀንስም!!! (በፍቃዱ ሞረዳ)

ከዕለታት በአንዱ ቀን (ያኔ) ከዚህ ሰዉ ጋር ከበቂ በላይ በሆነ ምክንያት ተደባብረን ነበር፡፡ ከምርጫ 97 በፊት፡፡
ከምርጫዉ በኋላ ፖርላማ ባለመግባት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ባለመረከብ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከሰጠዉ ምክንያት ጋርም ከማይስማሙት ሰዎች  አንዱ ነኝ፡፡ነበርኩ፡፡ እንደዜጋ፡፡
       በምርጫ ዘመቻ ወቅት የእርሱን፣ የልደቱንና የመረራን ንግግር የመስማትን ያህል እንደእህል እንደ ዉኃ የሚያስደስተኝ ነገር አልነበረም፡፡
   በፖሊስ መያዙን ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረኝ ዶ/ር መረራ ነዉ፡፡ ከዚያ ጀምሮ እንደማናቸዉም የዚያ ዘመን እስረኞች ልቤ ያዝንለት ነበር፡፡ ከእስር ተፈቶ፣ ፈረንጅ ሀገር መጥቶ ድርጅት ሲመሰርት እንደገና ብሽቀት ያዘኝ፡፡ ድርጅት በመፍጠራቸዉ አይደለም ብሽቀቴ፡፡ ስሙ ደበረኝ፡፡ሥላሴዎች አይቀየሙኝና ግንቦት ሰባትን አልቀደዉም፡፡ ቀኑን፡፡ አንደኛ፣ ያስከተለዉ ጦስ ደባሪ ነዉ፡፡ ሁለተኛ፣ ለእኔ ቀኑ የድል ቀን ሳይሆን ወርቃማ ዕድል ያመለጠበት ቀን ነዉ፡፡ ከዚያ በኋላ ለተከፈለ መራራ መስዋዕትነት በር የተከፈተበት ቀን ነዉ፡፡
    ይኼ ያለፈና እምብዛም የማይጠቅመን ነገር ነዉና ልከኛዉን መግላልት ከድነንበት እንለፍ፡፡ በዛሬዉ እዉነት ላይ እንሹር፤ ስለነገ እንኑር፡፡
ለማዉራት እምቃጣዉ ስለዶክተር ብርሃኑ ነጋ ነዉ፡፡ ድርጅት መስርቶ፣ዓላማ ሰርቶ፣ መንገድ አሰናድቶ ትግል ጀመረ፡፡ አሥመራም ገባ፡፡ አሥመራ በመግባቱ ያልተደሰቱ፣ ዛሬም የሚያጉተመትሙ በሽበሽ ናቸዉ፡፡አቃቂረኛ ታጋዮች፡፡ እኔ ከእነርሱ መሐል አይደለሁም፡፡ የትጥቅ ፍልሚያን ያካተተ ትግል ከተጀመረ ያለዉ ምርጫ ወደሀገር መሬት መቅረብ ነዉ፡፡ በዚህ ሀቅ አምኖ ‹‹ ለምን ኤርትራ ;›› የሚል ካለ ደግሞ፣ እርሱ/እርሷ ለሀገራችን አካባቢ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታ መሀይም መሆን አለበት፡፡ እናም ‹‹ እሰየዉ!›› አልኩ፡፡ ቢያዋጣም፣ ባያዋጣም፡፡
 ራሴንም ታዘብኩ፡፡ እንደ ብርሃኑ ቤተሰቤን ጥዬ፣ ጮማ ኑሮና ደመወዜን ወዲያ ብዬ…መሄድ አልሆነልኝማ፡፡ ለመወሰን ደፋር መሆን አልቻልኩማ፡፡ ማድረግ የነበረብኝ ነገር እርሱንና  አብረዉት ወደትግል ያቀኑትን ማድነቅ ብቻ ነዉ፡፡
ምንም ኬላ ባይሰብሩ፣ ምንም ወንዝ ባይሻገሩ አድናቆቴና አክብሮቴ አይቀንስም፡፡ እኔ ማድረግ የማልችለዉን ማድረግ እዉቀትና ቁርጠኝነት ያለዉ ሰዉ ሁሉ ከእኔ ይበልጣል፡፡ የአክብሮቴም ሰበብ ይኼዉ ነዉ፡፡
   የወቅቱን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ አስመልክቶ ሰሞኑን ዶክተር የሰጠዉ አስተያየት እንደገና እንዳደንቀዉ፣ እንዳከብረዉ አድርጎኛል፡፡አስተያየቱ ከእነፎቶዉ ከዚህ ፅሑፍ ጋር የተለጠፈ ስለሆነ ልፅፈዉ አያሻኝም፡፡ ከጊዜዉም፣ ከአንድ አዋቂ ሰዉም የሚጠበቀዉ ይኼዉ ነዉ፡፡
‹‹ ሥር ነቀል…›› የሚለዉ ጉዳይ  ጣፋጭ ጭቅጭቅ ማስነሳቱን አልጠላዉም፡፡ ‹‹ ሥር መንቀል›› የሚባለዉ ነገር ‹‹ አፍርሶ መገንባት ›› ወደሚል አዙሪት የሚያስገባን መንገድ ከሆነ እኔና ነፍሴ የለንበትም፡፡ ‹‹ በቀልን እንግደል፣ቂምን እንስቀል›› የምንል ከሆነ ትንሽ ቢሆን በነበረዉ ላይ እየገነባን በሂደት ከምንፈልግበት ግብ እንድረስ ባይ ነኝ፡፡ ይህ መሆን የሚችለዉ ዛሬዎች ለራሳችን ሥልጣንና ምቾት ሳይሆን ለልጅ ልጆቻችን አዘጋጅተን ስለምናልፈዉ ሠላም፣ነፃነት፣ እኩልነት…የጋራ ሀገር የምናስብ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነዉ፡፡ እነ ‹‹ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ›› የእዉቀታቸዉን ያህል ብፎትቱም፡፡
 ዶክተሩ ሆይ፣ ከዚህ በላይ ስለአንተ ማለት ብሻም ፣እኔ ቀለብ እንደምሰፍርልህ የማያውቅ አንዳንድ ወፈፌዎች‹‹ ቀለብ ስለሚሰፍርልህ ነዉ ›› እንዳይሉኝ እዚሁ ልቁም፡፡
ያቺ ‹‹ እኔ ወደትግል የገባሁት ማንንም ነፃ ለማዉጣት ሳይሆን መጀመሪያ ራሴንና ቤተሰቤን ነፃ ለማዉጣት ነዉ›› ያልካት ነገር ምን ዓይነት ምትሃታዊ እዉነት እንዳላት አስበህ ታዉቃለህ ?
የሃሳብ ልዕልና በልጦ፣ ሁሉም ጠመንጃዉን አስቀምጦ…ለሰላማዊ ፉክክር በሕዝብ ዳኝነት ፊት መቆም እንችል ዘንድ አሉታ ኮንትኑዋ! እዚያዉ እንገናኝ እንደገና፡፡እስከዚያዉ ክብርና ምስጋና፡፡
Filed in: Amharic