>
5:13 pm - Friday April 18, 3930

የኦ.ዴ.ግ ተደራዳሪ ቡድን አዲስ አበባ ገባ!? (መለሰ በቃሉ)

የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባ ዱላ ገመዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
አምስት የተደራዳሪ ቡድኑን ልዑክ እየመሩ የመጡት የግንባሩ ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባደረጉት ንግግር፥ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወደ ሃገር ቤት እንዲመጡ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
አቶ ሌንጮ ግንባሩ ከስድስት አመት በፊት ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተሳትፎ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።
ከመንግስት ጋር የሚደረገው ድርድር እንደሚቀጥል የጠቀሱት አቶ ሌንጮ፥ ግንባሩ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ጋር በተለያየ ጊዜ የተሳካ ድርድር አድርጓል ብለዋል።
የትጥቅ ትግል ወደ ዴሞክራሲ አይመራም ያሉት ሊቀ መንበሩ፥ በውጭ ሀገር የትጥቅ ትግልን አማራጭ ያደረጉ ኃይሎች አሁን ላይ በሃገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ከግምት በማስገባት በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ወደፊትም ግንባሩ ራሱን በመቻል ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ በመሆን ወይም ከሌሎች ጋር በመጣመርና በመዋሃድ በሃገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ማሰቡንም ጠቁመዋል።
የግንባሩ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ዲማ ነግሮ በበኩላቸው፥ ኦዴግ ህጋዊ መንገድ ተከትሎ የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሚሆን አንስተዋል።
ግንባሩ በሃገር ውስጥ በሚካሄደው ፖለቲካዊ እንቅስቅሴ ሊኖረው በሚችለው ተሳትፎ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር ለመምከር መምጣቱንም አስረድተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት ጉዳዮች አማካሪ አቶ አባዱላ ገመዳ ደግሞ፥ በሃገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሰላማዊ መንገድ መታገል ይገባል ነው ያሉት።
መንግስትም ሃገር ገንቢና የተሻለ ሃሳብ ካለው አካል ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የኢፌዴሪ መንግስት በቅርቡ መቀመጫውን ከሃገር ውጭ ካደረገው የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) ጋር ድርድር እንደጀመረ መግለጹ ይታወሳል።
የግንባሩ ተደራዳሪ ቡድንም የተጀመረውን ድርድር ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ መጥቷል።
Filed in: Amharic