>

የርእሰ መጻሕፍቱን ኃይለ ቃል አላግባብ መጥቀስ (ከይኄይስ እውነቱ)

ሂስ/ገንቢ ትችተ/ነቀፋ ስህተትን ለማረም፣ ለማስተካከል፣ ለማረም፣ ለማነጽና ለማስተማር እስከሆነ ድረስ ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በዚህ ረገድ  እውቀትና ልምድን፣ ማስረጃንና በቂ መረጃን ይዘው በአመክንዮና ምክንያት ታግዘው ሂስ/ትችት የሚያቀርቡና ቀናውን መንገድ የሚያሳዩ በቂ ባለሙያዎች ያሉን አይመስለኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ለአፉ ልጓም ማበጀት ያቃተው ተሳዳቢ፣ ተራ ወሬና አሉባልታ ቃራሚ ኹሉ በዓለ ሂስ ሆኖ በተለይም በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛዎች እንዳሻው ሲንቧችበት ይስተዋላል፡፡

በየትኛውም የእውቀት፣ የጥበብና የካበተ ልምድ ደረጃ የሚገኝ ሰው ፍጹም አይደለምና (ሊሆንም አይችልም) ከጉድለቱ በመነጨ ስህተትን ሊሠራ፣ ጥፋትን ሊፈጽም ይችላል፡፡ ስህተቱም ሆነ ጥፋቱ በአሳብ፣ በንግግር፣ በጽሑፍ ወይም በድርጊት ሊገለጽ ይችላል፡፡ ስለሆነም መሳሳትም ሆነ ማጥፋት ሰዋዊ ነው፡፡ ስህተትን/ጥፋትን አለመቀበል፣ ከቅንነት በመነጨ የተሻለ እውቀትና የልምድ ተሞክሮ ባለቤቶች ከሆኑ ግለሰቦች በተለይም እንደ አገር አዕማድ ከምናያቸው ዋኖቻችን የተጣመመውን ለማቅናት፣ የጎደለውን ለመሙላት ሕፀፆቻችንን ሲነግሩን አለመቀበል ወይም አሳማኝ በሆነና ደርዝ ባለው የተገረዘ አስተሳሰብ ማስተባበል አለመቻል ግን የሕማም ምልክት ይመስለኛል፡፡ በአንፃሩም ሳያውቁ ሳይጠነቅቁ ለመተቸት መጋበዝም እንዲሁ የጤንነት ምልክት አይደለም፡፡ በተለይም ከእውቀትና ጥበብ መራቆቱ በተጨማሪ ገንቢ ትችት መሆኑ ቀርቶ ስድብና ዘለፋ ሲሆን ጉዳዩ የሕማም ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊነት መጓደልም ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን በተለያዩ የሕይወት ዘርፎች የምናውቃቸውም ሆነ የማናውቃቸው፤ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ ዋነኞች አሏት፡፡ እነዚህ ዋኖቻችን ሰዎች በመሆናቸው ይሳሳታሉ/ያጠፋሉ፡፡ በመሆኑም እነሱም የሂስ/የትችት ርዕሰ ጉዳይ ከመሆኑ ነፃ አይደሉም፡፡ በሌላ አነጋገር አይነኬዎች አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት ሳይዘነጋ፣ በጨውነት÷ በታረመና በለዘበ ቋንቋ አሳባቸውን መንቀፍ/ማሄስ ይቻላል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው በእልህና በስሜተኝነት እነሱን ለማዋረድ በማሰብ፣ ተሳድቦ ለሰዳቢ አሳልፎ ለመስጠት ሲባል በብዙ አንደምታ (በታሪክ፣ በምሥጢር፣ በሰምና ወርቅ) የሚፈታ/የሚተረጐመውን የርእሰ መጻሕፍት (ቅዱሳት መጻሕፍት) ኃይለ ቃል አለቦታው መሰንቀር አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ራስን ማስገመት ነው፡፡

አገራዊ ጉዳይ ያሳስበኛል ብሎ አሳቡን በጽሑፍ ለወገኖቹ ለማካፈል (እንዲነበብ) የሚፈልግ ሰው ራሱን በእንደዚህ ዓይነት ጸያፍ/ነውረኛ ድርጊት ውስጥ የሚያገኘው ከሆነ፣ በጽሑፉ የሚያስተላልፈው መልእክት ቁም ነገር ቢኖረው እንኳ ተነባቢነቱ ÷ ተአማኒነቱና ተጽእኖ ፈጣሪነቱ በእጅጉ እንደሚቀንስ ማሰብ ይገባል፡፡ ቅድሚያ ራሳችንን እንግዛ፤ ቅድሚያ እናስተውል፤ ቅድሚያ እንመርምር፤ ቅድሚያ እንከባበር፡፡ እንዲህ ስንሆን ለሌሎች አርዓያ መሆን እንችላለን፡፡ ጽሑፎቻችንም ሆኑ ሌሎች ሥራዎቻችን በቊዔት ይኖራቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከልሳነ ዳኅፅ ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን፡፡

ከፍ ብዬ የገለጽኹት ሠፋ ያለ የመንደርደሪያ አሳብ ብዙዎቻችንን የሚያስማማ ከሆነ፤ ሰሞኑን በአገራችን ተከሥቶ ያለ፣ ከወያኔ ትግሬና ግብረ አበሮቹ በስተቀር ኹላችንንም በእጅጉ ያስቆጣና አሁንም ሃይ ባይ ጠፍቶ ተጠናክሮ የቀጠለ እኩይ ድርጊት አለ፡፡ ይኸውም ማንነትን መሠረት አድርጎ (ወያኔ ለራሱ ዓላማ ‹የጎሣ› መለያ በለጠፈለት አንድ ማኅበረሰብ) በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የማፈናቀልና የእልቂት ዘመቻ በተለያዩ የአገራችን ግዛቶች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጊት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ድንገት የተፈጸመ ሳይሆን ላለፉት 27 የሰቈቃ ዓመታት ሆን ተብሎና በዕቅድ ሲከናወን መቆየቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውንና እየደረሰ ያለው ግፍ ያሳሰባቸው ወገኖች ጩኸታቸውን በጽሑፍም በተግባርም በሚገለጽ ድጋፍ እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ አስተያየት ሰጭዎች የወገኔ ጥቃት የኔም ነው በሚል በዜግነት ተቆርቋሪነት የሚገለጹት ባንድ ወገን፤ በሌላ ወገን ደግሞ ለጉዳዩ ‹ልዩ› ባለቤቶችን ነን በሚሉ ወገኖችም ይጻፋሉ፡፡ ለዛሬው አስተያየት ያነሳሳኝ ጽሑፍ ከኋለኞቹ ወገኖች የተጻፈ አንድ አስተያየት ጥቃት ስለደረሰበት የኅብረተሰባችን ክፍል ማንነት አስመልክቶ የማኅበረሰቡ መለያ ጠባያት ብለው የገለጹበት መንገድና የቋንቋ አጠቃቀማቸው ሌሎች የአገራችንን ማኅበረሰቦች ቅር የሚያሰኝ፣ ለአብሮነት የማይበጅና ለአሉታዊ የአፀፋ መልስ የሚጋብዝ ነው በማለት ጋሼ መሥፍን ወ/ማርያም አንድ አጠር ያለች አስተያየት ‹‹የአማራ ፋሺዝም›› በሚል አቅርበዋል፡፡ ጸሐፊው በበኩሉ የጋሼ መሥፍንን አስተያየት በመቃወም ያስተላለፈው መልእክት  ስድብ/ዘለፋ መሆኑን ታዝቤአለሁ፡፡ ለዘለፋውም በመዝሙረ ዳዊት ምዕ. 89÷ ቊ.10 የተመዘገበውን ቃለ እግዚአብሔር በድጋፍነት ጠቅሶ አንብበናል፡፡ ዝርዝር ውስጥ መዝለቅ ሳያስፈልግ የተጠቀሰው ቃለ እግዚአብሔር ዓላማ የአገር አድባራትን ለመዝለፍ አለመሆኑን በመግለጽ ብቻ አልፈዋለኹ፡፡

የዚህ አስተያየት አቅራቢ ይህንን ጽሑፍ ሲያዘጋጅ ለእኚህ ግዙፍ ኢትዮጵያዊ ጥብቅና የመቆም  ዓላማ ኖሮት አይደለም፡፡ ጋሼ መሥፍን እንኳን ለራሳቸው ለአገር ዋልታ የሆኑ የአደባባይ ምሁር ናቸውና፡፡ ዓላማዬ ዋኖቻችንን እናክብር!!!! ለማለት ብቻ ነው፡፡ ከዋኖቻችን አንዱና ግንባር ቀደሙ ደግሞ ጋሼ መሥፍን ናቸው፡፡ ስድብና ዘለፋው እንኳን ከዋኖቻችን ከእኩዮቻችንና ከበታቾቻችንም ጋር ተገቢ አይደለም፡፡

ከቅዱሳት መጻሕፍት ኃይለ ቃላትን ስንጠቀም አሳባችንን ከማጠናከር እና ለመልእክታችን ክብደት ከመስጠት በላቀ ሁኔታ ለበጎ መሆኑን ብናስብበት መልካም ይመስለኛል፡፡ ተመቸኝ ብሎ ቃለ እግዚአብሔርን እንደ አህያ ዦሮ መጎተት ተገቢ አይደለም፡፡ አለበለዚያ ሳናውቀው ከሐሰት አለቃ ዲያቢሎስ ጋር መመሳሰል ይሆንብናል፡፡ ሰይጣንም ለማሳት ሲል ከቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቅሳልና (ማቴ. 4÷5-7)፡፡

ለማጠቃለል አንድን ማኅበረሰብ በማንነቱ ምክንያት ማንኳሰስም ሆነ በመታበይ መንፈስ ሰማይ ላይ መስቀል ተቀባይነት የለውም፡፡ በአንፃሩም ማንነትን መሠረት አድርጎ ማኅበረሰቡ ከሌላው ተለይቶ በኹሉ ረገድ የላቅ ነው የሚለው የዘረኝነት አስተሳሰብ (በውስጡ ሌሎችን የማሳነስ/የመናቅ አንድምታ ስላለው) እንደ መለስ ‹‹ወርቅ ሕዝብ›› ፋሺስታዊ አመለካከት ነው፡፡ ከፋሺስታዊነት መገለጫዎች መካከል ጽንፈኛ ‹ብሔርተኝነት› እና በናዚ ጀርመን የታየው ሌላ ገጽታው ደግሞ ከኹሉም ዘር የላቅኹ እና ለመግዛት የተመረጥኹ ነኝ ብሎ ማሰብ ይገኙበታል፡፡  

በመጨረሻም አበክሬ መናገር የምፈልገው ኢትዮጵያዊ ወገናችን በማንነቱ ምክንያት ላለፉት 27 ዓመታትም ሆነ በቅርቡ በወያኔ ትግሬ ወንበዴዎች እየደረሰበት ያለው ግፍና በደል በእጅጉ ያመናል፡፡ ወያኔ ለይቶ ከአገር ከመንደሩ ከቀዬው የሚያፈናቅለው ወገናችን ጥቃት የኹላችን ኢትዮጵያውያን ጥቃት ነው፡፡ ወገናችንን ለማቋቋም፣ መብቱ ተከብሮ ወደተፈናቀለበት ቦታው ለመመለስ፣ ዳግም ጥቃት እንዳይፈጸምበት ለመከላከል በግልም ሆነ በቡድን በመርዳት ከምናደርገው ድጋፍና መለስተኛ መፍትሄ ጀምሮ በዘለቄታው በአገር ባለቤትነት (ዜግነት) ላይ የተመሠረተ መብትና ነፃነት እንዲከበር ትግላችንን ማጠናከር የኹላችን ኃላፊነትና ድርሻ ነው፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ የማስተዋል፣ የመደማመጥና የመከባበር፣ መንፈሱን ያድለን፡፡ ዋነኞቻችንን ዕድሜ ከጤንነት ጋር ይስጥልን፡፡

Filed in: Amharic