>

ውሻ የራሱን ጆሮ ቆርጠው ሲያበሉት ስጋ የሰጡት ይመስለዋል!" (ዶ/ር አብይን አትንኩብን ለምትሉ በሙሉ) [ወንድማገኝ ለማ]

ጉድ ነው መቼስ ዘንድሮ?! ለካ ጊዜ እንዲህ ያስተዛዝባል! ተቃዋሚው ሁሉ ሰርከስ ኢትዮጵያ ይሰራ ነበር እንዴ?…ምነው ታዲያ ሁሉም አክሮባት ሰሪ ሆነብን! ማንም ዶ/ር አብይን አይደለም መደገፍ ማምለክ ይችላል ፤ ነገር ግን እኔ ሰውየውን ወድጄዋለሁና አትናገሩብኝ…
“ያንቀጠቅጠኛል ብርቱ ዛር አለብኝ
ጠቅላይ ሚኒስቴሬን ሌላ ሲነካብኝ” ….ብሎ ድቤ መምታት ፣ መሰንቆ መገዝገዝ ግን አይነፌክስ ነው! አሁን አሁን ደግሞ እየታዘብን ያለነው “አብይን የነካ አይኑ ይጥፋ ነው!” የሚለው ሰው እየበዛ ነው። በርግጥ ሰውየው እንደፖለቲከኛ ጎበዝ ኦራተር ነው ፣ ህዝቡ ምን መስማት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል…ሌሎች ሌሎችም መልካም ነገሮችንም አድርጓል።
.
ነገር ግን አሁንም ያሸነፈው ኢህአዴግ ነው። ህውሓት ደግሞ የሚፈልገው አብይና ህውሓት አይዋደዱም እንደውም ጠላታማቾች ናቸው ብለን እንድናስብላት ነው ፣ ያው ግቧን መታለች ፣ አብዛኞቻችን አብይ ሌላ ህውሓት ሌላ ማለት ጀምረናል። በነገራችን ላይ 1 ኢትዮጵያዊ መሪ የኢትዮጵያን ስም ደጋግሞ ቢያነሳ ምንም አያስገርምም ነበር። አገዛዙ ግን ኢትዮጵያን ቀማንና አሁን መሪው በሙሉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲል ደነቀን! መታሰር የሌለባቸውን ሰዎች አሰሩና ልክ ሲፈቱልን ታሳሪዎቹ ካሳ ይገባቸዋል ብለን እንደመሞገት አሳሪውን ከልክ በላይ አወደስነው ፣ ራሳቸው የቋንቋ ፌደራሊዝም (አንዳንዶች የዝንጀሮ ፌደራሊዝም ይሉታል) ጭነውብን ርስበርስ አጋድለው ፣ ደም አቀባብተው ስልጣናቸውን ካራዘሙ በኋላ አሁን ደግሞ ተታረቁ ባዮቹም ራሳቸው ሲሆን እንዳጣሉን ረስተንላቸው ታረቁ ሲሉን ድቤ ደለቀን! ይሄንን ነው እንግዲህ ውሻ የራሱን ጆሮ ቆርጠው ሲያበሉት ስጋ የሰጡት ይመስለዋል የምላችሁ!
.
እኔ ጨለምተኛ አይደለሁም! ዶ/ር አብይ ተስፋ እንዳረግንበት የውስጥ አርበኛ ሆኖ የምንናፍቀው መሲህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን መጠርጠር ግድ ይለናል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ላይ የመጡ አምባገነን መሪዎች ስልጣናቸውን እስኪያደላድሉ 1 ሁለት አመት ድረስ “ህዝቡ ሲጠራቸው አቤት ሲልካቸው ወዴት?” የሚሉ መሪዎች ነበሩ ፤ ጥቂት ሲቆዩ ነው ለምድ የለበሱ ተኩላዎች የሆኑት! እንዳው እንደምናስባቸው ዓይነት ታላቅ መሪ ቢሆኑ እንኳን ብዙዎች ዋጋ የከፈሉላትን የምንናፍቃትን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለመመስረት ኮ ቁምስቅላቸውን የሚያሳዩዋቸው ተቃዋሚዎች ፣ የመንግስታቸውን ስህተት የሚያጎሉ ጋዜጠኛና አክቲቪስቶች ፣ ያስፈልጉናል ኮ! አንርሳ እርሳቸው ፓርላማ ውስጥ ፈጣሪ ህዝቦቿንና ኢትዮጵያን ይባርክ ሲሉ ያጨበጨቡ የፓርላማ ሰዎች በሙሉ ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት የተከበሩ ግርማ ሰይፉ “ፈጣሪ ህዝቦቿንና ኢትዮጵያን ይባርክ” ሲሉ ሙሉ አዳራሽ ነበር የተሳለቀበቀቸው! ኢህአዴግ ለስልጣኑ ማራዘሚያ እስከተመቸው ድረስ ምንም ከማድረግ ወደኋላ አይልም። እኛ ግን ሁሌም እንሸወዳለን ፣ ትንሽ ሲሰጡን የእንትናችን  ዋንጫ እስኪወልቅ ድረስ እናጨበጭባለን። በመጨረሻም እናንተ ዶ/ር አብይን እስከጥግ የመውደድ መብት እንዳላችሁ ሁሉ ፣ እኛም ነገረ ስራውን ሁሉ በጥርጣሬ የመመልከት መብት እንዳለን አትዘንጉ። የተሻለችዋ ኢትዮጵያ የምትገነባው እኔ ብቻ ልክ ነኝ በማለት ሳይሆን ፣ አንተም ኮ ልክ ነህ ግን በአሁን ሰዓት የሚያስፈልገን የተሻለው ልክ የትኛው ነው? ብለን ከጭፍን ጥላቻም ሆነ ፍቅር የፀዳ ውይይትና ክርክር ስናካሂድ ነው።
ኢትዮጵያ ትቅደም
Filed in: Amharic