>

የዶ/ር ዐቢይ ያልተሄደበት የእርቅ መንገድ!! (መረጃ ለትውልድ)

ኔልሰን ማንዴላን ታላቅ የሰላምና ዕርቅ ተምሳሌት የሚያደርጋቸው በአፓርታይዱ ዘመን ለጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ያደረጉት መራራ ትግልና የ27 ዓመታት እስራት ብቻ ሳይሆን፤ በገዛ መሬታቸው ጥቁሮች በነጭ ወታደሮች አንደ እንስሳ ተቆጥረው በውሾች እስከመበላት የደረሰ ሰቅጣጭ ውርደትና ግፍ ሲፈጸም እያዩ ኖረው በትረ ስልጣናቸውን በተረከቡ ጊዜ በነጮች ላይ የበቀል እርምጃ እንደመውሰድ ዕርቅና ሰላም አውርደው አብሮ የመኖርና ተባብሮ ሀገራቸውን የመገንባት መንገድ መከተላቸውና ፤ በቀል የተጠሙ ደመኛ ጥቁሮችን አሳምነው አደብ ማስያዛቸው ጭምር ነው፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት መንግስት የደርግ ፋሺሲዝምን እየሰበከ ህልውናውን በመቃብሩ ላይ ተክሎ ለማቆም ሲታትር ቆይቷል፡፡ ህያው ስርዓት የሞተን ስርዓት እያወገዘ ለመቆም ሲጥር፤ በደርግ ዘመን የነበሩ አያሌ የቡድኑ አባላት ስደት፣ እስራትና እንግልት ተቀብለዋል፡፡ (ደርግ ከጣሊያን የበለጠ የኢትዮጵያ ጠላት ተደርጎ የመሳሉና፤ ግንቦት 20 ከአድዋ በዓል የበለጠ ትኩረት የመሰጠቱ ሀቅ ታሪክ የሚዳኝበት ዕለት ሲመጣ የመበቃቀል ጥማታችን ልክ የቱን ያህል ዕውር እንዳደረገን ይገልጥልን ይሆናል፡፡)  ይህ የመንግስት ባህርይም ወደ ህዝቦች በተዋረድ ተንቆርቁሮ በቀልን አብዝተን በመጠማታችን ወደ ኋላ ሁለት ትውልዶችን ቆጥረን በመሄድ በሚኒልክና ቴዎድሮስ ድርጊቶች ተከፋፍለን እየተደናቆርን ጦርነት ቀረሽ ውዝግብ አድርገናል፡፡
መንግስት ከ97 ወዲህ ከሕዝብ ጋር ደም መቃባት ውስጥ ሲገባ፤ ሕዝብን ከታርክ ቁርሾ አፋቶ እያስታረቀ፣ ራሱ ስለበደሉ የእውነት ይቅርታ እየጠየቀ አዲስ የዕርቅና ሰላም አካሄድ ተከትሎ ሕዝቡን ገንዘቡ ከማድረግ ይልቅ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማወክና የሕዝብ ፍላጎት በኃይል የማፈን መንገድ ሲከተል ነበር፡፡ ዕርቅና ሰላምን የይስሙላ ሽፋን ሰጥቶ በሃይማኖት መሪዎችና በሀገር ሽማግሌዎች ጣፋጭ ምላስ የተቀባባ መግባባት በመፍጠር የይቅርታ ደብዳቤ እያስታቀፈ በመሸኘት ለማስተካከል የሄደበት መንገድም የበለጠ የፖለቲካ ኪሳራና የሕዝብ አመኔታ ንፍገት ከመስጠት ውጪ ሌላ ትርፍ አልነበረውም፡፡
ብሔራዊ መግባባት እውነተኛ ሀገራዊ ዕርቅ የሚፈጠረው የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሚመራ የይስሙላ ዲስኩር ሳይሆን (የእነርሱን ሚና ማቃለሌ አይደለም) ሀገሪቱን የሚመራ ኃይል ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም በመያዝ ከማስመሰልና ሽንገላ በተፋታ እውነተኛ ስሜት ለሕዝቦች አንድነትና ለሀገር ህሊውና መቀጠል ከልቡ ሲሰራ ነው፡፡
የጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ የዕርቅ መንገድ አስተማማኝነቱም እዚህ ጋር ነው፡፡  የፖለቲካው ዓለም ከመንፈሳዊው ዓለም የተዋሰው ‹‹ካሪዝማ›› የምትል ቃል አለች፡፡ ካሪዝማ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር የፀጋ ስጦታን  ለመግለጽ የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የተጠቀሙት ቃል ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ለኢትዮጵያ ካሪዝማ ሲሆኑ፣ ተግባራቸውም ካሪዝማቲክ ነው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ የቀድሞውን የመንግስት ባህርይ ወደ ጎን ትተው መንግስታቸውን አዲስ (መንፈሳዊ) ቅርጽ አስይዘውታል፡፡ የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞችን የይስሙላ ‹‹ይቅር ተብላችኋል›› ደብዳቤ አስታቅፈው ሳይሆን ‹‹ሲጀመርም መታሰር አልነበረባችሁም›› በሚል መልኩ በትዕዛዛቸው ክስ እያስቋረጡ እየለቀቁ ናቸው፡፡ በቁጥር አንድ ፋሽስት ነፍሰ ገዳይነት ተፈላጊ የሆኑ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ሀገር ቤት መግባት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‹‹ተቃዋሚዎች ሳይሆኑ ለሀገሪቱ አማራጭ ሀሳብ ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች›› ናቸው በማለት እንደ ጠላትና ባለንጣ ከመቆጠር እንደ ወዳጅና የሀገር ባለቤት ተደርገው እንዲቆጠሩ አድርገዋል፡፡ ውጪ የተሰደዱትም ወደ ሀገር ቤት ገብተው በነፃነት አቋማቸውን ማራመድ እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡
እሳቸው አፄ ምንሊክን፣ ቴዎድሮስን፣ ኃይለስላሴን … ለሀገር አንድነት ሲሉ፣ በኢትዮጵያ ፍቅር ተነድፈው በዱር፣ በድንበር፣ በጫካ፣ በሀሩር የተሰውና የወደቁ አርበኞችን እያወደሱ ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን አንድነታችንን በዚያ የታሪክ መሰረት ላይ ለመትከል ጀምረዋል፡፡
የህመማችን ጥልቀት ከቆዳችን ዘልቆ ወደ አጥንታችን የጠለቀ መሆኑን፤ የዘረኝነትና መከፋፈላችን ክፋት ከክልል ዐልፎ ጎጥ ድረስ በመውረድ ፀገራችንን የሰነጠቀ መሆኑን በሚገባ ተረድተው አዲስ የሰላም፣ የዕርቅና መግባባት መንገድ ጀምረዋል፡፡ የዶ/ር ዐቢይ አዲሱ የዕርቅ መንገድ ያልተለመደና ያልተሞከረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን በሰላም ጠብቆ፣ አዕምሮኣቸውና ሰውነታቸውን በጤንነት አቆይቶ ዕድሜ ከሰጣቸው፤ በነበረው አሮጌ መንገድ የመቀጠል ክፉ አባዜ የተጠናወተው ተንኮለኛ ተነስቶ ካልበጠበጣቸው በቀር ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ወደ እውነተኛ የሰላምና እርቅ፤ አንድነትና ብልጽግና የሚመራ አስተማማኝ መንገድ ነው!!
             ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
            ጠ/ሚ አብይ ጤና ና ዕድሜ ይስጥህ
Filed in: Amharic