>

ከመሳከር ስሜቱ ባሻገር በምድር ላይ የሚታየው ያገጠጠ ጽድቅ [ከይኄይስ እውነቱ]

ሰሞኑን በኢትዮጵያችን እየሆነ ያለውን ለሚታዘብ እውን መንግሥት አለ ወይ የሚያሰኝ ነው፡፡ ይህን ስናገር ባለፉት 27 የባርነት ዓመታት መንግሥት ነበር እያልኩ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሕዝብ መጠነኛ ተሰፋ እያደረገ ባለበት የጠ/ሚ ዓቢይ ‹አስተዳደር› የጠ/ሚሩ ንግግርና መሬት ላይ ያለው ጽድቅ አልተገናኝቶም ቢሆንብኝ ያነሳሁት የትዝብት ቃል ነው፡፡

ይህ አስተያየት አቅራቢ አዲሱ ጠ/ሚ ከተሰየመ ጀምሮ ዕድል ተሰጥቶት ቢታይ፤ ይህም ሲደረግ ሕዝባዊ ትግሉ የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠሉ ንግግሩ ባዶ ቃል ኪዳን ሆኖ እንዳይቀር ዋስትና ይሆነዋል፤ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ ጠ/ሚ ዓቢይ ጸያሔ ፍኖት (መንገድ ጠራጊ/አቅኚ) መሆን ይችላል፤ በዚህ ኹሉ ውስጥ ግን በወያኔ ትግሬ/ሕወሓት ላይ ያለን ጽኑዕ አቋም ተቀየረ ማለት አለመሆኑን ከዚህ ቀደም በጻፍኳቸው አስተያየቶች ለማቅረብ ሞክሬአለሁ፡፡ ይህንን አቋም ያንፀባረቅኩት የማከብራቸው አንጋፋ ምሁራን ስለደገፉት ወይም ጅምላው ሕዝብ በመሳከር ስሜት (infatuation) ስላጨበጨበ ወይም እልል ስላለ፣ የጠ/ሚሩን ፎቶግራፍ በየመኪናው ስለለጠፈ ወይም በየቦታው ስለሰቀለ አይደለም፡፡ በብዙ ታሪካዊ ክስተቶች እንደታዘብነው በመንጋ አስተሳሰብና ድርጊት የሚመራው የማኅበረሰባችን ክፍል ለማወደስም ሆነ በድንጋይ ለመውገር ፍጥነቱ ያው ነው፡፡ ባንድ በኩል በጅምላው ሕዝብ ጨርሶ መፍረድም ይከብዳል ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነትን በመንደርተኛ ዱርዬዎች ተቀምቶ ከእነሱው ጉያ አፈንግጦ በወጣ ወጣት ‹መሪ› የኢትዮጵያ አንድነት፣ ክብርና ልዕልና ሲነገር መስማት የፈውስ ያህል በእጅጉ የተጎዳ ስሜትን የማከም ኃይል ስላለው ነው፡፡ ‹ምሁር› ነኝ የሚለው፣ ፊደል ቆጠርኩ የሚለው እና ጅምላው ማኅበረሰብ በአመዛኙ ነገሮችን ከስሚ ስሚ ባለፈ ግራ ቀኝ በማየት በሰከነ ሁኔታ አመዛዝኖና ተንትኖ በጥናት በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ ባህላችንም አይመስልም፡፡ ሕዝቡን አቅጣጫ የሚያስይዝ መንገድ የሚመራ ጠፍቷል፡፡ ፊትን ዓይተው የማያዳሉ፣ የሚመክሩ፣ የሚወቅሱ፣ የሚገሥፁ ምሁራን እንደ ዋልያ ብርቅዬ ናቸው፡፡ በማኅበረሰባችን ትምህርትና በሱም የሚገኝ እውቀት ዓላማና ትርጕም ከመተዳደሪያነት (meal card) ያለፈ አይመስልም፡፡ አንዳንዱም ‹አቦ አቦ› እንዲባል ውዳሴ ከንቱ ማግኛና ለመኮፈስ፤ ገሚሱም (በሚጣልለት ፍርፋሪ ምክንያት) በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የፈረንጆች ተላላኪ ለመሆን፤ አንዳንዱም እንቅብ እንደተደፋበት ፋኖስ ወይም የጋን ውስጥ መብራት ከመሆን የዘለለ ሚና የሌለው ወዘተ ሆኖ ይታያል፡፡ የትምህርት ሥርዓታችንም (የዛሬው ለይቶለት ትውልድ ገዳይ ሆነ እንጂ) ቀድሞም ቢሆን ፈጣሪ፣ አሰላሳይ፣ ሞጋች፣ በምክንያታዊነትና አመክንዮ የሚያምን አእምሮ በመቅረፅ ማኅበረሰባዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ዓውድን በማስተሳሰር የሕብረተሰብን ኹለንተናዊ ችግር ለመፍታት የተዘጋጀ አይደለም፡፡ ከሠለጠነው ሕብረተሰብ ለኛ የሚበጀውን መርጦ ከመውሰድ ይልቅ የተጫነውን ግሳንግስ ኹሉ (ያለበትን ማኅበረሰብ ታሪክ፣ እምነት፣ ባህል፣ ትውፊት ወዘተ. ግምት ውስጥ ሳያስገባ) የሚዘረግፈው ‹ምሁር› ቊጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ለማለዘብ ብዬ እንጂ አብዛኛው በዚህ ጎራ ውስጥ የሚመደብ ይመስለኛል፡፡ በየእውቀት አድባራቱ (ከፍተኛ ት/ት ተቋማት) የሚገኙ መምህራን በጣት ከሚቈጠሩ በቀር ያገኙትን እውቀትና ልምድ በልግስና ያለ ስስት ለወገናቸው አያካፍሉም፡፡ አጠቃላይ ከባህል የመነጨ ችግር ይሁን ሌላ በውል ባይታወቅም (ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ይመስለኛል) ትንሹንም ትልቁንም ጉዳይ እንደ ምሥጢር ማየት፤ እንደ ባህል የሕክምና ‹ዐዋቂ› የያዘውን ‹እውቀት› እና ‹ልምድ› መቃብር ይዞ መውረድ፤ የአስተማሪና የተማሪ ግንኙነት የጌታና ሎሌ መሆኑ ያመዘነበት፤ በሌላ አነጋገር ሥር የሰደደ ምቀኝነት ያለ ይመስለኛል፡፡  የበጎ መምህር አንዱና ዋናው ፍሬ ቢቻል ከራሱ የላቀ ደቀመዝሙር ማፍራት ይመስለኛል፡፡ መልካም መምህር የሚያየው የሩቁን፣ የሚያስበው መጪውን ትውልድና ትልቁን አገራዊ ሥዕል ነውና፡፡

ከይቅርታ ጋር ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያዊነት ስም ከመነሻው በጠላትነት የፈረጀውን ማኅበረሰብ ላይ የማያቋርጥ ጥቃት ሲፈጽም ዝም ብሎ መመልከት ኢትዮጵያዊነት አይደለም፡፡ ወያኔ ትግሬ ጠ/ሚ ዓቢይ ከተሾመ ጀምሮ (በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅና በወታደራዊ ዕዝ ሽፋን) የሚፈጽማቸው አረመኔያዊ ድርጊቶች ገና ለገና እነ ዓቢይን ከሕዝብ ጋር ለማጣላት ነው ብለን በዝምታ የምናልፍ ከሆነ ተሳስተናል፡፡ ተሳስተናል ብቻ ሳይሆን የነውረኛ ድርጊቱም ተባባሪ መሆን ነው፡፡ ሕወሓት በተባለው የዱርዬዎች መንጋ እና እሱን አኽሎና መስሎ የቆሻሻ ተልእኮው ፈጻሚ በሆነው የድውያን ስብስብ ብአዴን ሆን ተብሎ ማንነትን መሠረት ያደረግ መፈናቀል፣ ጥቃት፣ በአእምሮም በቁስም የማደህየት ደባ ያለማቋረጥ ሲፈጸም እያየን ዝም ማለት ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እኩል የምትሆን ኢትዮጵያን የሚፈልግ ሕዝብ ትክክለኛ መንገድ አይደለም፡፡ ያለ ምእመን ቤ/ክርስቲያን እንደሌለች ኹሉ ያለ ሕዝብ አገር የለም፡፡ ያውም ራሱን የእገሌ ነኝ ሳይል በሆደ ሰፊነት ከጎሣ ከነገድ በላይ ለሆን ብሔራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት)፣ ለአገር ህልውናና ለአብሮነት ለዘመናት በደሙና በአጥንቱ ኢትዮጵያን ሲዋጅና ሲያስከብር የኖረ፣ ከቀደምት የአገር ቆርቋሪዎች አንዱና ዋናው ኢትዮጵያዊ ባለውለታነቱ ተረስቶ ሲገፋ ሲበደል በአገሩ ሀገር አልባ፣ ዜግነት የሌለው መጤ ተደርጎ ሲቆጠር በአራቱም ማዕዝናት የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ነግ በኔን በማሰብ እምቢኝ አይሆንም ማለት ይገባው ነበር፡፡ አሁንም ይጠበቅበታል፡፡ አብሮነትን የሚፈልግ ሕዝብ መገለጫ አንዱ የወገንን ጥቃት በራስ ላይ እንደተፈጸመ መቊጠር ነውና፡፡

ታዲያ የኢትዮጵያ አንድነት፣ ክብር፣ ልዕልና ሲነሳ የፈነጠዝነው በባዶ ነው እንዴ? ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ፈልገን ነው? ወያኔ ትግሬ ለርስ በርስ ግጭትና ለዝርፊያ ያሰመረልንን የአትድረሱብኝ የጎሣ አጥር የሚፈልግ ኹሉ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሊያነሳ አይገባውም፡፡ ወያኔ በሸነሸነው የጎሣ ክልል መሠረት አገሬ ‹ክልሌ› ብቻ ነው፤ በዚያም የሚገኘው የተፈጥሮ፣ ቁሳዊና መንፈሳዊ ሀብታት የኔ ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ወገን ካለ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማንሳት አይገባውም፡፡ ወያኔንና ማናቸውንም አገዛዝ አጥብቀን የምንታገለው ኢትዮጵያውያን ዜጎች በሙሉ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እኩል መብት እንዲኖራቸው ነው፡፡ በፈለጉበት አካባቢ ተንቀሳቅሰው (ከየት መጣህ ሳይባል፣ መታወቂያው ኢትዮጵያዊ ዜግነቱ ብቻ ሆኖ) በመረጡት ሥራ ተሰማርተው፣ ኑሮአቸውን መሥርተውና ሀብት አፍርተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ የተባለች ጥንታዊትና ታሪካዊት የጋራ ቤታችንን በነፃነት፣ በሰላም፣ በሕግ የበላይነት፣ በእኩልነት፣ በፍትሕና ርትዕ ጽኑዕ ዓለት ላይ ለማዋቀር ነው፡፡ ወያኔ ትግሬ በጠላትነት የፈረጀውንና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በሦስትዮሽ የተገመደውን ማኅበረሰብ ይቅርና፤ ማንኛውም ኢትዮጵያ ዜጋ ለየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍለ ግዛት መጤ አይደለም፡፡ እንዲህ ማሰብ በራሱ ነውር ነው፡፡ ሃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ የእምነት መሠረት ላለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በጭራሽ አይስማማም፡፡

አንዳንድ ወገኖች ወያኔ ትግሬ በመክሥተ ደደቢትም ሆነ በይስሙላ ‹ሕገ መንግሥቱ› የተከላቸው የጎሣ ሰንኮፎች/መርዞች (ማንነትን የማስከበር፣ ከአስተዳደር ግዛት ጋር ተያየዘው የሚነሱ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ወዘተ.) በሕግ የበላይነት እና እኩልነት ላይ የተመሠረተ መንግሥተ ሕዝብ ማቆም ሲቻል ሰንኮፎቹም ይነቀላሉ፤ መርዞቹም ይበርሳሉ ብለው ያስባሉ፡፡ ይህ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የተቀናጀ ሕዝባዊ ዓመፃ ተደርጎ ሥር ነቀል የሥርዓት ለውጥ እስኪመጣ አንድ ማኅበረሰብ ላይ ያነጣጠረውን መገፋት በፍጹም ልንታገሠው አይገባም፡፡ ዛሬ ይህንን በኅብረት መመከት ካልቻልን ነገ ከተነገ ወዲያ ወያኔ ትግሬ በሌሎችም የአገራችን ማኅበረሰቦች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት ሲፈጽም መልሳችን ዝምታ ሊሆን ነው? ከቤንሻንጉልም ሆነ ከተለያዩ ክፍላተ ሃገር ጥቃት የደረሰባቸው፣ የተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ለመደገፍ ባገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ርዳታ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም ዘላቂ መፍትሄው እነዚህ ወገኖቻችን የዜግነት መብታቸው ተከብሮ ከሕይወትና ንብረት ዋስትና ጋር ወደኖሩበት ቀያቸው መመለስ አለባቸው፡፡ የሰሞኑን ብቻ አይደለም፡፡ ለበርካታ ዓመታት የዚህ ዓይነቱ ድርጊት ሰለባ የሆኑት ወገኖቻችን በሙሉ ከበቂ ካሣና ዋስትና ጋር ደረጃ በደረጃ ቤት ንብረት አፍርተው ከቤተሰባቸው ጋር ሲኖሩ ወደነበሩበት ክፍለ ሃገር መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገውን ወጪ የፌዴራልና የሚመለከታቸው የየክፍለ ሃገራቱ ‹አስተዳደሮች› መሸፈን ይገባቸዋል፡፡ በዚህ የወንጀል ድርጊት ሲሳተፉ የነበሩ በፌዴራልም ሆነ በክፍለ ሃገር ደረጃ ያሉ ባለሥልጣናት በሙሉ ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ፍርድ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡

አሁን ባለው የጠ/ሚ ዓቢይ አስተዳደር ዘመን የተፈጸመው ጥቃትና መፈናቀል አዲስ ባይሆንም ቢያንስ ጥገናዊ ለውጦችን አደርጋለኹ ብሎ የተነሳው አስተዳደር ጥቃት የደረሰባቸውን ተፈናቃዮች በሚመለከት ምን አደረገ? መቼም ለዚህ አንገብጋቢ ብሔራዊ ጉዳይ ጊዜ ይሰጠው ብለን እንደማናፌዝ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡

አንድ የአገር መሪ እንዳሁኑ ዓይነት አሳዛኝና አስደንጋጭ ብሔራዊ ክስተት ሲፈጠር የእገሌ ጉዳይ ነው ብሎ የሚገፋው ተራ አጀንዳ አይደለም፡፡ በቅድሚያ የተፈናቀሉት ዜጎቹ ጋር ሄዶ ማጽናናት፤ በጊዜያዊ መፍትሄነት አስቸኳይ ርዳት እንዲደረግላቸው ግብረ ኃይል አቋቁሞ መከታተል፤ ሕገ ወጥ በሆነው ድርጊት የተሳተፉት በሙሉ ሕግ ፊት ቀርበው ፍርድ እንደሚያገኙ ቃል መግባትና መከታተል፤ የተፈናቀሉትን ባስቸኳይ ወደ ቀድሞ ይዞታቸው መልሶ ማቋቋም ይጠበቃል፡፡ ሕግ ባለበትና በሚሠራበት አገር ደግሞ ጥቃቱ እንዲፈጸም ያደረገውና ያፈናቀለው የክፍለ ሃገር ‹አስተዳደር› ባለሥልጣን ኅሊና ካለው ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ በገዛ ፈቃዱ፣ ካልሆነም ሕጋዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ከሥልጣኑ እንዲነሳ ይደረጋል፡፡ (ዛሬ ወያኔ ‹ክልል› ብሎ ባዋቀራቸው ግልጽ የሕዝብ ወህኒ ቤቶች የተሰየሙ የወያኔ ትግሬ ሎሌዎች መካከል እጃቸው በደምና በዝርፊያ ያልተጨማለቀ ማግኘት እንደ ተአምር የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡)

እውን ቤንሻንጉል ያለና ወያኔ ትግሬ በአሻንጉሊትነት ያስቀመጠው ‹ባለሥልጣን› አቅም ኖሮትና በራሱ ፍላጎት ተነሳስቶ ነው ወገኖቻችን ላይ ጥቃት እንዲሰነዘርና እንዲፈናቀሉ ያደረገው? ለመሆኑ ጎጃም መተከል ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች አንዱ ሌላውን አልፈልግህም ውጣልኝ በሚል የተፈጸመ ጥቃትና መፈናቀል ከወያኔ አገዛዝ በፊት ነበር? ወያኔ ትግሬ በመክሥተ ደደቢት በጠላትነት ፈርጆ የመንግሥትን ሙሉ መዋቅርና የአገርን ሀብት ተጠቅሞ በልዩ ልዩ ስልት ከምድረገጽ ለማጥፋት የሚታገለው ማኅበረሰብ የቱ እንደሆነ፣ አይደለም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተለው የውጭው ዓለም ያውቀዋል፡፡ አንዳንዶቹም በታሪካዊ ጠላትነት ተሰልፈው ወያኔን በቅጥረኝነት ያሰለፉና የሚደግፉ መሆናቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡

ጠ/ሚ ዓቢይ ወገኖቻችን ማንነታቸውን መሠረት አድርጎ ስለደረሰባቸው ጥቃትና መፈናቀል ምን አድርጓል? ካላደረገ ለምን? እንደሚወራው ወያኔ ትግሬ አላላውስ ብሎት ከሆነ ይህንኑ በይፋ ለአገሩ ባለቤት ለሕዝቡ ማሳወቅና ከሕዝብ ጋር በጋራ ሆኖ መፍትሄ መፈለግ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች የሚያምኑት ጠ/ሚ ዓቢይ የሕዝብ እምቢተኝነት ውጤትና በአስተሳሰቡም ከወያኔ ትግሬዎች የተለየ መሆኑን ነውና፡፡ አሁንም በድጋሚ እናገራለኹ አንድ የአገር መሪ ነኝ የሚል ግለሰብም ሆነ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል ከሕዝብ/ዜጎች ደኅንነት በፊት የሚያስቀድመው ምንም ዓይነት ብሔራዊ አጀንዳ አይኖርም፡፡

በመጨረሻም ለሁሉም ጊዜ አለውና ኢትዮጵያና ሕዝቧን ላለፉት 27 ዓመታት ያዋረዱትና ከትግራይ ምድር የፈለቁት አውሬዎች (በሕይወት ያሉትም ሆነ ታሪካቸውን አጥቁረው ያለፉት ሰው መሳይ አውሬዎችን /ከሕወሓት ጋር ባንድነት ያሉትንም ሆነ በሥልጣን ጉዳይና ለትግራይ ጎሣ የበለጠ ጠበቃ ነን በሚል የተለዩትንና በልዩ ልዩ ድርጅት ስም ተወሽቀው የሚገኙትን እነ አረጋዊና ስዬ የመሳሰሉትን ጨምሮ/ በሕዝብ አስተያየት ፍ/ቤት ብቻ ሳይሆን በሕግ የበላይነት በሚቋቋም ፍርድ ቤት ተዳኝተው ተገቢውን ፍርድ እንደሚያገኙ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡

 

አምላከ ኢትዮጵያ ለተገፉት ወገኖቻችን እውነተኛ ፍርዱን ይስጥልን፡፡

Filed in: Amharic