>

የሱዳኑ ደርቡሽ  ለገደላቸው  በመተማ ሐውልት  ከመቆሙ  በፊት...(አቻምየለህ ታምሩ)

የሱዳኑ ደርቡሽ  ለገደላቸው  በመተማ ሐውልት  ከመቆሙ  በፊት «የትግሬው ደርቡሽ» ዐፄ  ዮሐንስ  ጎጃምን  ስላጠፉት ሐውልት ሊቆም ይገባል!

አቻምየለህ ታምሩ
ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ጎጃምን  ለማጥፋት ሁለት ጊዜ በዘመቱበት  ወቅት «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» ብለው አዋጅ በማስነገር ነበር።  ሰማኒያ ሺ የዐፄ ዮሐንስ  ሰራዊት  ጎጃም የተሰማራው ይህንን  ንጉሣዊ ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ነበር።  የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጸሐፊም  ይህን አልደበቁም። ዜና መዋዕል   ጸሐፊያቸው ሊቀ መርዓዊ የዐፄ ዮሐንስን የጎጃም  ዘመቻ  ሲገልጹ «ወሖረ ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ  ጎጃም» ሲሉ ነበር የጻፉት። ይህን  የዐፄ ዮሐንስ የዘር ማጥፋት ዘመቻና አላማው  ወደ አማርኛ ሲመለስ  «[ጃንሆይ] ወደ ሰው በላው [ቡዳው] አገር ወደ  ጎጃም ዘመተ» ማለት ነው።
ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን  ከዳር እስከ ዳር ቤተ ክርስቲያን ሳይቀር እያቃጠሉ፣ ታቦቱን እያወጡ እየጣሉ ካባይ እስከ አባይ ድረስ ያጠፉት በመጀመሪያ ሕዝቡን  «ቡዳ» በማለት  demonize አድርገው  ሰራዊታቸው ሰው ሳይሆን ቡዳ እየጨፈጨፈ እንደሆነ እንዲሰማው  በማድረግ  ነበር።  የሴቱን ጡት፣ የወንዱን ብልት ቁረጥ ተብሎ በጎጃም ላይ  የዘመተው የዐፄ ዮሐንስ ሰራዊት ጎጃምን ያን ያህል  ጥፋት ያደረሰውና  ካባይ እስከ አባይ የሬሳ ክምር ያደረገው «ወሖር  ሀገረ በላዕተ ሰብእ እምብሔረ  ጎጃም» ተብሎ ሰው ሳይሆን  ጎጃምን በሙሉ ቡዳ  ነውና  መደዳውን ጨፍጭፍ ተብሎ  በንጉሠ ነገሥታት ዮሐንስ ንጉሠ ፅዮን ዘ ኢትዮጵያ አዋጅ ስለተነገረው  ነበር። ይህ ተረት ተረት አይደለም፤ የተመዘገበ ታሪክ እንጂ።
ከታሪክ ማስረጃዎች በተጨማሪ በማሕበረሰቡ ዘንድም ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ያካሄዱት  ሁለት ዙር ጭፍጨፋ በስነ ቃል ሲወሳ ኖሯል። ጭፍጨፋውን በአይኑ ያየውና በተዓምር የተረፈው  ቦጋለ አይናበባ የሚባል የጎጃም አልቃሽ ያንን  የጎጃም የመከራ ዘምን  እንዲህ ሲል ገልጾት  ነበር፤
ዮሐንስ ነው ብለው ስንሰማ ባዋጅ፣
ዮሐንስ አይደለም ሳጥናኤል ነው እንጂ፤
ዮሐንስ አጠፋው አደረገው ዱር፣
ጎጃምን የሚያህል ያን ለምለም ምድር፤
በትግሬ ተዘርፈን እንጀራ ፍለጋ ወንዙን ሳንሻገር፣
ድሮ ባገራችን ቡቃያው በጓሮ በጎታ እህል ነበር፤ 
በላይኛው ጌታ በባልንጀራዎ፣
በቅዱስ ሚካኤል በጋሻ ጃግሬወ፣
በጽላተ-ሙሴ በነጭ አበዛወ፣
ጎጃምን ይማሩት ፈሪም አንልወ፤
ጎጃም ተቃጠለ ዐባይ እስከ ዐባይ፣
ትግሬ ቅጠል ይዞ ሊያጠፋው ነወይ፤
ከሀበሻ ወዲህ ከሀበሻ ወዲያ፣
ሰውን ገረመው እኔንም ገረመኝ፤
ዮሐንስ እግዜርን ገድሎታል መሰለኝ
በእኔ ዘመንም  ከዛሬ ሀያ ሶስት ዓመታት በፊት ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን በጨፈጨፉ ልክ በመቶ አመቱ የዐፄ ዮሐንስ የልጅ ልጆች ነን ያሉን  ፋሽስት ወያኔዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የተቋቋመን  የጎጃምን  የወባ ማጥፊያ  ድርጅት ነቅለው ወደ ትግራይ  ስለወሰዱት በመቶ ሺዎች እንደሚቆጠር የሚገመት  የጎጃም ሕዝብ እንዲያልቅ አድርገው ነበር። በወቅቱ  ከመቶ አመት በፊት ዐፄ ዮሐንስ በጎጃም ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ተመሳስሎ  ከመቶ አመት በኋላ የልጅ ልጆቻቸው ነን ባሉ ወያኔዎች ዘግናኙ ታሪክ  መልኩን ቀይሮ ራሱን በጎጃም ላይ ሲደግም፤
ጦማችን ባይሰምር ጸሎታችን ባይደርስ፣
በልጅ ልጅ መጡብ ዐፄ ዮሐንስ፤
ብሎ  ነበር ጎጃም።
ፋሽስት ወያኔ  ባለፉት ሀያ ሰባት አመታት የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክን ታሪክ ለማጥፋትና ኢትዮጵያውያንን ለማጋጨት ይጠቅመኛል ያለውን  ክፋት ሁሉ  አድርጓል፤ በየቦታው በፈጠራ ታሪክ  የተዋጁ የተቆረጠ እጅና ጡት ሐውልትን ጨምሮ እልቆ ቢስ ጸረ ምኒልክ  ሐውልቶችን አቁሟል።
ከሰሞኑ ደግሞ ወያኔዎች የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት መተማ ላይ ይቁምልን  እያሉ ነው። ወያኔዎች የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት  መተማ ላይ እንዲቆምላቸው  የሚጠይቁት ዐፄ ዮሐንስ የወደቁለትን አላማ ለማክበር ፈልገው አይደለም።  መተማ ላይ ዐፄ ዮሐንስ ሐውልት  እንዲቆምላቸው የሚጠይቁት  የወደቁለትን አላማ  በማክበር ቢሆን  ኖሮ  ዐፄ ዮሐንስ የሞቱለትን መሬት  እየቆረሱ ለሱዳን አይሰጡም ነበር። እነሱ በዋናነት ለዐፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ሐውልት እንዲቆምላቸው የሚፈልጉት  በጊዜ ብዛት የዐፄ ዮሐንስ ሐውልት የቆመበት ሁሉ የትግራይ  መሬት ነው ብለው መሬቱን ወደ ትግራይ ለማጠቅለል  እንዲያመቻቸው ነው።
አንድ ነገር ግን ማንሳት እፈልጋለሁ።   ዐፄ ዮሐንስ ራሳቸው በጎጃም ላይ «ደርቡሽን  እንደሆኑበት» ወይንም ደርቡ ኢትዮጵያን  ያጠፋውን ያህል እሳቸው  ጎጃም እንዳጠፉት ተናግረዋል። የነፍስ አባታቸው አቡነ ቴዎፍሎስ  ሳይቀር «በሕዝቤ ላይ ደርቡሽ ሆንህበት» ብለው አውግዘዋቸው ነበር። ይህ ማለት ዐፄ ዮሐንስ ጎጃምን ያጠፉት ደርቡሽ እኛን ያጠፋንን ያህል ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ የሱዳኑ ደርቡሽ  በመተማ ምድር ስላጠፋው ሐውልት ይቁም ከመባሉ በፊት የትግሬው ደርቡሽ ዐፄ  ዮሐንስ  ጎጃምን  ስላጠፉት  በቅድሚያ ጎጃም ላይ ሐውልት ሊቆም ይገባል።  የሱዳኑ ደርቡሽ መተማ ላይ ሐውልት ይቁም  እያሉ  ከመተማው ጥፋት በፊት የትግሬው ደርቡሽ ዐፄ  ዮሐንስ ጎጃም ስላጠፉት ሐውልት  እንዲቆም የማይጠይቅ ቢኖር  የሱዳኑ ደርቡሽ መተማ ላይ  ስላጠፋው ሐውልት ይቁም የሚለው በሰብአዊነት ስሜት  ሳይሆን  ለፖለቲካዊ ትርፍ ብቻ ነው። የሰብአዊ ፍጡር መስዕዋትነት ደግሞ ለፖለቲካ አላማ የሚውል ከሆኑ ሰማዕቱን ሁለት ጊዜ መግደል ነው።
ከዚህ በተጨማሪ  ወያኔ በየቦታው ያቆማቸው  ጸረ ምኒልክ ሐውልቶች አላማቸው በደልን ታሳቢ ያደረገ  ከሆነ  በፈጠራ ታሪክ ላይ ተመስርቶ  ያቆማቸውን በትግራይ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የተገነቡ የፈጠራ ሐውልቶች አፍርሶ  የዐፄ ዮሐንስ ዜና መዋዕል ጸሐፊ ሊቀ መርዓዊ ሳይቀር  ለጻፉትና  ዐፄ ዮሐንስ በሁለት ዙር  «ሴቱን ጡቱን ወንዱን ብልቱን አይተርፈኝም» እያሉ ዘምተው  የቆረጡት የሴት ጡትና የወንድ ብልት ባግባቡ ተጠንቶ  ዘመኑን የዋጀ መታሰቢያ ሊቆምና  የዐፄ ዮሐንስን  የጎጃም ጭፍጨፋ የሚያወግዝ ሐውልት ሊቆም ይገባል።
ዐፄ ዮሐንስ በአዋጅ የጨፈጨፏቸው፣ ምላሳቸውን የቆረጧቸው፣ አፍንጫቸውን የፎነኗቸው፣ ካገራቸው ያሰደዷቸው የወሎ እስላሞችም ሰማዕታቶቻችን  ናቸውና  ከመተማው ሐውልት በፊት ደሴ ላይ ሐውልት ሊቆምላቸው ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ  ከባህላችን  ባፈነገጠ መልኩ ከማረኳቸው  በኋላ  ከፍትሕ ነገስቱ በመውጣት ያለ ፍርድ አይናቸውን  በጋለ ብረት አፍርጠው፣ በዱልዱም በማረድ  በግፍ ለገደሏቸው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዐፄ  ተክለጊዮርጊስም ወርዒ ማዶ መታሰቢያ ሊቆምላቸው ይገባል!
Filed in: Amharic