>

የኢህአዴግ ግራ መጋባትና የሃገራዊ መግባባት አጀንዳ!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

(አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ እንደ ማሳያ)

ኢህአዴግ ለ17 ቀናት አደረኩት ባለው ድርጅታዊና ሃገራዊ ግምገማ መሰረት ከአራቱ የግንባሩ አባል ድርጅት መሪዎች የጋራ መግለጫ እንደተገነዘብነው “ኢትዮጵያ ሃገራችን አደጋ ላይ ናት በመሆኑም ሃገራችንን ለመታደግ ኢህአዴግ የማሻሻያ እርምጃዎችን ያደርጋል” የሚል ነው። ይህንንም ሃገራዊ አደጋ በአፅኖት ሲገልፁ “የማናችንም ስልጣንና ክብር ገደል ይግባ፤የግለሰብ ክብርና ስልጣን ከሃገር አይበልጥም” (የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር ልብ ይሉዋል) በማለት መናገራቸው አይዘነጋም።
 በተጨማሪም የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለሃገራዊ መግባባት ሲባል ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጦ የተፈረደባቸውም ሆነ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲ  አመራሮችና ሌሎች ግለሰቦች በምህረት ይለቀቃሉ ማለታቸውን ተከትሎ በአብዛኛው በውሸትና አልፎ አልፎም በእውነት በግንቦት ሰባት ተጠርጥረውና ተፈርዶባቸው የነበሩ ዜጎች ከእስር ተለቀዋል።
 ይህ ከሆነ እነዚህ የተፈቱ ግለሰቦችበኢህአዴግ እምነት ጥፋት ስላልፈፀሙ ሳይሆን ሃገር አደጋ ላይ በመሆኑና ለሃገራዊ መግባባት አስፈላጊ በመሆኑ መንግስት በሆደ ሰፊነት ለሃገር ሲባል ከእለት በእለት የህግ ማስከበር ባለፈ ነገሩን ከፍ ባለ ሁኔታ አይቶ ዜጎች ከእስር እንዲወጡ ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ መወሰኑን ነው። ግራ የሚያጋባው ነገር ግን ይህ ለብሔራዊ መግባባት ይጠቅማል የተባለው ውሳኔ የድርጅት መሪ የሆኑትንና ብዙ ኢትዮጵያዊ ወደ ትጥቅ ትግል መግባታቸውን የሃገራችን ፖለቲካ ጤና ማጣት ምክንያት አድርጎ በምልክትነት የሚያያቸውን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ይህ ተወሰነ የተባለው የፖለቲካ ውሳኔ አለማካተቱ የኢህአዲግን የሃገራዊ መግባባት አጀንዳ የምር የተያዘ ሳይሆን ከግራ መጋባት የመነጨ የፖለቲካ ንግድ አድርገን እንድንረዳው እንገደዳለን።
ከዚህም በተጨማሪ ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የነበሩ የኢህአዲግ  አመራሮች ብዙ ጊዜ በመመፃደቅ የሚጠቀሙበት አገላለፅ አለ። ይህውም “በመራራ መስዋዕትነት የገነባነው ስርዓት አደጋ ላይ እንዳይወድው”  የሚል ነው። ይህ የሚመፃደቁበት አባባል እውነት ቢሆን ኑሮና የጋራ ውሳኔን የሚያከብር ስርዓት ቢኖር ኑሮ ለብሄራዊ መግባባት ሲባል በ17ቱ ቀን ስብሰባቸው የወሰኑት የፖለቲካ ውሳኔ ለአቶ አንዳርጋቸውም እውን ይሆን ነበር ፤እኛም ዛሬ አቶ አንዳርጋቸው ይፈታ እያልን አንጮህም ነበር። ለዚህም ነው ብዙዎቻችን እንደ ግለሰብ መንፈሰ መራራና ቁጡ እስከምንባል ድረስ በኢትዮጵያ አገዛዝ እንጅ ህጋዊ ስርዓት የለም እያልን በተደጋጋሚ የምንጮኸው።
በመጨረሻም የሚሰማ ካለ አቶ አንዳርጋቸው በዚህ ወከባና ግርግር በሚበዛበት ዓለም በሃገሩ ጉዳይ ላይ አትኩሮ ብዙ ጊዜ ያሰበና ያሰላሰለ ሰው ስለሆነ አንዳርጋቸውን መፍታት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ፖለቲካም አንድ አካልና ጠቃሚ አድርጎ መውሰድና መወያየት ለሃገራችን ቅን አስበው ለሚወጡ ለሚወርዱ የፖለቲካ ሃይሎች ሁሉ ጠቃሚ እርምጃ ይመስለኛል።
በነገራችን ላይ ስለ አንዳርጋቸው መፈታትና በፖለቲካ ማሳተፍ አስፈላጊነትን ደጋግሜ ስናገር ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር ያሉኝ የፖለቲካ እምነትና ሃሳብ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ነው። ምናልባትም ከሃገራዊ መግባባት ቀዳሚ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ጤናማ በሆነ ሁኔታ የሃሳብ ልዩነትን አስፈላጊነት በማመን በጤናማ መንገድ የሚስተናገዱበትን ስርዓት  ማመቻቸት ይመስለኛል።አቶ አንዳርጋቸውን መፍታት ለቤተሰቡም ለሃገራዊ መግባባትም በጣም ወሳኝ እርምጃ ነውና “በመራራ መስዋዕትነት” የተገነባ ነው የምትሉት  ስርዓት ዋጋ እንዳያጣ አቶ አንዳርጋቸውን ፍቱት።
Filed in: Amharic