>

"ዋና ቢሯችሁን አ.አ አድርጉ" ሲባል መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ!??! (ኪታባ መገርሳ)

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የባለአደራ ቦርድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በውጭ አገር የሚገኙ የሚድያ ተቁዋማትን አስመልክተው ስለተናገሩት ንግግር የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዋሳ ከተማ ተገኝተው ባደረጉት ንግገር የሚከተለውን ተናግረዋል።
“ዴሞክራሲ ይስፋ ይስፋ ብላችኃል ብዙ ሰዎች። አሁን በናንተ ፊት ለማረጋግጥ የምፈልገው፣ በአሜሪካን አገር ሚዲያ ያላቸው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የሚናገሩ፣ የሚጮሁ፣ የሚቆጡ፣ የሚጨነቁ ሰዎች አሉ። በናንት ፊት ማረጋግጥ የምፈልገው የነዚህ ሰዎች ዋና ቢሮአቸው አዲስ አበባ እንዲሆን እንፈልጋለን።”
ይህ የሚያበረታታ ንግግር ነው። አደናጋሪ የሚሆነው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ባደረጉብት ዕለት መንግስታቸው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በሳተላይት የሚያስተላልፈውን ስርጭት በአራት ዓመት ውስጥ ለሃያ ሰባተኛ ጊዜ ከአየር ላይ እንዲታጎር አድርጎአል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአዋሳ ንግግር ከመንግስታቸው ተግባር ጋር ማስታረቅ ግን እጅግ አስቻጋሪ ነው ። ይሁን እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በተስፋ ለመጠበቅ እንፈልጋለን። በርሳቸው ንግግርና በመንግስታቸው ተግባር መካክል ያለዉን ልዩነት ለማስቀረት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ በሳተላይት የሚያደርገውን ስርጭት እንዲቀጥል በመፍቀድና ድህረገፁን በመክፈት እንደሚጀምሩ ጽኑ እምነት አለን።
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክና ሌሎች የሚዲያ ተቁዋማት ዋና መስሪያ ቤታቸውን በአዲስ አበባ ለማድረግ እንዲችሉ ግን ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል።
1ኛ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክና ዋና ስራ አስኪያጁ አቶ ጀዋር መሐመድ እአአ በ2009 በወጣዉ የፀረ ሽብር ሕግ ያላግባብ ተከስዋል። ይህ ክስ ባስቸኳይ መነሳት አለበት። የነፃ ሚድያ ተቁዋማት ወደፊት በዚህ ሕግ እንዳይጠላልፉም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጉን መሻር አለበት።
2ኛ፣ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የመናገር መብትና የሃሳብ በነፃ መንሸራሽር እንዲኖር የሚደግፍ ድርጅት ነው። አሁን በስራ ላይ ያለው የፕሬስ ሕግ እያለ ግን ስራዉን በነፃነት ማከናወን አይችልም። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ሕግ በተቻለ ፍጥነት መሻር አለበት።
3ኛ፣ አሁን በስራ ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ እስካልተነሳ ድረስ ነፃ ሚዲያ አገልግሎቱን መስጠት አይችልም። የግል ሚዲያ በነፃነት ለመስራት ይችል ዘንድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጉን መሻር አለበት።
እነዚህ እርምጃዎች ከተወሰዱ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግብዣ አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት እናያለን። ተስፋችንም ከፍ ይላል። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እስካሁን ድረስ ግን ባለው ቃሉን ያለመጠበቅ ታሪክ አንፃር ስናየው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአሜሪካን አገር ያሉ ሚዲያዎች” ወደ አገር እንዲገቡ ሲሉ ያቀረቡትን ጥሪ የተለመደው የመንግስት መሰሪ ሃሳብ አድርግን ነው የምንመለከተው። ይህ አስተሳሰባችን ትክክል እንዳልሆነ ለማሳየትና አዲስ የፖለቲካ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ለማረጋገጥ መንግስታቸው ከላይ የተዘረዘሩትን እንቅፋቶች ለማስወገድ እንደሚሰራ እምነታችን የፀና ነው።
ኪታባ መገርሳ 
የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የባለአደራ ቦርድ ፀሐፊ
Filed in: Amharic