>
5:13 pm - Wednesday April 19, 6367

''አፈ ባንዳ'' (ርእዮት)

አገራችን ኢትዮጵያ በ1928 ዓ/ም በአፄ ኃይለ ሥላሴ መሪነት ከጣልያን ጋር ባካሔደችው ጦርነት ከ40 ዓመታት በፊት በዘመነ ምኒልክ በአድዋ ያስመዘገበችውን ውጤት ማስጠበቅ ያልቻለችው በምን ምክንያት ነው? ማለት ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ሁለቱ ጦርነት (የ1888 እና 1928 ዓ/ም) ብዙ ነገሩ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሁለቱም ጦርነት የተካሄደው በጣልያን እና በኢትዮጵያ ነው ፤ የጦርነቱ ሜዳም ከ40 ዓመት በፊት የተጫወቱበት የኢትዮጵያ ምድር ነበር፡፡ ነገር ግን አገራችን በሁለተኛው ተጋድሎዋ የመጀመሪያ ድሏን አላስጠበቀችም፡፡ ለምን? ይህንን ጥያቄ በደንብ ለመረዳት እና ሚዛናዊ ብይን ለመስጠት የጦርነቱን ፍጻሜ (ማሸነፍና መሸነፍ) ሳይሆን የነበረውን አሰላልፍ እና በእያንዳንዱ የጦር ግንባር የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ በደንብ ማጤን የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በጦርነቱ ከኢትዮጵያውያን ጎን ተሰልፎ የተዋጋው ዩጎዝላቭያዊው አዶልፍ ፓርለሳክ የሐበሻ ጀብዱ በሚለው መጽሐፉ ጦርነቱን ከታሪክነት ከፍ አድርጎ ክውን ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ፓርለሳክ በእያንዳንዱ ቀን የጦር ውሎ አብረን በመጓዝ የድሉም ሆነ የውድቀቱ አካል እንድንሆን ያደርገናል፡፡ ጦርነቱን በዚህ መልኩ ማዬት የቻለ ሰው ለምን እንደተሸነፍን በትንሹም ቢሆን ፍንጭ ማግኘት ይችላል፡፡
ጣልያኖችን ያሸነፉን እንደ ውኃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ ሆነው አይደለም፡፡ አርባ ዓመታት ሙሉ እንቅልፍ አጥተው እኛን ለማሸነፍ የሚያግዙ ብዙ ስልቶችን ሲነድፉና ሲተገብሩ ኖረዋል፡፡ እኛ ግን ወደ ጦርነቱ የገባነው አንዳች ዝግጅት ሳናደርግ ሱሪአችንንም በውል ሳንታጠቅ ዝልኛችንን እያለን ነው፡፡ ጣልያን ባገኘችው አርባ የእፎይታ ዓመታት በጥልቀት አስባ ከሠራቻቸው ሴራዎች ባንዳነት ቀዳሚው ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንን ፊት ለፊት ተዋግቶ ማሸነፍ እንዳማይቻል የተረዳችው ጣልያን ከጦርነቱ የተማረችው አብይ ትምህርት ነው . . . ባንዳነት፡፡ ጣልያንን እንደ ጭራቅ የሚቆጥሩት ኢትዮጵያውያን መንፈሳቸው በፍጹም አይሸነፍም፣ አይሸውድም፡፡ ሰይጣን አዳምን ማሸነፍ የቻለው በእባብ ላይ አድሮ እንደሆነ ሁሉ ከይሲ ጣልያንም ይህንን መንፈሰ ኩሩ ትውልድ ማሸነፍ የሚችለው የሚያድርበት እባብ ካገኘ ብቻ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ስለዚህም አርባ ዓመት ሙሉ ከራሳቸው ከኢትዮጵያውያን የሚያድርባቸውን (ባንዳ) ሲሠራ ኖረ እንጂ እንደ ኢትዮጵያውያን ጊዜውን ዝም ብሎ አላሳለፈም፡፡ በአጭሩ ባንዳ ማለት ጣልያን ያደረበት ሐበሻ ማለት ነው፡፡
ጣልያን ባንዳዎቿን ሠርታ ስትጨርስ . . . ያን ጊዜ ነው ጦርነቱን ያሸነፈች ፤ ቀሪውን ሥራ የጨረሱላት ከኢትዮጵያ አብራክ የተገኙት የእኛው ወገኖች (ባንዳ) ናቸው፡፡ ባንዳ ከአፉ በቀር በመልኩ፣ በአለባበሱ፣ በቋንቋ አጠቃቀሙ ወዘተ ብቻ ምን አለፋችሁ በሁለንተናው እኛን ነው የሚመስለው፡፡ ልቡ ግን በሰይጣን (ጣልያን) ስለተያዘ የሚናገረው ነገር ሁሉ ከሬት የመረረ፣ ከክሰልም የጠቆረ ነው፡፡ ‘‘ጣልያን የመጣችው አገራችንን እንደ አውሮፓውያን ልታሰለጥን እንጂ ቅኝ ልትገዛን አይደለም፡፡ ለድጉ የጣልያን መንግሥታችን እሸ በጄ ብንል ትምህርት፣ ጤና፣ መንገድ፣ ዕድገት ወዘተ ይስፋፋል፡፡ ንጉሡ ራሳቸውም ይህንን ስለረተዱ ለጣልያን አድረዋል፡፡ ይህንን የጣልያን ሐሳብ ባለመረዳት ስትቃወሙ ለነበራችሁ ሁሉ ርኁርኁ መሪያችን ግራዚያኒ ከዛሬ ጀምሮ ምሕረት አድርገዋል፡፡ ስለዚህም በየጫካው የሸፈተ ሁሉ እጁን ለጣልያን በፈቃዱ ቢሰጥ ሹመት ሽልማት ያገኛል፡፡ ይህንን ምሕረት አሻፈረኝ ብለው የሚሸፍቱ (አርበኞች) ያሉበትን ቦታ የጠቆመ ወይም ይዞ ያቀረበ ደግሞ ከፍ ያለ ማዕረግ ይሰጠዋል፡፡’’ እና መሰል ትምህርቶች የሁሉም ባንዳዎች የዘወትር ስብከት ሆነ፡፡ በጣልያኛ እያሰቡ በአማርኛ የሚናገሩ እነዚህ ባንዳዎች በዚህ ስብከታቸው ብዙውን ወገን አታለሉት፡፡
ይህ የባንዳ ወሬ ከአገር እስከ አገር ለኅብረተሰቡ ይደረስ ዘንድ ባፍም በጡፍም መሬት ላይ ተዘራ ፣ አየር ላይ ተበተነ፡፡ የባንዳን የአፉን እንጂ የልቡን ማወቅ የተሳናቸው አያሌ ወገኖቻችን የተለፈፈው ሁሉ እውነት መስሏቸው እየበረሩ እሳት ውስጥ ገብተው ገብተው አለቁ፡፡ ነገሩ ሁሉ ግራ የሆነባቸው አያሌ ጀግኖች ደግሞ ማንንም ባለማመን ደዌ ተያዙ፡፡ ይህ ሕመማቸው የጸናባቸውም በተስፋ መቁረጥ ሰይፍ ተመትተው ወደቁ፡፡ የባንዳ ክፋቱ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቱ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ አብሮ በጦር ሜዳ ይሰለፋል ፤ ነገር ግን የአገራዊ ደኅንነት መረጃዎችን አሳልፎ ለጠላት ይሰጣል፡፡ በአካል ከኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ኢትዮጵያውያን የሚሸነፉበትን ስልት ይቀይሳል ፤ በወገኑ ላይም ሰይፍ ይመዛል፡፡  ባንዳ ባለበት ሁሉ አገር መቸም አሸንፋ አታውቅም፡፡
በባንዳ ምክንያት በ1928 ዓ/ም የተሸነፈችው ኢትዮጵያችን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በባንዳ አፍ ምክንያት እስከዛሬ የተለያዩ ሽንፈቶችን እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ ዛሬም ጠላትን በባንዳነት ከሚያገለግሉ አፎች መካከል ዋናውና ቀዳሚው ነው . . . ሚዲያ፡፡ በዋናነት ደግሞ ቴሌቪዥኖቻችንን ለጠላት ተግተው የሚሠሩ ክፉ ባንዳዎች ናቸው፡፡ ስማቸው የኛ ይመስላል፣ ለፋፊዎቹ (ጋዜጠኞች) ኢትዮጵያዊ ይመስላሉ፣ የሚናገሩት ቋንቋም የእኛን ይመስላል፡፡ ልቡናቸው ግን የእኛ ስላልሆነ ሐሰባቸውና ምኞታቸው ሁሉ ከጣልያን የከፋ ጸረ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የቀደመውን ኩሩና ጨዋ ኢትዮጵያዊ መንፈስ እንደ መርገም ጨርቅ ስለሚጠየፉት ስለአባቶቻችን መመስከር አይወዱም፡፡ በተቃራኒው የሮሜ መራሹ ምዕራባዊነት ዕብደትና ጩኸት የዘወትር ምርጫቸው ነው፡፡ የባንዳ አፍ ስለአድዋ ወይም የካቲት 12 በዓል አንዲት ቃል ትንፍሽ የማይል ዲዳ ነው፡፡ ስለ ጣልያን ላሊጋ ወይም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ግን ቀኑን ሙሉ ቢያወራ ጉሮሮው አይደክምም፡፡ የባንዳን አፍ ስለ መስቀል፣ ጥምቀት፣ ጾመ ሁዳዴ፣ ጳጉሜን፣ እንቁጣጣሽ እና መሰል የኢትዮጵያ ሥጦታዎች ለምን አታወሳም ስትሉት ይህ በሃይማኖት አልያም በብሄሮች መካከል ያለውን እኩልነት ያጠፋል ይልሀል፡፡ ‘ሰው ከጦጣ መሰል ፍጥረት የመጣ እንስሳ ነው!’ ብሎ ዘወትር ሲጮብህ ግን ጠያቂ የለውም፡፡ ባንዳ ምንጊዜም ሥራው የአንተን ታናሽነት፣ የጠላትህን ደግሞ ታላቅነት ሰማይ ድረስ አግዝፎ ማሳዬት ነው፡፡
ወንድሜ ሆይ የባንዳን አፍ ሰምተህ በፍጹም አንዳች ነገር እንዳታምን ተጠንቀቅ፡፡ አድገህ ተመድገሃል፣ ተመችቶሃል ወዘተ ቢልህ ጠልፎ ወደ ማትወጣው ጉድጓድ ሊጥልህ እያደባህ መሆኑን አውቀህ አንተ ሰይጣን ከዚህ ወግድ! በለው እንጅ በፍጹም ደስ አትሰኝለት፡፡ አልቆልሀል፣ ደቆልሃል፣ ምንም ተስፋ የለህም ብሎ ቢዝትብህ ደግሞ በጎራዴ የጣልያንን ታንክ የማረኩ የማይጨው ዘማች አባቶችህን አስበህ ጸንተህ ቁም እንጂ ሳትዋጋ በወሬ ብቻ እጅህን የምትሰጥ ፈሪ አትሁን፡፡ ስለዚህም የባንዳን ልባዊ ሐሳብ የምትመረምር ጥበበኛ እንጂ በአፉ ፉጨት ብቻ እንደ ከብት የምትነዳ ሊል ዘሊል አትሁን፡፡
የባንዳን ሐሳብ ማወቅ ከቻልህ ያን ጊዜ በኢትዮጵያ ማልያ ለፈረንጅ የሚጫወቱና ራሳቸው አገር ላይ ግብ ለማስቆጠር የሚቻወቱትን አካለት ለይቶ የሚያይ የንሥር ዓይን ይሰጥሃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከጠላት ወገን ሆነውም ለእውነት የሚቆሙና ግፍ ሲደርስብህ አንተን ለማገዝ የሚፈልጉ ብዙ መንፈሰ ኢትዮጵያውያን በዙሪያህ ታገኛለህ፡፡ ታሪክ እንደ አዶልፍ ፓርለሳክ እና ሲልቪያ ፓንክረስት፡፡ ፓርለሳክ በቆዳ ቀለም፣ በዜግነት፣ በባህልም ሆነ በሥልጣኔ ከኢትዮጵያ ይልቅ ለጣልያን ይቀርብ ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያውያን ንጽሕና እና የዋህትነት የመንፈስ ምርኮኛ ስላደረገው ከጥቁር (የቆዳ) ኢትዮጵያውያን ጋር በመሰለፍ ለመንፈስ አገሩ ታላቅ መስዋእትነትን ከፈለ፡፡ አገሪቱ ግን አሁንም የምትናገረው በባንዳ አፍ ስለሆነ አገር ለመሸጥ የሚደራደሩ ባንዳዎችን የፈጠራ ታሪክ እንጅ የአዶልፍ ፓርለሳክን እና እርሱን መሰል የኢትዮጵያ ባለውለታዎች ታሪክና አስተዋጽኦ ለመናገር ፍላጎትም ሆነ ጊዜ የላትም፡፡
ይ.ይ የካቲት 11/2010
Filed in: Amharic