>
5:13 pm - Monday April 19, 4269

አብይ ተመርጧል፣ ለማ አሸንፏል! (ስዩም ተሾመ)

ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሲሆን ያሸነፈው #ለማ_መገርሳ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የህዝባዊ ንቅናቄው ባለቤት የኦሮሚያ ቄሮዎች ናቸው፡፡ ይህን ተከትሎ በኢህአዴግ  መንግስት ውስጥ የለውጥ ንቅናቄ የተጀመረው በለማ ቡድን (Team lemma) አማካኝነት ነው፡፡ ስለዚህ በፖለቲካና ኢኮኖሚው ረገድ ስር-ነቀል ለውጥ እንዲመጣ እየጠየቀ ያለ ማህብረሰብ እና ይህን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ያለው አመራር አለ፡፡ ነገር ግን የለማ አመራር የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ሁለት መዋቅራዊ ችግሮች ነበሩበት፡፡ አንደኛ፦ በማንኛውም አግባብ የለውጡን ንቅናቄ ለመቀልበስ ጥረት የሚያደርግ ፀረ-ለውጥ የሆነ የፖለቲካ ቡድን (ህወሓት) የለማን እጅ ጠምዝዞ ይዞት ነበር፡፡ ሁለተኛ፦ በአገልጋይነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት መስፈርት ተመርጠው በክልሉ የሲቪል ሰርቪስ መዋቅር እና በድርጅቱ ኦህዴድ ውስጥ የተሰገሰጉ ካድሬዎች የሚፈለገው ለውጥ የሞት ያህል ያስፈራቸዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በክልሉ ውስጥ ካሉት 500ሺህ ሲቪል ሰርቫንቶች 100ሺህ (20%ቱ) በተጭበረበረ የትምህርት ዶክመንት ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው፡፡ አንደኛ ላይ የተጠቀሰው እንቅፋት በተገኘው  አጋጣሚ ሁሉ የለማን ቡድን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል የለማ አመራር ሁለተኛውን እንቅፋት ለመፈንቀል ሙከራ ሲያደርግ ካድሬዎቹ ከወላጃቸው ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር በመመሳጠር ለማን እጁን ጠምዝዘው ለመጣል ይሞክራሉ፡፡ የዶ/ር አብይ መመረጥ ከማንም በላይ የለማን አመራር ጠቅሞታል፡፡ ምክንያቱም የለማ ቡድን እጁን ከፀረ-ለውጥ ቡድኑ አስለቅቋል፡፡ በመሆኑም አሁን በነፃነት መወሰን፣ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ በአገልጋይነት እና ኪራይ ሰብሳቢነት መስፈርት ተመርጠው በክልሉ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉትን ሆድ-አደሮች መንጥሮ ማስወገድ ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት፣ በክልሉ ህዝብና መንግስት መካከል ያለውን እንቅፋት ፈንቅሎ መጣል ይችላል፡፡ በመሆኑም በክልል ደረጃ ስር-ነቀል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡
Filed in: Amharic