>

አሁን ባለንበት ደረጃ የራሳችንን ጉዳይ ብቻ ማንፀባረቅ የኦሮሞን ህዝብ ደረጃ አይገልፅም!! (ታዬ ደንደኣ)

በታዬ ደንደኣ
ትርጉም ፡ ጥላሁን ግርማ 
ብሄርተኝነት የራስን ብሄር ወይም ዜጋ  አብልጦ መውደድ ማለት ነው። መውደድ ደግሞ በቃላት ጋጋታ ብቻ አይገለፅም። የህዝብን ደስታ ፣ ነፃነት እንዲሁም ብልፅግና ለማረጋገጥ ዋጋ መክፈልን እና በርትቶ መስራትን ይጠይቃል።በዚህ ላይ ችግር የለብንም። የመናበቡ ጉዳይ ግን በዚህ ውስጥ ይገኛል። በጉዳዩ ላይ የጋራ መናበብን እንደ መፍጠር አላማን አቀጭጮ ማየት እና  መተናነስ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ መጥፎ ደዌ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዶ/ር አብይ “የኦሮሞን ብሄርተኝነት” ተሳድቧል የሚል ክስ እና ወቀሳ ይሰማል። ይህ ምን ማለት ነው? እንዴትስ ይሄ ይታሰባል? ዶ/ር አብይ የኦሮሞን ብሄርነኝነት እንዳልተራገሙ ለማወቅ ንግግራቸውን  ማድመጥ ሳይሆን እሳቸውን በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል። የምናውቃቸው ሰዎች ልንጠረጠራቸው አንችልም።
የኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ነው። የኢትዮጵያ እና የምስራቅ አፍሪካ ሰላም መሰረት ነው። የአፍሪካዊነት ፍልስፍናም በእጁ ይገኛል። የኩሽ ስልጣኔ ከማንም በላይ ኦሮሞን ይመለከታል።ግሪካውያን ለአውሮፓ እንደሆኑት የኦሮሞ ህዝብም ለአፍሪካ ምልክት ነው። የኦሮሞ ህዝብ ለአለም ህዝብ መድሃኒት የሚሆነውን እንኳን የሚያውቅ ህዝብ ነው። የገዳ ስርአት በዩኔስኮ የተመዘገበውም ያለምክንያት አይደለም። ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በራሱ ድንበር ብቻ ተወስኖ “ኦሮሞ…ኦሮሞ” በማለት ዘመናትን መቁጠር የለበትም። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ባለቤት መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።
 አሁን ባለንበት ደረጃ የራሳችንን ጉዳይ ብቻ ማንፀባረቅ የኦሮሞን ህዝብ ደረጃ አይገልፅም።ከራሳችን አልፈን ለሌላውም ማሰብ ይኖርብናል። ከማንም በላይ ስለኢትዮጵያ ማሰብ ይበጀናል። የአፍሪካ ልማትና ሰላም ሊያሳስበን ይገባል። ስለአለማቀፋዊነት ጉዳይም ልናስብ ይገባናል። ራሳችንን ሳንረሳ ስለኢትዮጵያ ብሄሮች ፣ ስለአፍሪቃ ቀንድ እና በአለም ላሉ ችግሮች መፍትሄ ለማምጣት ዋጋ መክፈል ይጠበቅብናል።ስለኦሮሞ ጉዳይ ብቻ መቆርቆር ትልቅነታችንን መርሳት ይሆናል። የዶ/ር አብይም ጉዳይ በዚሁ መልክ መታየት ይኖርበታል።
ሰላም ዋሉ!
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
Filed in: Amharic