>

ጠ/ሚ ዓቢይን የወራት ዕድሜ ተሰጥቶት ይታይ የምንለው በወያኔ ትግሬ ላይ ያለን አቋም ስለተቀየረ አይደለም (ከይኄይስ እውነቱ)

ጠ/ሚ ዓቢይን የወራት ዕድሜ ተሰጥቶት ይታይ የምንለው

በወያኔ ትግሬ ላይ ያለን አቋም ስለተቀየረ አይደለም

ከይኄይስ እውነቱ

አለመታደል ሆኖ ላለፉት 27 የሰቆቃ ዓመታት ጥንታዊቷና የገናና ታሪክ ባለቤት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ‹‹በታችኛው ዓለም ገዥዎች›› (በተደራጁ የወያኔ ትግሬ ወንጀለኞች) እጅ ወድቃ አገሪቱንም ሆነ ሕዝቡን ለውርደት ጥግ ዳርገውታል፡፡ በዚህም የወያኔ ትግሬና ታማኝ ሎሌዎቹ ለይቅርታ የማይመች ሰይጣናዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፡፡ መተኪያ የሌለው የእልፍ አእላፋትን ሕይወት ቀጥፈዋል፤ ከቀረንው ኢትዮጵያውያን ላይ ደግሞ የማይተኩ 27 ዓመታትን ዘርፈዋል፡፡ ዝንተ ዓለም በክፉ የሚታወሱበት በቀላል የማይሽር ጠባሳም ትተዋል፡፡ ይህ በንጹሐን ደምና በማይጠረቃ ዝርፊያ ተጠቃሚ ከሆኑት ሕወሓትና ግብር አበሮቹ በስተቀር ለተቀረነው ኢትዮጵያውያን መራር እውነት ነው፡፡

በወያኔ አገዛዝ ራሱ የፈጠራቸውና ለጥፋት ተልእኮው ከሚጠቀምባቸው እንደ አሸን የፈሉ ‹‹ታማኝ ተቃዋሚዎች›› በስተቀር ‹‹እውነተኛ የፖለቲካ ተቃዋሚ ቡድኖች›› በተለይም ጎሣ – ዘለል የሆኑትን የሚያላውስ የፖለቲካ ምኅዳር (ላልቶ የሚነበብ) አለመኖሩ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ገዥው ወያኔ ከነፈጋቸው ነፃነት በማይተናነስ መልኩ የርስ በርስ መቆራቆስ፣ በሚያስማማ አጀንዳ ላይ በጋራ አለመሥራት፣ አንዳንዱ ፖለቲካን የትርፍ ጊዜ ሥራ ማድረግ፣ ሌላው ደግሞ ዋናው የገቢ ምንጭ (መተዳደሪያው) ማድረግ፣ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ከጅምሩ የተገፋውን ሕዝብ በመርሳት የሥልጣን ወር ተረኛ ለመሆን፣ በአጠቃላይ አገርን ለመታደግ እንኳ ኅብረት በማጣት የሕዝብ ውክልና እንደሌላቸው የታዩ፣ በመሆኑም ሕዝቡ በነርሱ ላይ ያለውን ተሰፋ አለኝታ ትቶ ያለማንም አደራጅ ደረትና ግንባሩን ለጨካኞች ጥይት በመስጠት ባደረገው ሰላማዊ እምቢ ባይነት እነ ለማና ጠ/ሚ ዓቢይ ከንፍሮው ወያኔ ውስጥ የማይነፍሩትን የባቄላ ፍሬዎች ሆነው ተገኝተዋል፡፡

እኔ ጠ/ሚ ዓቢይንና አጋሩን ለማን የማያቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ዓመፃና የራሳቸው ፍንገጣ ውጤት አድርጌ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለማና ዓቢይን ከወያኔ ትግሬ ነጥዬ ለማየት የምፈልገው፡፡ ለብዙዎችም እንቆቅልሽ የሚሆነው ይህ ይመስለኛል፡፡ እንደውም አንድ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ጸሐፊ የጠ/ሚ ዓቢይን በዓለ ሢመት ንግግር ተከትሎ በጅምላው ሕዝብ፣ ፊደል በቆጠረውና በምሁራኑ ዘንድ የተፈጠረውን ስሜት ተመልክተው ‹‹ዕብደት›› ባይሉትም ሰዉ ምን ነካው በሚል አንድምታ ‹‹ ይህ በኢትዮጵያ እንግዳ ጊዜ ነው›› በማለት የጽሑፋቸው ርእስ አድርገው ትዝብታቸውን ማስፈራቸውንና በማጠቃለያቸው እንደ ብዙኀኑ ፍላጎት እንዲሆን መመኘታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ አዎን እንግዳና አስገራሚ ጊዜ ነው፡፡ ወያኔ ጠፍጥፎ በአምሳሉ የሠራቸው ሦስት ድኩማን ድርጅቶች ለትግሬው አገዛዝ ሎሌ መሣሪያ ሆነው የራሳቸውን ሕዝብ ቁም ስቅሉን አላሳዩትም? አላስገደሉትም? አላሳሰሩትም? አላዘረፉትም? ወዘተ. በቡድን ደረጃ ሁሉንም አድርገዋል፡፡ በግለሰብም ደረጃ በአስነዋሪ ድርጊታቸው ተጠያቂዎች የትየለሌ ናቸው፡፡ ሆኖም ለማና ዓቢይ በትግሬ ወያኔ እንደተገፈገፈው ሕዝብ እነሱም ሎሌነት በቃን እምቢኝ አሻፈረኝ ብለው ከሕወሓት አፈንግጠዋል፡፡ ከወያኔ ትግሬ አገዛዝ ነው ያፈነገጡት፡፡

  • ያፈነገጡት ወያኔ ላለፉት 27 ዓመታት ሲከተል ከቆየው  የጎሣ እና የጥላቻ ፖለቲካ ነው፤
  • ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን ሲሠራ ከነበረው የወያኔ ቆሻሻ አስተሳሰብና ድርጊት ነው ያፈነገጡት ፤
  • ያፈነገጡት ሐሰት፣ ቅጥፈት፣ ድንቁርናን፣ ዝርፊያን በኢትዮጵያ ምድር ካሠለጠነው፣ ነውርን ክብር ካደረገው የወንበዴው ሕወሓት ቡድን ነው ፤
  • ላይታደስ ከሥር መሠረቱ ከበሰበሰው የወያኔ አገዛዝ ነው ያፈነገጡት ፤
  • ያፈነገጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላነሳቸው የፍትሕ፣ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የመንግሥተ ሕዝብ፣ የሕግ የበላይነት ወዘተ. ጥያቄዎች ግድያ፣ ሽብር፣ አፈና፣ እስር፣ ስደት፣ እንግልት መልሱ ከሆነውና ሳይገባው ምንይልክ ቤተመንግሥት ከተቀመጠው ከደደቢቱ ሽፍታ ነው፤
  • ጥፋትን ለማመን፣ ይቅርታን ለመጠየቅ ልቡን ካደነደነው፤ ለእውነትና ዕርቅ፣ ለፍቅርና ለሰላም ባይተዋር ከሆነው የሕወሓት ዕኩይና ዕቡይ ቡድን ነው ያፈነገጡት፤
  • ያፈነገጡት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን በዓለም ፊት ካዋረደው ወራዳው የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ነው፤
  • ለወያኔ ትግሬ ሎሌ፣ አሽከር በትር ከመሆን ነው ያፈነገጡት፤
  • ያፈነገጡት ከፋፋይ፣ በታኝ፣ የአጥፍቶ ጠፊነት ድውይ አስተሳሰብ ከተጠናወተው ወያኔ ነው፤
  • ሕወሓትንና ታማኝ ሎሌዎቹን አስቀድሞ ከተፋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በጋራ ለመቆም ነው ያፈነገጡት፤

እነዚህና ሌሎች አዎንታዊ ማፈንገጦች ጠ/ሚ ዓቢይ ከሥርዓተ ሢመቱ ጀምሮ የአብዛኛውን ሕዝብ ድጋፍ ለማግኘትና ስሜቱንም ለማዳመጥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እያደረጋቸው ባሉ ንግግሮችና ውይይቶች ተንፀባርቀዋል፡፡ ቃል ኪዳንም ተገብቶባቸዋል፡፡ የተገባ ቃል ደግሞ ያልተከፈለ ዕዳ ነው፡፡ ይህ ሸክም ቀላል አይደለም፡፡

ለመሆኑ ከአዲሱ ጠ/ሚ እንደ ግለሰብ ‹መሪ›ም ሆነ እንደ ‹አዲስ አስተዳደር› የምንጠብቀው ምንድን ነው? ለሽግግር መደላድል የሚፈጥሩ መለስተኛ ለውጦችን ወይስ ሥር ነቀል ለውጥን? ከወቀሳና ከትችት አልፈን ሸክሙን ለማቃለል የእኛ ድርሻ ምንድነው ብለን ጠይቀናል? በወጣት ‹መሪነቱ› ለሚፈጸም ስህተት ትንሽም ቢሆን ‹የማርያም መንገድ› ለመስጠት ቸርነቱ አለን ወይስ ይጎድለናል?

ሕዝቡ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ተቃዋሚ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የሃይማኖት ተቋማት ሁላችንም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ በቡድንና በግለሰብ የሚጠበቅብንን እየሠራን የጠ/ሚ ዓቢይ መልካም ውጥኖች ከግቡ እንዲደርሱ በምንችለው ሁሉ እናግዘው፡፡ ለዚህም እንዲረዳን ጠ/ሚኒስትሩ ባጭርና በመካከለኛ ጊዜ ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን ዐቢይ አገራዊ ተግባራት በማያሻማ መልኩ አንድ ሁለት ብሎ ከገለጸልን ጥረቱን ለማገዝ፣ እንቅፋቶቹን ሁሉ በሰላም በማስወገድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ ይሆናል፡፡

የወቅቱ ጽሑፎችና ንግግሮች በአመዛኙ በጠ/ሚ ዓቢይ ላይ ያለ ተስፋና ሥጋት፣ ጥርጣሬና እስከነአካቴውም ተስፋ መቁረጥ ይመለከታል፡፡ በተለይ ከአንዳንድ ተቃዋሚ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚጻፈው አስተያየትና የሚደመጠው ንግግር ማስረጃን መሠረት ካለደረገ አስተሳሰብ የመነጨና መላምታዊ ግምት በመሆኑ ዓላማው ከማደናገርና ተስፋ ከማስቆረጥ ባለፈ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ ቸግሮኛል፡፡ ይህ አዝማሚያ ለእኔ ገንቢ አይመስለኝም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ በጎ ተመኝተንም ከሆነ ወደዚያ የሚያደርስ አይመስልም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ ተቃዋሚ ‹‹የፖለቲካ ማኅበራት›› በተለይም በጎሣ መስመር የተደራጃችሁ የየፓርቲያችሁን አቋምና ፕሮግራም ወይም ልዩነታችሁን እንደያዛችሁ ልትተባበሩ በምትችሉበት የጋራ ጉዳዮች ላይ (በዋናነት ኢትዮጵያን ወደገደል ጠርዝ ከገፋት የትግሬ ወያኔ አገዛዝ ለመታደግ) ኅብረት ፍጠሩ እያለ ሕዝቡ ለበርካታ ዓመታት ሲወተውታችሁ እምቢኝ አሻፈረኝ አላላችሁም? ጽንፈኞች ደግሞ ኢትዮጵያን ካልበታተንን እንቅልፍ አይወስደንም አላላችሁም? ኅብረት ለመፍጠር ሙከራ ያደረጋችሁም በጥርጣሬ መንፈስ በመሆኑ ጥረታችሁ በጅምር የቀረ እንጂ በሚፈለገው ጊዜ አልደረሳችሁም፣ ሕዝብንም ለማስተባበር አልቻላችሁም፡፡ ይህን በወቅቱ ብታደርጉ ኖሮ (አሁንም ቢሆን ኅብረትና ተቀራርቦ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ስድሳ ፓርቲ አትፈልግም፡፡? ርእዮተ ዓለምን፣ ዜግነትን፣ መርሆዎችን፣ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን መሠረት ያደረጉ ቢበዛ ከ5 ያልበለጡ /በሂደት ወደ 2 የሚጠቃለሉ/ ጥራት ያላቸውን አገር አቀፍ የፖለቲካ ማኅበራትን እንጂ፡፡) ኅብረቱንና ተቀራርቦ ለጋራ ዓላማ የሠራችሁ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን በተግባር ለመውደዳችሁ፣ አንድነቷን እንደምትፈልጉ፣ ለአገርና ለሕዝብ ቅድሚያ እንደምትሰጡ አንድ መገለጫ/ማሳያ ይሆን ነበር፡፡ አሁን የወያኔ ሎሌነት በቃን ብለው ያፈነገጡ ወጣቶች የኢትዮጵያን ክብር አንድነት ልዕልና ሲያነሱና ሕዝቡን በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ ለማስተባበር ሲሞክሩ ቢያንስ እስከነ ጥርጣሬአችሁ ጥቂት ጊዜ ሰጥቶ ማየት/ አጋዥ መሆን፤ ባይቻል ደግሞ እንደ ወያኔ ትግሬ እንቅፋት ላለመሆን መጣር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ እነ ለማና ዓቢይ የጀመሩት ጥረት ሁላችን ወደምንፈልገው አቅጣጫ የሚያመራ ከሆነ እንደ ደናቁርቱ የወያኔ ቡድን እኛ ያሰብነው ብቻ ነው ለኢትዮጵያ ፈተናዎች መፍትሄ የሚሰጥ የሚል ግብዝናና መመፃደቅ እንደሌለብን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ወያኔ ትግሬ (ሕወሓት) በጻእረ ሞት ላይ ሆኖም አድፍጧል፡፡ አለሁ ለማለት በቅጥረኛ የወታደራዊ ዕዙ አማካይነት ለጊዜው የተቆጣጠረውን የግል ደኅንነቱንና ሠራዊቱን በመጠቀም እንደ አበደ ውሻ እዚህም እዚያም ትንኮሳውንና መቅበዝበዙን አላቋረጠም፡፡ ጠ/ሚ ዓቢይ ቃል እንደገባው የወያኔን የደኅንነት መ/ቤት ወደ እውነተኛ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት ተቋምነት ከቀየረውና በሁሉም ‹‹መንግሥታዊ አካላት›› ውስጥ የተሰገሰጉትን ከአንድ አካባቢ የመጡ ታማኞችንና ሆድ አደር ሎሌዎችን መመንጠር ከተቻለ የጠ/ሚኒስትሩ መንገድ ጠራጊነት ሥራ በአንፃራዊነት የቀለለ ይሆናል፡፡

ሕገ ወጥ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ጊዜያዊ በመሆኑ በቅርቡ (በአዲሱ ካቢኔ ውሳኔ) እንደሚነሳ ተስፋ አደርጋለኹ፡፡

ኹላችን ልንገነዘብ የሚገባን በመጠባበቅ ወይም እጅን አጣጥፎ በመቀመጥ የሚመጣ ተአምር የለም፡፡ ስለሆነም ከግምታዊ/ነሲባዊ ከሆነ ትችትና ነቀፋ ወጥተን ትክክለኛ መረጃና ማስረጃን መሠረት ባደረገ አስተሳሰብ የራሳችንን ዝግጅት ከማድረግ ጎን ለጎን ጠ/ሚ ዓቢይ ከወያኔ ትግሬ ጠልፎ የመጣልና ከሕዝብ የማጋጨት ሴራ በመታደግ የሚገኘውን አገራዊ ትርፍና ኪሣራ ሰክኖ መተንተን የሚገባ አይመስላችሁም? የአገርን ጉዳይ በትርፍና ኪሣራ ስሌት ሳስቀምጠው አቅልላችሁ እንዳታዩብኝ፡፡

የኔ ሥጋት ተዳክሞም ቢሆን ያደፈጠው የሕወሓት ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ ነው፡፡ ለዚህ አውሬ ቡድን በጭራሽ ምንም ክፍተት መፍጠር የለብንም፡፡ ከልብ በመጨነቅ ትችትና ነቀፌታ የምትሠነዝሩ ወገኖች (አጀንዳ ተነጠቅን /ለነገሩ አገራዊ ፈትለ ነገር ላይ ማንም የሞኖፖል መብት የለውም/፣ ተቃዋሚነታችን ትርጕም አጣ ወዘተ. በማለት ድብቅ ፍለጎት ያላቸው አካላት እንደተጠበቁ ሆነው) ሥጋት ጠ/ሚ ዓቢይ የዘረኛውን የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ባለበት ሁኔታ ለማስቀጠል እየሠራ ያለ አስመሳይ ነው ወይም ይህን ዓይነት አደገኛ ተልእኮ ላለመያዙ ምንም ዋስትና የለንም የሚል ነው፡፡ አያድርገውና ይሄ ቢሆን በእናንተ በኩል የመጠባበቂያ ዕቅድ አዘጋጅታችኋል ወይ? ከአሉባልታው ይልቅ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱ ማናቸውም ዓይነት ክስተቶች ራስን ማዘጋጀቱ አይሻልም? እውነቱን ለመነጋገር ይህን የኋለኛውን ሥጋት በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ያቀረበ ቡድንም ሆነ ግለሰብ አላየሁም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የመላምት ጽሑፍም ሆነ ንግግር የሕዝብን ልብ ከመክፈል፣ ከማዘናጋት፣ ውዥንብር ከመፍጠርና ተስፋ ከማስቆረጥ የተለየ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም፡፡ በተለይም አንድ ካገር ሸሽቶ የወጣ የወያኔ ደኅንነት የቀድሞ አባል በቅርቡ የሰጣቸው ቃለ መጠይቆች ገንቢ ሆነው አላገኘኋቸውም፡፡ የወያኔ ደኅንነት ተቋምን፣ ምንም አቅም የሌለው ጠ/ሚ ዓቢይ ቀርቶ የሕወሓት ዋና ሰዎች እንኳን ሊነኩት የማይቻላቸው አይበገሬ ድርጅት አድርጎ ሥሎልናል፡፡  ይህ ግለሰብ ከወያኔ ተፋትቶ ወጣሁ ቢልም በወያኔ ደኅንነት አባልነት ዘመኑ በአገርና በሕዝብ ላይ ምን ጥፋት/ወንጀል እንደሠራ ለጊዜው ማስረጃ በእጃችን ስለሌለ አናውቅም፡፡ (መቼም የወያኔ ደኅንነት የአገርና የሕዝብ አለመሆኑን በሚገባ ያውቀዋል) ይህ የወያኔ ትግሬ የግል ተቋም ወያኔ በምድረ ኢትዮጵያ ቆሻሻ እና ነውረኛ ድርጊቶችን የሚያስፈጽምበት በአመዛኙ የኅሊና ቢሶች ስብስብ እንደሆነ ላለፉት 27 ዓመታት ከተፈጸሙት ግፎችና በደሎች ማንም ኢትዮጵያዊ የሚገነዘበው ነው፡፡ ታዲያ የዚህን ግለሰብ ንጽሕና ማን መሠከረለት? እጁ እንደወያኔ በንጹሐን ኢትዮጵያውያን ደም ተጨማልቆ ከሆነ የፈጸመውን ጥፋት አምኖና ከልቡ ተጸጽቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ጠይቋል ወይ? የሚናገረውን ሁሉ በማስረጃ እንዲያስደግፍ ሲጠይቅ በስሜታዊነትና እኛ ተራ ዜጎች ስለወያኔ ደኅንነት በእኛና በወገኖቻችን ደርሶብን ካየነው/ከሰማነው እንዲሁም በመላምት ከምንናገረው የተለየ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በማስረጃ የነጠረ ሐቅ ይዞ ሳይመጣ እሱ ሕይወቱን ለማትረፍ (በዚህ ምክንያት ወጥቶ ከሆነ) ሸሽቶ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአረመኔዎች ጥይት እንዲያልቅ የእልቂት ጥሪ ለማድረግ ምን የሞራል ብቃት አለው?

ለማጠቃለል ለጠ/ሚ ዓቢይ እነዚህ ጉዳዮች ቢፈጸሙ በማለት የተለያዩ ወገኖች ዝርዝር ፍላጎታቸውን፣ አስተያየታቸውን፣ ምክራቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡ እኔ የምመኘው፣ ሰው ከልቡ ሞልቶ የተረፈውን ይናገራል እንዲል መጽሐፍ ይህ ወጣት ‹መሪ› የተናገራቸውን ለአገር የሚበጁ አሳቦች በቅንነት በመውሰድ፣ መልካም አገራዊ ውጥኖቹን ኹሉ ለመፈጸም እንዲችል የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳው ማለትን ነው፡፡

በመጨረሻም እንደ ሥርዋጽ የሚወሰድ አንድ መሆን የሚገባው ምኞት ላቅርብ፤ የምሻው ጉዳይ በአንፃራዊነት ቀላል÷ አገራዊ አንድምታው ግን ታላቅ የሆነ፣ ቢፈጸም አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያስደስት ጥሩ ጅምር  ይመስለኛል፡፡ ይኸውም ፕሬዚዳንት ለማ በሚያስተዳድረው ክፍለ ሃገር እንደተደረገው ኹሉ በቀሪውም የኢትዮጵያ ክፍል መታወቂያችን በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ እንዲሰጠንና የአገር ባለቤትነታችን ቢያንስ በመታወቂያ ካርዳችን ይገለጽ ዘንድ አስቸኳይ መመሪያ ቢተላለፍ፡፡

አምላከ ኢትዮጵያ መጪውን ጊዜ የፍቅርና የሰላም፣ የመደማመጥና የመተሳሰብ፣ የእውነትና የዕርቅ ያድርግልን፡፡

Filed in: Amharic